በሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የአመራር ለውጦች አድርጓል።
ያለፉትን ሁለት ዓመታት በውጤት መገራገጭ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ለክለቡ ውድቀት ዋንኛው ምክንያት የአመራር ሰጪው ብቃት ማነስ መሆኑን የክለቡ የበላይ አካል ቅርቡ ባደረገው ግምገማ የተለያዩ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን መወሰኑን ሰምተናል። በዚህም መሠረት ያለፉትን ዓመታት ክለቡን በሥራ አስኪያጅነት ይመሩ የነበሩት አቶ ሱልጣን በተደረገው ግምገማ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ሲደረግ በምትኩ አቶ አብዲሳ ለማን በጊዛዊነት መተካቱ ተገልፇል። በሌላ በኩል የቀድሞ ቡድን መሪ አቶ ጁሀድ ከድር በማንሳት አቶ ሙባረክ ነስሮን መተካቱ ታውቋል። የቡድን መሪነቱ ቦታ ላይ የክለቡ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ናስር አባዲጋ በጊዜያዊነት ሲሰሩ እንደነበር ይታወሳል።
የክለቡ የበላይ አካል እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ አሁን ጅማ አባ ጅፋር የሚገኝበት ሁኔታ ትኩረት የሚያስፈልገው እንደሆነና በርከት ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች በመስራት ክለቡን ወደ ቀድሞው ቁመናው ለመመለስ የሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሲከፈት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማስመጣት ቡድኑን ለማጠናከር መታሰቡን ገልፀውልናል።
አባጅፋሮች ወደ ሊጉ በመጣበት ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት አጀማመራቸውን አሳምረው የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውጤት እየራቀው በሊጉ ላለመውረድ እየታገለ ይገኛል።