በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋች የዚህኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 አቡበከር እና ጎል ታርቀዋል
ዐምና በ29 ግቦች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው አቡበከር ናስር በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ግቡን ለማግኘት አምስት የጨዋታ ሳምንታትን ጠይቋል።
በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር በአቻ ውጤት ሲለያይ ከአምና በተሸጋገረ የአምስት ቢጫ ካርድ መነሻነት መሰለፍ ያልቻለው አቡበከር በተከታታይ በነበሩት ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ተስኖት ቆይቶ ነበር።
በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ባደረገው ጨዋታ አቡበከር ናስር ከ322 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ የ2014 የውድድር ዘመን የመጀመሪያውን ግብ ከያብቃል ፈረጃ የደረሰውን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ ማስቆጠር ችሏል። በዚህች ግብ የተነቃቃው አቡበከር ናስር ከሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በኋላ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
አቡበከር ናስር ከዚህ በኋላ የሚዳኘው በአምናው አስደናቂ የውድድር ዘመን ግስጋሴው ጋር እንደመሆኑ በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ግብ የማስቆጠር ጫና ውስጥ ሆኖ ጨዋታዎችን እንደመጀመሩ ከዚህ ውጪያዊ ጫና ጋር ራሱን በምን ዓይነት መንገድ አስማምቶ ይጓዛል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 የተደበላለቀ ቀንን ያሳለፈው በረከት ወልደዮሐንስ
ወላይታ ድቻ ከመመራት ተነስቶ ሰበታ ከተማን 4-2 ባሸነፈበት ጨዋታ የወላይታ ድቻው የመሀል ተከላካይ በረከት ወልደሐሀንስ እጅግ የተደበላለቀ ዓይነት የጨዋታ ዕለት ነበር ያሳለፈው።
የቡድኑ ሁለት ቀዳሚ ተመራጭ የመሀል ተከላካዮች ደጉ ደበበ እና አንተነህ ጉግሳ ባልነበሩበት በዚሁ ጨዋታ በረከት ከመልካሙ ቦጋለ ጋር በመሆን በድቻ የመሀል ተከላካይ ስፍራ በመጣመር በጥቅሉ ውጤታማ የሚባልን ጊዜ ማሳለፍ ችለዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎችን መሪ ያደረገችውን ኳስ አንተነህ ተስፋዬ በራሱ መረብ ላይ ሲያስቆጥር በረከት የማጥቃት እንቅስቃሴውን በማስጀመር የተወጣው ሚና ወሳኝ ነበር። ከድቻ የሜዳ አጋማሽ እጅግ ግሩም የሆነ ኳስ ለምንይሉ ወንድሙ ማቀበል የቻለ ሲሆን ምንይሉም ኳሷን በጥቂቱ ከነዳ በኋላ ወደ መሀል ያቀበለው ኳስ በራሳቸው ላይ ለማስቆጠር ተገደዋል።
በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ሰበታ ከተማዎች አቻ መሆን ችለው ነበር። የሰበታው የመሀል ተከላካይ በረከት ሳሙኤል ላስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ መገኘት መንስኤ የነበረው ደግሞ ራሱ በረከት ወልደዮሐንስ ነበር። በረከት በመከላከል እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ኳስ በእጅ በመንካቱ ሰበታ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት ሊያገኙ ችለዋል።
በዚህ ያላበቃው የበረከት ውሎ በሁለተኛው አጋማሽ 64ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን ሁለት አቻ ያደረገችን ግብ ደግሞ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር በእሱ ምክንያት ለተቆጠረችው ግብ ምላሽ ሰጥታታ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጨዋታው በወላይታ ድቻ የበላይነት መጠናቀቁ የተጫዋቹን የጨዋታ ዕለት ውሎ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
👉 ጌታነህ ከበደ እና ቅጣት ምቶች
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሳይጠበቅ ወደ ወልቂጤ ከተማ ያቀነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነው ጌታነህ ከበደ በአዲሱ ክለቡ መልካም የሚባል ጅማሬን እያደረገ ይገኛል።
ከብዙ መለዋወጦች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ተመሳሳይ የአጥቂ መስመር ጥምረትን በተጠቀሙት ወልቂጤ ከተማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉም ጨዋታዎችን መጀመር የቻለው አጥቂው ለቡድኑ በወሳኝ ሰዓት ወሳኝ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል።
አጥቂው በ2009 ከ3 ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ከተመልሰ ወዲህ አንዱ አሻሽሎት የመጣው ጉዳይ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀሙን እንደሆነ እየታዘብን እንገኛለን።
ተጫዋቹ የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብ የመቀየሩ ጉዳይ በራሱ በሂደት በደንብ እየተሻሻለ ይገኛል። በቅርቡ እንኳን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደቡብ አፍሪካን በባህር ዳር ስታዲየም ስንገጥም ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ዘንድሮም በሊጉ ቡድኑ ያስቆጠራቸው ሁለት የቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ያደረጉት የጌታነህን እግር ነበር።
በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ የወልቂጤ ግብ የተገኘችው ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ያሰሻገረውን ኳስ የአዳማው የተከላካይ አማካይ በግንባሩ ገጭቶ በራሱ ግብ ላይ ሲያስቆጥር ነበር። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ቡድኑ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ባስመዘገበበት ጨዋታ የጨዋታውን ውጤት የወሰነችውን ወሳኝ ግብ በቀጥታ ከቆመ ኳስ ማስቆጠር ችሏል።
በሀገራችን እግርኳስ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በቋሚነት የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ረገድ የሚነሱ ተጫዋቾች ብዙም አይስተዋሉም። ነገር ግን ጌታነህ ከበደ በዚህ ረገድ የተሻለው ተጫዋች ሳይሆን እንደማይቀር መናገሩ ስህተት ላይ የሚጥል አይመስልም።
👉 የፍራኦል ጫላ ዕለታዊ ብቃት
ከዕድሜ እርከን ቡድኖቹ ለሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት የማይታማው አዳማ ከተማ ቀጣዩ ኮከብ ፍራኦል ጫላ ይሆን ?
