በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር ለሚገኙ በሁለቱም ፆታ እየተካፈሉ ላሉ ክለቦች የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ጎፈሬ መካከል ለሁለት ቀናት በቤስት ዌስተርን ሆቴል ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በዋናነት ስልጠናው ከስፖርት ማርኬቲንግ እና ስፖንሰርሺፕ ጋር የተያያዘ ሲሆን ስልጠናውን ለሁለት ቀን የሰጡት የድሬደዋ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የማርኬቲንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍፁም ክንደሼ ናቸው። የስልጠናው አሰጣጥ መንገድ በተወሰኑ ገለፃዎች ከተሳታፊዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት እንደሆነ ታዝበናል። በዛሬው የስልጠናው መዝጊያ ፕሮግራም ላይ አቶ ደረጄ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝደንት፣ አቶ ሳሙኤል የጎፈሬ ሥራ አስኪያጅ እና የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ፍቅሩ ተፈራ በክብር እንግድነት ከመገኘታቸው ባሻገር ከመድረኩ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራርያ ሰጥተዋል።
አቶ ደረጄ በንግራቸው የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደነዚህ ያሉ ስልጠናዎችን ማዘጋጀቱ ክለቦች በየትኛውም መለኪያ አቅማቸውን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነና በተለይ በማርኬቱ በኩል በክለቦች ያለውን የአቅም ውስንነት ከፍ ለማድረግ ሌሎች ስራዎች በቀጣይ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ስልጠናው እንዲዘጋጅ ድጋፍ ያደረጉትን አካላት በተለይ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራቹ ጎፈሬን አመስግነዋል።
የጎፈሬ አመሰራረት እና አሁን ያለበትን ደረጃ ለተሳታፊዎቹ ያብራሩቱ የጎፈሬ ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው” አብዛኛው ሰው ጎፈሬ ዘንድሮ ስራ የጀመረ ነው የሚመስለው። ሆኖም ግን ከትንሽ ካፒታል በአነስተኛ መሳርያ ከአምስት ዓመት በፊት የተመሠረተው። በሂደት አቅሙን እያሳደገ ዛሬ ትልቅ ስም እና ጥራት ያላቸውን ስራዎች በመስራት በብዙ ክለቦች ዘንድ ተፈላጊ የሆነ መጥቷል። ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ይህን ስልጠና ያዘጋጀንበት ዋና ምክንያት ክለቦች የራሳቸው ቋሚ የሆነ እነርሱን የሚገልፅ የማንነት መገለጫ ቀለም እንዲሁም ሎጎ ሊኖራቸው ይገባል፤ ጎፈሬም በዚህ ጉዳይ አስፈላጊውን ነገር ለማገዝ ዝግጁ ነን፟’ ብለዋል። አክለውም አቶ ሳሙኤል በማልያ አቅርቦት ላይ አሁን ባለው ሁኔታ ከዘጠኝ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር እየሰሩ እንደሆነ እና በተለይ ተጫዋቾች ማልያቸውን ለሚያደንቃቸው ግለሰቦች፣ ለደጋፊዎች ለህፃናት ፈርመው የሚሰጡበትን እንዲሁም ከተጫዋቾች ጋር ሜዳ ውስጥ ተቀያይረው የሚወጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በለተያዩ አሁጉራት ለረጅም ዓመት ተዟዙሮ በመጫወት የሚታወቀው የቀድሞ ተጫዋች ፍቅሩ ተፈራ ከማርኬት ጋር ከታዳጊዎች አሰለጣጠን አንፃር በተዟዟረባቸው ክለቦች ያለውን ተሞክሮ ለሰልጣኞቹ ልምዱን ያካፈለ ሲሆን በቀጣይ በኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት ላይ ለመስራት እንደሚፈልገ ተናግሮ ያለውን የረጅም ዓመት ልምድ በአዲስ አበባ ቢገኙ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በመገኘት ታዳጊዎቹን የማንቃት ስራ እንደሚሰራ በመድረኩ ላይ ቃል ገብቷል።
በመጨረሻም ስልጠናውን ለተካፈሉ አካላት የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኃላ በቡድን ሆኖ ፎቶ በመነሳት የስልጠናው መዝጊያ ሆኗል።