ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የአምስተኛ ሳምንት ምርጥ 11

ከቀናት በፊት የተቋጨው የዘንድሮው ውድድር አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ተንተርሰን ቀጣዩን ምርጥ የሳምንቱ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ 3-2-3-2

ግብ ጠባቂ

ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ

ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመ ነው። ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የገባው ዳንኤል ከአዳማ ከተማ በኩል ሲሰነዘሩ የነበሩ ሰባት የቆሙ እና የክፍት አጋጣሚ ኳሶችን በጥሩ ቅልጥፍና ሲያመክን ነበር። በዋናነት ደግሞ ዳዋ ሁቴሳ በተለያዩ የጨዋታ ሂደቶች ሲሰነዝራቸው የነበሩ ጥቃቶችን በማክሸፉ ረገድ የተዋጣለት የነበረ ቢሆንም ግቡን ሳያስደፍር የሚወጣበትን ሁነት ባለቀ ሰዓት በተከላካዮች የትኩረት ማነስ አጥቷል።

ተከላካዮች

ዋሀብ አደምስ – ወልቂጤ ከተማ

ጋናዊው የመሐል ተከላካይ ቡድኑ ወልቂጤ ግቡን ሳያስደፍር ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን እንዲያገኝ የነበረው ተሳትፎ ጥሩ ነበር። ሊጉን ለመላመድ እምብዛም ያለተቸገረው ቀልጣፋው ተከላካይ ከዳግም ንጉሴ ጋር የፈጠሩት ጥምረት መልካም ቢሆንም በግሉ የሚያደርጋቸው ጊዜያቸውን የጠበቁ ሸርተቴዎች እንዲሁም የአየር እና የመሬት ላይ ፍልሚያዎች የሚያሸንፍበት መንገድ የግብ ዘቡ ሲልቪያን ግቦሆ ብዙም እንዳይጋለጥ አድርጎታል።

በረከት ወልደዮሐንስ – ወላይታ ድቻ

ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ውስጥ በመገኘት ኳስ እና መረብ እንዲገናኙ (አንድ በራሱ ላይ አንድ ተጋጣሚ ላይ) አድርጎ የነበው በረከት ስህተቱን የማረሚያ ጎል ከማግኘቱ በተጨማሪ ዋና ኃላፊነቱ የነበረውን የመከላከል እንቅስቃሴ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አጣምሮት ከተጫወተው መልካሙ ቦጋለ ጋር ሲከውን ነበር። ቁመታሙ ተከላካይ ከፍጥነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ቢነሱበትም ክፍተቶቹን በጥሩ የቦታ እና የሰዓት አጠባበቅ ለመሸፈን ሲጥር ባሳለፍነው ሳምንት ተስተውሏል።

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

በዚህ ሳምንት የተከላካይ ክፍል ተሰላፊዎችን መምረጥ ቀላል አልነበረም። በግል ብቃት ነጥረው የወጡ ጥቂት በመሆናቸውም ካሉት ውስጥ በንፅፅር የተሻለውን አካተናል። በዚህም መሰረት ጋናዊው የሀዋሳ ከተማ የመሀል ተከላካይ ምርጫችን ሆኗል። በተለመደው ጥንቁቅነት እና እርጋታው ከስህተት ነፃ ሆኖ ከሀዲያ ሆሳዕንን ጋር የነበረው ጨዋታ የጨረሰው ላውረንስ አጣማሪው ፀጋሰው ድማሙ በቀይ ካርድ ከመውጣቱ በፊት እና በኋላ ኃላፊነቱን በሚገባ ሲወጣ ተስተውሏል።

አማካዮች

ሀብታሙ ንጉሴ – ወላይታ ድቻ

ባሳለፍነው ሳምንት ድንቅ ጨዋታ ካሳለፉ ቡድኖች መካከል አንዱ ከሆነው ወላይታ ድቻ ሌላም ተጫዋች በምርጥ ቡድናችን ተካቷል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት አሠልጣኙን ተከትሎ ድቻ የደረሰው ሀብታሙ አምስቱንም የሊጉን ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት ጀምሯል። በተለይ ቡድኑ ሰበታ ላይ ባገኘው ድል ደግሞ የነበረው ብቃት ልዩ ነበር። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑን መሐል ላይ በመሆን ከመዘወሩ ባለፈ አንድ ግብ የሆነ ኳስ በማመቻቸቱ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲገባ ሆኗል።

በኃይሉ ተሻገር – ወልቂጤ ከተማ

ከሀብታሙ አጠገብ በተከላካይ አማካይ ቦታ ያስቀመጥነው ተጫዋች ደግሞ የወልቂጤ ከተማው በኃይሉ ተሻገር ነው። የአሠልጣኝ ጻውሎስ ቀዳሚ ተመራጭ የሆነው አማካይ ምንም እንኳን በተከላካይ አማካይ ቦታ ቢደረግም ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን (Late Runner) በማድረግ በተደጋጋሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ እየተገኘ በተጋጣሚ የመከላከል ሲሶ ላይ ቡድኑ የቁጥር ብልጫ እንዲያገኝ ሲያደርግ ይታያል። በድሬዳዋውም ጨዋታ ይህ በተወሰነ የነበረ ሲሆን በዋናነት ግን ቡድኑ መሐል ለመሐል ጥቃቶች እንዳይደርሱበት ሲታትር ነበር።