በ2011 የውድድር ዘመን አዳማ ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ በቡድኑ ከ17 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ አንስቶ በአዳማ ከተማ ዋናው ቡድን ውስጥ እየተጫወተ የሚገኘው ፍራኦል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በአዳማ ከተማ ዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አካሂዷል።
በ2011 የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌደሬሽን በተዘጋጀው ከ17 ዓመት በታች ውድድር 28 ግቦችን በማስቆጠር ያለውን የግብ ማስቆጠር አቅም ያሳየው ወጣቱ የመስመር አጥቂ አሁን ደግሞ ዋናው የአዳማ ቡድን ዘንድሮ ላጋጠመው ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር መፍትሄ እንዲሰጥ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ዕምነት ተጥሎበት በመጀመሪያ ተሰላፊነት መጀመር ችሏል።
የመጀመሪያ ጨዋታውን በቋሚነት በጀመረበት የአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ የነበረው እንቅስቃሴ በሊጉ የመጫወት ልምድ ያለው እንጂ ገና ጀማሪ አይመስልም ነበር።
ገና በ3ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አጥብቦ በመግባት ያደረገው ሙከራ የግቡ ቋሚ የተመለሰበት ፍራኦል በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ እንዲሁ መሀል ሜዳ አካባቢ ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂ ሊመክንበት ችሏል።
ከሙከራዎች ባለፈ በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው ፍራኦል ጫላ ገና የእግር ኳስ ህይወት ጅማሮው ላይ እንደመገኘቱ አሁን የጀመረውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል እና ያለውን እምቅ አቅም ይበልጥ አውጥቶ ለማሳየት እግርኳስ እና እግርኳስ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባዋል።
👉 የሁለቱ አምበሎች ፍልሚያ
በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት እና በሁለቱ አጋማሾች የመጨረሻ ሰከንዶች በተቆጠረ ግብ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች አምበሎች ከፍተኛ ፍልሚያ አድርገዋል።
በአዳማ ከተማ በኩል ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ እንዲሁም እያሱ ለገሰ አለመኖሩን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማን እየመራ ወደ ሜዳ የገባው የቀደሞው የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ የነበረው ዳንኤል ተሾመ በየፊናቸው አቅማቸው የፈቀደውን ለቡድኖቻቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
አዳማ ከተማዎች በ90 ደቂቃው የጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻለ የበላይነትን ይዘው በተጫወቱበት ጨዋታ በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም የአዲስአበባ ግብ ጠባቂ የሚቀመስ አልነበረም። ከሰባት በላይ አደገኛ ሙከራዎች የገጠሙት ዳንኤል ተሾመ በአስደናቂ ብቃት ኳሶቹን በማዳን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።
ዳዋ ሆቴሳ በ49ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር መነሻውን አድርጎ አምስት የአዲስአበባ ተጫዋቾችን ቀንሶ ወደ ሳጥን ከደረሰ በኋላ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ዳንኤል በንቃት ማዳን ችሏል። እንዲሁም በ85ኛው እና በ92ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ እና ግራ ካደላ አቋቋም በሳጥኑ ቅርብ ርቀት ከሚገኝ አቋቋም በቀጥታ የተላኩትን የዳዋን ቅጣት ምቶች በግሩም ሁኔታ ማዳን ሲችል በተመሳሳይ የአቡበከር ወንድሙን የግንባር ኳስ እና የኤልያስ ማሞን የግብ አጋጣሚ ያዳነበት መንገድ ተጫዋቹ ስላሳለፈው አስደናቂ የጨዋታ ቀን ምስክር ናቸው።
ፍፁም ጥላሁን በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ እስከመጨረሻው ደቂቃ በዳንኤል ተሾመ አስደናቂ የግብ አጠባበቅ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ቀርበው የነበሩት አዲስአበባ ከተማዎች በ96ኛው ደቂቃ ግን ከዳዋ ሆቴሳ የቅጣት ምት መነሻዋን ያደረገችውን ኳስ አብዲሳ ጀማል በአዲስአበባ ከተማ ተከላካዮች መዘናጋት ታግዞ ግብ ተቆጥሮበት ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።
👉 የስንታየሁ መንግሥቱ ፍፁም ቅጣት ምት
በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻ ሰበታ ከተማን በረታበቶ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ቃልኪዳን ገዛኸኝ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
ፍፁም ቅጣት ምቱን የመምታት ኃላፊነት ተጥሎበት የነበረው የወላይታ ድቻው የፊት አጥቂ ስንታየሁ መንግሥቱ ምቱን ከማምከኑ ባለፈ ኳሷን ወደ ግብ የላከበት መንገድ ብዙም የተለመደ አልነበረም።
ወደ ኳሷ የተንደረደረው ስንታየሁ በተፈጥሮአዊ እግሩ በሆነው የቀኝ እግሩ ይመታል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ኳሷ ከተጠጋ በኋላ ኳሷን ሳይጠበቅ በግራ እግሩ ደንቆል አድርጎ በተቃራኒው በቀኝ እግሩ ኳሷን የሚመታ ለማስመሰል ያደረገው ጥረት አስገራሚ ነበር።
እርግጥ መሰል ያልተለመደ የኳስ ዓመታት ሂደቶች በመጨረሻ ውጤታቸው የሚዳኙ ቢሆንም ጨዋታው 0-0 በነበረበት ሂደት መሰል የዓመታት መንገድን ለመጠቀም መወሰኑ በራሱ የተጫዋቹን ከፍ ያለ የራስ መተማመን የሚያሳይ ነው።
👉 ዳዊት ፍቃዱ ዳግም በሊጉ ግብ አስቆጥሯል
የቀድሞው የአየር ኃይል ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢትን ጨምሮ በተለያዩ የሊጉ ክለቦች በመጫወት ማሳለፍ የቻለው ዳዊት ፍቃዱ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ግብ አስቆጥሯል።
በተለይ በኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት መለያ በትልቅ ደረጃ አስደናቂ የግብ ማግባት አቅሙን ማሳየት የቻለው አጥቂው በተለያዩ ምክንያቶች በፕሪሚየር ሊጉ ሳንመለከተው ብንቆይም በክረምቱ የዝውውር መስኮት በጅማ አባ ጅፋር የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ በሚገባ በመጠቀም የውል ስምምነት በመፈፀም ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለስ የሚያስችለው ዕድል ፈጥሯል።
ከጅማ አባጅፋር ጋር በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ጥሩ የሚባል ጊዜን ያሳለፈው ዳዊት ወደ ሊግ ውድድር ሲመጣ ግን ግብ ማስቆጠር ባይችልም በግሉ ጥሩ የሚባልን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቶ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ሲረታ ቡድኑ ያስቆጠራትን ብቸኛ ግብ ከሳጥን ውጭ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
👉 የሥዩም ተስፋዬ ቁምጣ ?
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሳይጠበቅ የካሳዬ አራጌውን ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተቀዳሚ ተመራጭ የቀኝ መስመር ተከላካይ የነበረው ስዩም ተስፋዬ እንደ ቡድን ቀዝቃዛ የሊግ አጀማመር ባደረገው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በአንዳድ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ እየተመለከትነው እንገኛለን።
በእነዚሁ ጨዋታዎች ላይ ታድያ የመስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ የሚለብሰው የመጫወቻ ቁምጣ ከሌሎች የተለየ ሆኖ አስተውለናል። የስዩም የመጫወቻ ቁምጣን የተመለከተ ከቁምጣነት ይልቅ በተለምዶ ተጫዋቾች ከቁምጣ ስር ለሚለብሱት “ታይት” የቀረበ ይመስላል።
ምናልባት የስዩም ቁምጣ በግል ፍላጎቱ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ወይንስ በምርት ግድፈት የተፈጠረ ነው የሚለው ጉዳይ ምላሽ የሚሻ ቢሆንም ጥብቅብቅ ያለው የተጫዋቹ ቁምጣ ጉዳይ ግን ትኩረት የሚስብ ነበር።
👉 ወንድማማቾቹ …
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ በርከት ባሉ አጋጣሚዎች የአንድ ቤተሰብ አባላትን በተጫዋችነት ተመልክተናል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ ሁለት የቤተሰብ አባላት ወደዚህ ዝርዝር ተቀላቅለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ቡና የሚገኘው እና ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ማሳለፍ የቻለው ሙሉዓለም መስፍን ታናሽ ወንድም የሆነው እንዳልካቸው መስፍን በአሁኑ ሰዓት በአርባምንጭ ከተማ ጥሩ ቆይታን እያደረገ ይገኛል። ታድያ የሙሉዓለም እና የእንዳልካቸው መስፍንን ጉዳይ አስገራሚ የሚያደርገው ሁለቱም “20” ቁጥር መለያን መልበሳቸው እና በተመሳሳይ የተከላካይ አማካይ ስፍራ የሚጫወቱ መሆናቸው ነው።
በተመሳሳይ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወላይታ ድቻን ለቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው በረከት ወልዴ ታናሽ ወንድም የሆነው ውብሸት ወልዴ በወላይታ ድቻ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ማድረግን ችሏል።