ኢትዮጵያዊው ዓለምአቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ የኩዌት የሊግ ጨዋታዎች ለመምራት ወደ ስፍራው ያመራል።
በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የተለያዩ ጨዋታዎችን የመራው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን እየመራ እንደነበር ይታወሳል። በአምስተኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉትን ጨዋታዎች የመራው አልቢትሩም የኩዌት እግርኳስ ማኅበር በፃፈው ደብዳቤ መሰረት የሀገሪቱን የውስጥ ውድድሮች ሊመራ መመረጡ ታውቋል።
በቀረበበት ክስ ከሰሞኑን የመነጋገሪያ ርዕስ የነበረው በዓምላክ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 4 ድረስ የሚደረጉትን የኩዌት ኤስ ቲ ሲ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በዳኝነት እና በቪ ኤ አራ ዳኝነት ለመምራት ዛሬ ማምሻውም ወደ ስፍራው እንደሚያቀና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።