ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ሌሎች ጉዳዮች የመጨረሻው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 “አሳፋሪ የመጫወቻ ሜዳ..”

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የመጫወቻ ሜዳ በተለያዩ አካላት የወቀሳ ድምፆች ሲነሱበት ቆይቷል ፤ አሁንም እየተነሱበት ይገኛል።

የተለያዩ አሰልጣኞች በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ወቅት ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ያደመጥን ሲሆን በቅርቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጫወቻ ሜዳውን ሁኔታ በስብርባሪ ጠርሙሶች ላይ እንደመጫወት ነው ሲሉም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን መግለፃቸው አይዘነጋም።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ቡናው የፊት አጥቂ የሆነው አቡበከር ናስር ሜዳውን “የሊጉን ደረጃ የማይመጥን እጅግ አሳፋሪ” ሲል ገልፆታል።

ምንም እንኳን የሀዋሳው ሜዳ ብዙ የተባለበት ቢሆንም በሊጉ በመርሃግብሮች መካከል ካለው የተጣበበ ጊዜ አንፃር ከዚህ በኋላ ላሉት ጨዋታዎች ሁኔታዎች ይስተካከላሉ ተብሎ ባይጠበቅም በቀጣይ ውድድሩን የሚያስተናግዱ ከተሞች ላይ በሚገኙ ስታዲየሞች የመጫወቻ ሜዳዎች ጉዳይ ግን ከወዲሁ አክሲዮን ማህበሩ በትኩረት ሊያጤናቸው ይገባል።

በዚህ ሳምንት የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ አማረ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የሜዳውን ሁኔታ ሲመለከቱ ማስተዋላችን ምናልባትም የለውጥ እርምጃ ለመውሰድ እንደ ጅምር ሊቆጠር ይችላል።

👉 መለስተኛ ጥንቅሮች በጨዋታ ዕለት ስርጭት መጀመራቸው

የሀገራችን እግርኳስ በግዙፉ የክፍያ ቴሌቪዥን ተቋም ዲኤስቲቪ መተላለፍ ከጀመረ ሁለተኛ የውድድር ዘመናችን ላይ እንገኛለን። ተቋሙ የስርጭት ይዘት ለማሻሻል ሆነ የባለሙያዎች የዕውቀት ሽግግር ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ነገሮችን በአዲሱ የውድድር ዘመን እየሞከረ ይገኛል።

የቀድሞ ተጫዋቾችን በተንታኝነት እንዲሰሩ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ አዳዲስ ይዘቶችን በጨዋታ ዕለት የቀጥታ ስርጭቱ ውስጥ ለማካተት ሙከራዎችን እያደረጉ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል አምና በተወሰነ መልኩ ተሞክሮ የነበረውን እና ዘንድሮ ደግሞ በሸገር ደርቢ የቀጥታ ስርጭት ወቅት ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞ በነበረው የቅድመ ጨዋታ ውይይት ወቅት ረዳት አሰልጣኞች በሆኑት ዘሪሁን ሸንገታ እና ገብረኪዳን ነጋሽ ላይ ያተኮረ አጭር የምስል ጥንቅር እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም በመስኡድ መሀመድ ፣ ገብረመድህን ሀይሌ እና ሙሉጌታ ምህረት ላይ ያጠነጠኑ ጥንቅሮች አየር ላይ ውለው ተመልክተናል።

የጨዋታ ዕለት ስርጭቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት መሰል አዳዲስ ይዘቶች መጨመራቸው ለተመልካቾች የሚሰጠው የተለየ ጣዕም መኖሩን ታሳቢ በማድረግ የጀመሩት አበረታች ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

👉 ጭንቀት ውስጥ የነበሩት ሥራ አስኪያጅ

ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት የሊግ ጨዋታዎች በኋላ የመጀመሪያ ድሉን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማሳካት ችሏል። ታድያ በሰሞነኛ የውጤት ማጣት መነሻነት ጫና ውስጥ የሰነበቱት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ቡድናቸው ውስጥ የነበረውን ጫና የሚያሳይ ድርጊትን ሲያሳዩ ተመልክተናል።

