የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ሲዳማ ቡና

በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት እና ተጋጣሚ አሰልጣኞች ይህንን ቆይታ አድርገዋል።

ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

የ1-1 ውጤቱን አንፈልገውም ፤ ለማሸነፍ ነበር የገባነው። ግን መጀመሪያ ገብቶብን ለማሸነፍ የያደረግነው ጥረት ጥሩ ነው። ሁለት ሦስት ኳሶች አግኝተን አንዱን ተጠቅመናል። አሁንም ገና ይቀረናል ለማሸነፍ ነበር የገባነው።

በጨዋታው ሙከራዎች ስለማነሳቸው

ሁለታችንም የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ስለገባን የማጥቃት ክልላችን ላይ አልተሳካልንም። ተደራጅተን ስለመጣን ያገኘነው ዕድል ጥቂት ነው። እነሱ ቀድመው አገኙ እኛም ሁለተኛ ላይ አግኝተን 1-1 ወጥተናል።

ስለአቤል እና ቡልቻ ቅያሪ የማጥቃት ለውጥ

ጎል ከገባብን በኋላ ወደ ኋላ ማፈግፈግ አንፈልግም ፤ ማግባት የግድ ስለሚገባን። የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ሁለት ተጫዋቾች ቀይረን አስገብተናል። በፈለግነው መጠን ባይሆንም በጥቂቱ ተሳክቶልን አንድ ግብ አግብተን እኩል ለእኩል ልንወጣ ችለናል።

ስለእስካሁኑ የቡድኑ አካሄድ

በምንም ተአምር ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚመጥን ነገር እያደረግን አይደለም። ያንን ለማስተካከል አሁንም ጊዜ አለን። ለማሸነፍ ነው የምንገባው ሜዳ ውስጥ የሚገጥመን ግን ሌላ ነው። ያንን ከተጫዋቾቻችን ጋር በመነጋገር የተሻለ ነገር ሰርተን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።

ስለስካሁኑ የቡድኑ ቅርፅ

በትክክል ሙሉ ለሙሉ ቅርፁ አልመጣም። ማግኘት የፈለግነውን ነገር እስካሁን አላገኘንም። ገና ይቀረናል እዛ ላይ ለመድረስ።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

ባቀድነው መንገድ አልሄደም። ያሰብነው ለማሸነፍ ነው ግን አቻ ወጥተናል። ይህም ቢሆን ግን ተጋጣሚያችን ጠንካራ ቡድን ነው። ስለዚህ ምንም የሚከፋኝ ነገር አይደለም።

ሙከራዎች ስላለመታየታቸው

የጉልበት ጨዋታ ይበዛ ነበር። ዳኝነቱ እዚህም እዛም እየተነፋ ይቆም ነበር። አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ። ከዚህ አንፃር እና ጥብቅ የነበረ መከላከል ስለነበር ነው ሙከራዎች ያነሱት።

እስከ 86ኛ ደቂቃ ቅያሪ ስላለማድረጋቸው

መቀየር ዝም ብሎ ግዴታ አይደለም ። አስፈላጊ ሲሆን ትቀይራለህ አስፈላጊ ካልሆነ ደግሞ ላትቀይር ትችላለህ። ዘጠና ደቂቃውን በ11ዱ ልትጨርስ ትችላለህ።

ተጠባባቂዎች ሁለት ቢጫ ካርድ ስለማየታቸው

ይህ ከምን አኳያ እንደሆነ ግልፅ ነው። የነበረው የዳኝነት ሁኔታ ነው። የተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ማንም ያየው ስለሆነ እኔ ምንም የምለው የለኝም በዚህ ጉዳይ ላይ።

ስለእስካሁኑ የቡድኑ ቅርፅ

ይመጣል ፤ እየተስተካከለ ነው። አልሸነፍ ባይነቱ ጥሩ ነው። በአምስት ጨዋታ ብዙ ማለት ባይቻልም ተስተካክለን ወደ ፊት እንራመዳለን የሚል ዕምነት አለኝ።