ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

የአምስተኛው ሳምንት የመጨረሻ በኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር መሀከል ተደርጎ ቡና የ2-1 ባለድል ሆኗል።

በሊጉ ግርጌ ተቀምጠው የተገናኙት ተጋጣሚዎቹ ከመጨረሻ ጨዋታቸው አንፃር በርካታ ለውጦች አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል። ቡናዎች ወንድሜነህ ደረጄን በቴዎድሮስ በቀለ ፣ አልዓዛር ሺመልስን በያብቃል ፈረጃ ፣ እንዳለ ደባልቄን በኃይሌ ገብረትንሳይ እንዲሁም ታፈሰ ሰለሞንን በሮቤል ተክለሚካኤል ተክተዋል። በጅማ በኩል ደግሞ አድናን ረሺድ በመሐመድኑር ናስር ፣ ምስጋናው መላኩ በብሩክ አለማየሁ ፣ ሱራፌል ዐወል በሮጀር ማላ ፣ ታምራት ዳኜ በአልዓዛር ማርቆስ ፣ ወንድወሰን ማርቆስ በበላይ ዓባይነህ እንዲሁም ተስፋዬ መላኩ በትንሳኤ ያብጌታ ቦታ ተለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በጨዋታው ጅማሮ በተለመደው አኳኋን ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ ክፍተቶችን ፍለጋ ቅብብሎችን ሲከውኑ ከኋላ አምስት እየሆኑ ጠንቀቅ ብለው ጨዋታቸውን የጀመሩት ጅማዎች ደግሞ ወደ ግራ መስመር ያደሉ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ሲጠባበቁ ታይተዋል። ጨዋታው በዚህ መልኩ በፍጥነቱ ዝግ ብሎ ሲቀጥል የመጀመሪያው ሙከራ 17ኛው ደቂቃ ላይ ታይቷል። ጅማዎች በግራ በኩል በፈጣን ጥቃት ገብተው ሦስት ለሁለት በሆነ ብልጫ ሳጥን ውስጥ ቢደርሱም ምስጋናው መላኩ እና ዱላ ሙላቱ ከቅርብ ርቀት አከታትለው የሞከሩትን ኳስ አቤል ማሞ ሊያድንባቸው ችሏል።


ኢትዮጵያ ቡናዎች በሂደት የተጋጣሚያቸው የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት መዳረሻቻውን አቡበከር ናስርን ባደረጉ ቅብብሎች ወደ ሦስተኛው የሜዳ አጋማሽ ተጠግተው ተንቀሳቅሰዋል። አልፎ አልፎ በራሳቸው ሜዳ ላይ ሆነውም ጅማዎችን ወደ ፊት ለመሳብ እና እንዲበተኑ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ማጥቃታቸው ወደ ግብ ክልል መቅረብ የጀመረው ወደ መጨረሻ ላይ ነበር።

38ኛው ደቂቃ ላይ የቡና ቅብብሎች ሰብረው የገቡበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ከሮቤል ተከክለሚካኤል የተነሳውን ኳስ ዊሊያም ሰለሞን አመቻችቶትለት አስራት ቱንጆ በተከላከዮች መሀል አምልጦ በመግባት ያደረገው ሙከራ በታምራት ዳኜ ድኗል። ቡናማዎቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል በጅማ ሳጥን የሚገኙባቸው ቅፅበቶች ጎላ ማለት ሲጀምሩ የ43ኛ ደቂቃው የኃይሌ ገብረትንሳይ የተሻማ የርቀት ቅጣት ምት በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ቅፅበት የተሻለው ሙከራ ነበር። ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህ አካኋን የተጋጣሚያቸው የኳስ ፍሰት ከአቅም በላይ ወደ ሆነ ማጥቃት እንዳይቀየር ማድረግ ችለው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ ቢሆንም አቡበከር ናስር በተከታታይ ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል። 52ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ ላይ ከካቋረጡት ኳስ ጥቃት የሰነዘሩት ቡናዎች የአብቃል ፈረጃ በተከላካዮች መሀል በሰነጠቀው እና አቡበከር ናስር አምልጦ ገብቶ በጨረሰው ኳስ ቀዳሚ ሲሆኑ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቡበከር በድጋሚ አምልጦ በመግባት ከቀኝ መስመር ከኃይሌ ግብረትንሳይ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሲልከው የግብ ጠባቂው ታምራት ስህተት ታክሎበት ሁለተኛ ግብ ሆኗል። ጨዋታ ከግቦቹ በኋላ ክፍት ሲሆን ጅማዎች ከኋላ በተላከ ረጅም ኳስ 59ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አፋፍ ሲደርሱ ምስጋናው መላኩ አከታትሎ ያደረጋቸው ሙከራዎች በአቤል ማሞ እና በግቡ ቋሚ ተመልሰዋል።

 

ጅማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ከግቦቹ በኋላ ወደ ፊት ገፍተው ለመጫወት ጥረት ጀምረዋል። በዛው መጠን ቡናዎችም ክፍተት ያገኙ ሲሆን በተለይም አስራት ቱንጆ ሁለት ተከላካዮችን ቀንሶ ሳጥን ውስጥ በመድረስ ያደረገው ሙከራ የምት ጥንካሬ አነሰው እንጂ ሦስተኛ ግብ ለመሄን ቅርብ ነበር። ጅማዎች በሂደት በቀጥተኛ ኳሶች ወደ ቡና ሳጥን መቅረብ ሲጀምሩ የተሻለው የቡድኑ ሙከራ የታየው 80ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የአስናቀ ሞገስ ቅጣት ምት ግን በአቤል ማሞ ተመልሷል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግን የቡናን የኳስ ምስረታን ቀኝ መስመር ላይ አቋረጠው የከፈቱት ፈጣን ጥቃት በመስዑድ መሀመድ ሲመቻችለት ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግብነት ለውጦታል።

ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር ቢደረግባቸውም ውጤቱን የሚቀይሩ አልሆኑም። 90ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከቅጣት ምት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ በታምራት የዳነበት ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን አምስት አድርሶ ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ጅማ አባ ጅፋር ግን አሁንም ያለምንም ነጥብ በሊጉ ግርጌ ቀርቷል።

ያጋሩ