በስታዲየሙ ከክለቡ ቦርድ ፕሬዚዳንት ከሆኑት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታምራት ጋር ሆነው ጨዋታውን የተከታተሉት ሥራ አስኪያጁ ሁለተኛውን አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ጨዋታውን ቆመው ሲከታተሉ አስተውለናል።

የቡድን የሜዳ ላይ ውጤት በአጠቃላይ በክለቡ ዙርያ ያሉ አካላትን ስሜት በአውንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የመቀየር ኃይል አለው። የኢትዮጵያ ቡናም ሰሞነኛ ውጤት አልባ ጉዞ በክለቡ ዙርያ የተሰባሰቡ አካላትን በሙሉ ጭንቀት ውስጥ የጨመረ አጋጣሚ ነበር።

አሁን ላይ ግን የመጀመሪያው ድል እንደመመዝገቡ ይህ የጭንቀት ደመና በተወሰነ መልኩ የተገፈፈ ይመስላል።

👉 ክስተቶች የበዙበት የጨዋታ ሳምንት

5ኛ የጨዋታ ሳምንት በአዲሱ የውድድር ዘመን እስካሁን ከተመለከትናቸው የጨዋታ ሳምንታት በተለየ መንገድ በርካታ አነጋጋሪ ክስተቶችን የተመለከትንበት የጨዋታ ሳምንት ነበር።

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ባልተለመደ መልኩ በድምሩ ስድስት የፍፁም ቅጣት ምቶች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አራቱ ወደ ግብነት ሲቀየሩ የአርባምንጭ ከተማው ወርቅይታደስ አበበ እና የወላይታ ድቻው ስንታየሁ መንግስቱ የተቀሩትን ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን አምክነዋል።

ሌላኛው በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸው አደገኛ ጥፋቶች እንዲሁ ብዙ የሚያነጋግሩ ነበሩ በተለይም ሀዋሳ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ የሀዋሳው ፀጋሰው ድማሙ ፀጋዬ አበራ ላይ የሰራው እጅግ አደገኛ ጥፋት እንዲሁም ፋሲል ከነማ ከአርባምንጭ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የፋሲል ከነማው ተጫዋች ሀብታሙ ተከስተ ወርቅይታደስ አበበን በክርን በመማታቱ በቀይ ካርድ የወጡባቸው አጋጣሚዎች አነጋጋሪ ነበሩ።

👉 የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች መነቃቃት

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት ከሆኑ ቡድኖች ተርታ የሚመደቡት ወላይታ ድቻዎች ደጋፊዎቻቸው መነቃቃት ላይ ይገኛሉ ማለት ይቻላል።

በ2006 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊግ በመጡበት ዓመት በሜዳቸውም ሆነ ከሜዳቸው ውጪ በተለይም በአዲስአበባ ስታዲየም በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በቁጥር በርከት ባሉ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ጨዋታቸውን ያደረጉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ባለፉት ዓመታት ግን ከቡድኑ ውጤት መዋዥቅ ጋር በተያያዘ የደጋፊዎቻቸው ቁጥር መቀነሶችን አሳይቶ ነበር።

ነገርግን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑ ጥሩ የሚባል ጅማሮን እያደረገ ይገኛል። በ12 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ቡድናቸውን ለማበረታታት በርከት ያሉ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መምጣት ጀምረዋል።

በተለይም ቡድኑ ሰበታ ከተማን በረታበት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየሙ ጨዋታ በርካታ ቁጥር ያላቸው የክለቡ ደጋፊዎችን ተመልክተናል። በቁጥር በርከት ይበሉ እንጂ በሜዳው የነበሩት የክለቡ ደጋፊዎች ከሌሎች ክለቦች አንፃር የክለቡን መለያዎችን በስፋት ሲጠቀሙ አልተስተዋለም። ይህም ምንልባት ከማልያ እና ሌሎች ተያያዥ አቅርቦት አለመኖር ጋር ሊሆን ስለሚችል የክለቡ ኃላፊዎች እና የደጋፊ ማህበሩ ይበልጥ ትኩረት አድርገው ሊሰሩበት ይገባል።