ሪፖርት | አዲስ አበባ ወደ አናት ማጓዙን ቀጥሏል

በምሽቱ ጨዋታ ከተከታታይ ድሎቹ ተደናቅፎ የነበረው አዲስ አበባ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 መርታት ችሏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ ከተጋራበት ስብስብ ውስጥ አበባየሁ ዮሐንስ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ደስታ ዋሚሾን በመላኩ ወልዴ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ሀብታሙ ታደሰ በመተካት ጨዋታውን ሲጀምር አዲስ አበባዎች ግን ከአዳማ ከተማው ጨዋታ የአሰላለፍ ለውጥ አላደረጉም።

በፈጣን ጥቃቶች የጀመረው ጨዋታው ከጅምሩ በዓይን ሳቢ ሁነቶች ተሞልቷል። አዲስ አበባዎች በግራ በከፈቱት ጥቃት በእንዳለ ከበደ አማካይነት ኳስ እና መረብን ቢያገናኙም ከጨዋታ ውጪ ሲሆንባቸው ሀዲያዎች በመልስ ጨዋታው በተስፋዬ አለባቸው የሳጥን ውጪ ድንቅ ሙከራ አድርገው ዳንኤል ተሾመ አድኖባቸዋል። ከአፍታ በኋላ ሀዲያዎች በቅብብሎች ሳጥን ውስጥ ሲደርሱ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ጥፋት በመስራቱ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ጥፋት የተሰራበት ዑመድ ዑኩሪ ራሱ መትቶ ዳንኤል ሊያመክነው ችላል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጨዋታው ስድስተኛ ደቂቃ ላይ ነበር።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ከባባድ ሙከራዎች በብዛት አይታዩ እንጂ የጨዋታው ግለት እንደቀጠለ ነበር። በሦስት ተከላካዮች የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የመስመር ተመላላሾቻቸውን በተለይም በግራ በኢያሱ ታምሩ በኩል አጋድለው በመጠቀም አደገኛ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ ሲያደርሱ ታይተዋል። አዲስ አበባ ከተማዎችም እንዲሁ በግራ መስመር አጥቂያቸው ፍፁም ጥላሁን አቅጣጫ ያዘነበሉ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ይስተዋል ነበር።

ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ የተቃራኒን ጠንካራ ጎን መለየት የቻሉ የሚመስሉት ሁለቱ ተጋጣሚዎች በመከላከሉ ረገድ ጠንከር ብለው ታይተዋል። ይህ መሆኑ የማጥቃት ምልልሱ እንዳለ ቢሆንም ከባባድ ሙከራዎች እንዳይታዩ ሆኗል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ግን አዲስ አበባዎች ጫን ብለዋል 40ኛው ደቂቃ ላይ በኤልያስ አህመድ ከሳጥን ውጪ ከባድ ሙከራ ያደረጉት አዲስ አበባዎች ከሁለት የቆሙ ኳሶችም ግብ ለማግኘት ታቃርበው ነበር። በፍፁም ጥላሁን በቀጥታ የተመታው እንዲሁም በዲሜጥሮስ ተሻምቶ በእንዳለ ከበደ የተገጨው የቅጣት ምት ኳስ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ ተቃርበው የተቃረቡ የመጨረሻ ደቂቃ ዕድሎች ነበሩ። ፍፁም ጥላሁን ሆሳዕና ሳጥን ውስጥ ከፍሬዘር ካሳ የቀማውን ኳስ ከቅርብ ርቀት የሞከረበትም ሂደት ለቡድኑ ብልጫ ሌላ ማሳያ ነበር።

ከዕረፍት መልስ በሀብታሙ ታደሰ የርቀት የከረረ ሙከራ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ሀዲያ ሆስዕናዎች በሙሉ ኃይላቸው ሲያጠቁ ታይተዋል። አዲስ አበባዎች በሙሉቀን ታሪኩ 54ኛው ደቂቃ ላይ የርቀት ሙከራ ቢያደርጉም የሆሳዕና ፈጣን ጥቃቶች አደጋ የጣሉባቸው አጋጣሚዎች ከባድ ነበሩ። 56ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር ተማላላሾቻቸው ጥምረት ሲሞክሩ ብርሀኑ በቀለ አሻምቶ እያሱ ታምሩ በግንባሩ ሞክሮ ስቷል። የቡድኑ ጥቃት ለግብ የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ዘግየት ብለው ሲመጡ 65ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሳጥን ውስጥ ደርሰው ዑመድ ከሀብታሙ ታደሰ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ በሚያስቆጭ መልኩ ሲስት ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ ከአየር ያወረደውን እና ከሀብታሙ ጋር የተቀባበለውን ኳስ ከተመሳሳይ ቦታ ላይ አምክኗል።

 

በተፈጠረባቸው ጫና ማጥቃታቸው ረግቦ የነበሩት አዲስ አበባዎች ግን ወደ ግብ የሄዱበት ቀጣዩ ጥቃት ግብ ሆኗል። ከእጅ ውርወራ የተነሳውን እና ቻርለስ ሪባኑ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ተነጥሎ በመውጣት ግብ አድርጎታል። ሆሳዕናዎች ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ሳጥን ውስጥ ቢገኙም የዑመድ ሙከራ አሁንም ሊሰምር አልቻለም።

ከግቡ በኋላ ሆሳዕናዎች ኳሶችን ወደ ሳጥን በመጣል አቻ ለመሆን ሲጥሩ አዲስ አበባዎችም ጨርሰው ከማፈግፈግ ይልቅ ገፍተው ለመውጣት ሲሞክሩ ይታይ ነበር። ሆኖም በመጨረሻ ከፍተኛ የሀዲያ ሆሳዕናዎች ጫና የታየበት ጨዋታው በፍልሚያው ቀጠለ እንጂ ሌላ ግብ ሳይስተናግ በአዲስ አበባዎች የ1-0አሸናፊ ሆነዋል።

 

በውጤቱም ሀዲያ ሆሳዕና 15ኛ ደረጃ ላይ ሲቀር አዲስ አበባዎች ከስምንት ወደ ሦስት ከፍ ብለዋል።