ሪፖርት | በሁለቱ አጋማሾች የተቆጠሩት ግቦች ጊዮርጊስ እና ሲዳማን አቻ አለያይተዋል

ከመከላከያ ጋር ነጥብ ተጋርተው የመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለት ነጥብ ከጣሉበት ፍልሚያ አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ሄኖክ አዱኛ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ አቤል ያለው እና ቡልቻ ሹራ እንዲያርፉ አድርገው ደስታ ደሙ፣ ጋቶች ፓኖም፣ተገኑ ተሾመ እና ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። እንደ ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ባሳለፍነው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ተጫውተው አቻ የተለያዩት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ሦስት ለውጦችን አከናውነዋል። በለውጦቹም በጊት ጋትኩት፣ ቴዎድሮስ ታፈሠ እና ዳዊት ተፈራ ምትክ ግርማ በቀለ፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና ብርሃኑ አሻሞ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ እንዲገቡ ተደርጓል።

ከወትሮው በተለየ የተጨዋች ምርጫ እና አደራደር ቅርፅ ጨዋታውን የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ጅማሮ ላይ አንፃራዊ ብልጫ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ሲዳማ ቡናዎችም የጊዮርጊሶችን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማምከን እና የሚያገኟቸውን ኳሶች በቶሎ ወደ አደጋነት ለመቀየር ሲጥሩ ተስተውሏል። ውጥረት እና ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ ገና ከጅምሩ አንስቶ ማስተናገድ የጀመረው ጨዋታውም እስከ 21ኛው ደቂቃ ድረስ ሙከራ ሳይደረግበት የቀጠለ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ግን አማኑኤል ገብረሚካኤል ከርቀት አክርሮ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ በቁጥር በዛ ብሎ ሲዳማ የግብ ክልል ተገኝቶ ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ ወደ ግብ መቶት ያኩቡ መሐመድ በመለሰው እና የተመለሰውን ኳስ ሀይደር ለመጠቀም በጣረው አጋጣሚ መሪ ለመሆን ሞክሯል።

ጨዋታው 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን የሲዳማዎች የመጀመሪያው ሙከራ ወደ ግብነት ተቀይሮ መሪ ተገኝቷል። በዚህም ጊዮርጊስ መርጦት የገባው 3-2-3-2 (WW Formation) የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ላይ የመስመር ተመላላሽ ቦታ ላይ የተሰለፉት ከነዓን እና ተገኑ ወደ መሐል እና ወደ ፊት በሚሳቡበት ሰዓት የሚገኘውን ቦታ ለማጥቃት የተንቀሳቀሱት ሲዳማዎች በይገዙ አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል። ይገዙም ከመሐል የተነሳው ኳስ ብሩክ እግር ስር ሲደርስ በብሩክ እና በጊዮርጊስ ተከላካይ (ደስታ ደሙ) ጀርባ ራሱን ነፃ በማድረግ ኳስ ተቀብሎ ቻርለስ ሉክዋጎ ባጠበበበት ቋሚ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። አጋማሹም በብቸኝነት በተቆጠረችው የይገዙ ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሮ ላይ በቶሎ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት መታተር የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በደቂቃዎች ልዩነት አማኑኤል ገብረሚካኤል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከፈጠራቸው አጋጣሚዎች በተጨማሪ በ52ኛው ደቂቃ ተገኑም ከቀኝ መስመር ባሻገረው እና ከነዓን ለመጠቀም በሞከረው ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። አሠልጣኝ ክራምፖቲችም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አከታትለው በማስገባት ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በተለይ ደግሞ በ60ኛው ደቂቃ የተገኘ የቅጣት ምት ሲሻማ አማኑኤል አግኝቶ ወደ ግብ ቢመታውም ተክለማርያም ሻንቆ አምክኖበታል።

የሚፈልጉት በእጃቸው የገባላቸው ሲዳማዎች በዚህኛው አጋማሽ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ከኳስ ውጪ ስንመለከታቸው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን በቀጥተኛ አጨዋወት መሪነታቸውን ለማስፋት አልፎ አልፎ ሲጥሩ ነበር። ነገርግን በ75ኛው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮባቸው አቻ ሆነዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ ተከላካዮች በግንባር ሲያወጡት ቡልቻ አግኝቶት ለአልዓዛር ከሰጠው በኋላ የመጨረሻውን ኳስ ያገኘው ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ በግራ እግሩ ወደ ጎል በመምታት ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል። አቻ የሆኑት ሲዳማዎች በሽማሪ ደቂቃ ብሩክ ሙሉጌታ በሳጥኑ መግቢያ ላይ ከደስታ ደሙ ያስጣለውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ አክርሮ መትቶ ወደ ላይ ተሰቀለበት እንጂ መሪ ሆነው ጨዋታውን ሊያገባድዱ ነበር። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ፈጣን ጥቃቶች በመሰንዘር ወደ ሳጥኑ የገቡባቸው እጅግ አደገኛ አጋጣሚዎች በመጨረሻ ኳስ የቅብብል ጥራት መጓደል ወደ ሙከራነት ሳይቀየሩ ጨዋታው ተጠናቋል።

በውጤቱ መሠረት ወደ ጨዋታው ሲገቡ የነበራቸውን አንድ ነጥብ ከጨዋታው በኋላም ይዘው የወጡት ቅዲስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና በቅደም ተከተላቸው ወደ ስድስተኛ እና አስረኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።