ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የዲሲፕሊን ውሳኔ እንዲሰጠው ጠየቀ

ከሰሞኑን መነጋገርያ ርዕስ በሆነው ጉዳይ ዙርያ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።

በአምስተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ አስቀድሞ የሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ በተመደቡት ዳኛ ባምላክ ተሰማን ጨዋታውን እንዳይመሩ በማለት ሁለት ምክንያቶችን በማቅረብ ክስ አዘል ደብዳቤ ለአወዳዳሪው አካል ማቅረባቸው ይታወሳል። እንደ ምክንያት ካቀረቡት ሁለት ነገሮች መካከል አንደኛው ”ዳኛው በግሉ የተጋጣሚያችን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ እንደመሆኑ መጠን ጨዋታውን እንዳይመሩ እንጠይቃለን” የሚለው ነበር። ይህ ምክንያት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማን ያስቆጣው መሆኑ ሲታወቅ ይህን ጉዳይ በመከታተል አስፈላጊውን የህግ እርምጃ እንዲወሰድ በማሰብ ባምላክ ተሰማ በህጋዊ ወኪል እና የሕግ አማካሪ በሆኑት አቶ ብርሃኑ በጋሻው አማካኝነት ”ሀሰተኛ የስም ማጥፋት በደል የደረሰብኝ በመሆኑ የፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት ያቀረብነውን ቅሬታ በመመርመር በአጭር ጊዜ ውስጥ ክለቡ ላይ እርምጃ ወስዶ እንዲያሳውቀን” በማለት ባለ ሁለት ገፅ ደበዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብተዋል።

ጉዳዩን ተመልክቶ በቅርቡ ፌዴሬሽኑ ምላሽ እንደሚሰጥ ሲጠበቅ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ በኩዌት ሊግ ውድድሮችን ለመምራት ትናንት ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል።

ያጋሩ