ቃልኪዳን ዘላለም – ወላይታ ድቻ

በመረጥነው አሰላለፍ ከመስመር አጥቂነት ሚናው ወደ ተመላላሽነት ያመጣነው ቃልኪዳን ወጥ ብቃት በማሳየት ላይ ይገኛል። በቡድኑ የመከላከል ሽግግር ውስጥ በትጋት የሚሳተፈው ቃልኪዳን ፊት ላይም መልሶ ማጥቃት ምርጫው የሆነው ወላይታ ድቻ አስፈሪ እንዲሆን አስችሏል። በሰበታው ጨዋታ ቡድኑ በሰነዘራቸው ጥቃቶች ላይ ሰፊ ሚና የነበረው ቃልኪዳን ድቻ አቻ የሆነባትን ግብም በማስቆጠር የሳምንቱን ብቃቱን ይበልጥ አሳድጎ ታይቷል።

ቢኒያም በላይ – መከላከያ

ቢኒያም ከጉዳት ነፃ ሆኖ ሜዳ ላይ የመሰለፉ አስፈላጊነት ለመከላከያ ምን ያህል እንደሆነ ያሳየበትን የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል። ከቀጥተኛ ኳሶች ባለፈ መከላከያ በቅብብሎች አደጋ እንዲጥል በመርዳት ቁልፍ የማጥቃት መሳሪያ ሆኖ የተመለከትነው ተጫዋቹ ባህርዳርን እንዲያሸንፉ ያደረጉትን ሁለት ግቦች ከመረብ አገናኝቷል። በተለይም 85ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ በድንቅ አጨራረስ ያስቆጠራት ግብ ተጫዋቹ ያለውን ተሰጥኦ እና በራስ መተማመን ደረጃ ያሳየች ነበረች።

ብሩክ መሉጌታ – ሲዳማ ቡና

በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው የሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሲዳማዎች በሙሉ ልብ አጥቅተው የተጫወቱ አይመስልም። ብሩክም ከተለመደው በተለየ ከኳስ ውጪ ባለ የመከላከል ኃላፊነት ላይ አብዛኛውን ደቂቃ አሳልፋል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተመላላሽነት ሚና ላይ ተጠቅመነዋል። ያም ቢሆን ተጫዋቹ የሲዳማ ቡና ብቸኛው አስፈሪ የማጥቃት መሳሪያ ነበር ማለት ይቻላል። ብቸኛዋን የይገዙ ቦጋለን ግብ በግሩም ሁኔታ ሲያመቻች በጨዋታው መገባደጃ ላይ ጨራሽ ያላገኙ ሁለት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችንም ፈጥሮ ነበር።

አጥቂዎች

ምንይሉ ወንድሙ – ወላይታ ድቻ

በመከላከያ ቤት የብቃቱ ከፍታ ላይ ሆኖ የምናስታውሰው ምንይሉ ዳግም የተመለሰ ይመስላል። በተለይ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሰበታን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሲረታ ምንይሉ ከግብ አግቢነት የዘለለ ሚና ኖርት ታይቷል። በጨዋታው አንድ ግብ አስቆጥሮ አንተነህ ተስፋዬ በራሱ ላይ ላስቆጠረው ግብ መነሻ መሆን ችሏል። ከዛም በላይ ግን በማጥቃት ወረዳው ላይ የሚያገኛቸውን ኳሶች የተሻለ አቋቋም ላይ ላለ የቡድን ጓደኛው ለማመቻቸት ይጥር የነበረበት መንገድ የቡድን ተጫዋች ስለመሆኑ ምስክር የሚሆን ነበር።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

የሊጉ የምን ጊዜውም ኮከብ ግብ አግቢ ባለክብር የሆነው አቡበከር ናስር የጎል ድርቁን ያከተመባቸውን ሁለት ግቦች ከመረብ በማገናኘት በድኑን ለመጀመሪያ የሊግ ድል አብቅቷል። ከግቦቹ ባሻገር ሦስት ተከላካዮችን በተጠቀመው ተጋጣሚው ግብ ክልል ላይ ምርጫው በሆነው የመሀል አጥቂነት ሚና ተሰልፎ ወደ ወትሮው አስቸጋሪነቱ ተመልሶ አይተነዋል። በቦታ አያያዝ ፣ በቡድን ጨዋታ ፣ አምልጦ በመግባት እና በአጨራስ ብቃት አቡበከር የወትሮውን አቡበከር ሆኖ ያየንበት ሳምንት ሆኗል።

አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

የብዙዎችን ግምት ፉርሽ ባደረገ ሁኔታ ወላይታ ድቻ በሊጉ ድንቅ አጀማመር በማድረግ የደረጃ ሠንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጧል። ታጋይነት፣ አልሸነፍ ባይነት፣ ቡድናዊ መናበብ በተሞላበት አጨዋወት ተጫዋቾቹ እንዲጫወቱ ያደረጉት ደግሞ የቡድኑ አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ናቸው። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሰባት ጎል ተጋጣሚ ላይ ያገባው ቡድኑ በሰበታው ጨዋታ ቀዳሚ የሚሆንበትን የፍፁም ቅጣት ምት ስቶ እንዲሁም ተመርቶ ሳይረበሽ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንዲጫወት ያደረጉበት እንዲሁም የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ደግመው ያገኙበት መንገድ የሳምንቱ ምርጥ አሠልጣኝ ቦታን ያለ ከልካይ እንዲያገኙት አስችሏል።

ተጠባባቂዎች

መሀመድ ሙንታሪ – ሀዋሳ ከተማ
መልካሙ ቦጋለ – ወላይታ ድቻ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – ኢትዮጵያ ቡና
ሙሉዓለም መስፍን – ሲዳማ ቡና
ሰመረ ሀፍተይ – መከላከያ
በላይ ገዛኸኝ – አርባምንጭ ከተማ
ዳዋ ሆቴሳ – አዳማ ከተማ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