“የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” አቶ ባህሩ ጥላሁን

ትናንት የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የዕለቱ ዳኛን አስመልክቶ ሲዳማ ቡና በፃፈው ደብዳቤ ዙርያ አቶ ባህሩ ጥላሁን የሚሉት አላቸው።

በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚያደርጉት ጨዋታ አሰቀድሞ የዕለቱ አልቢትር ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ጨዋታውን እንዲመሩ መመደባቸው በሲዳማ ቡና በኩል ቅሬታ እንዳስነሳ እና ዳኛው እንዲቀየሩ የሚል ክስ አዘል ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት አስገብተው እንደነበር ይታወቃል።

ሲዳማ ቡና እንደ ምክንያት ያቀረበው አንደኛው ጉዳይ ዳኛው አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማን አጫውተው አርባ ስምንት ሰዓት ያልሆነው እንደሆነ እና በቂ ዳኛ ባለበት ሁኔታ መመደባቸው ተገቢ አይደለም የሚል ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዳኛው በግሉ የተጋጣሚያችን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ እንደመሆኑ መጠን ጨዋታውን እንዳይመሩ እንጠይቃለን የሚል ነበር። ሆኖም የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ የሲዳማን ክስ አዘል ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የትናቱን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እንዲመሩ ማድረጋቸው ይታወቃል።

አሁን መነጋገሪያ ጉዳይ የሆነው በዓምላክ በምን መረጃ እና ማስረጃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነው በማለት የሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ አይመደበብን ብሎ ጠየቀ የሚለው ጉዳይ ነው። ለዚህ ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡን የፌዴሬሽኑን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንን አናግረናል። 

“በዓምላክ የምንመካበት ሀገራችን በተለያዮ መድረኮች ገፅታዋን በበጎ እያስጠራ የሚገኝ ለብዙዎች ዳኞች ተምሳሌት የሆነ ዳኛችን ነው። ሲዳማ ይህን ለማለት ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ከዳኞች ኮሚቴ ጋር በመሆን ማብራሪያ እንዲሰጡ የሚደረግ ሲሆን ፌዴሬሽኑ በዝምታ የማያልፈው የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድበት ነው።”

ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን ተከታትላ የምታቀርብ ይሆናል።