አዲስ አበባ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን ድል ካደረገበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።
አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
ጨዋታው እንዳቀዱት ስለመሄዱ
እውነት ነው ጨዋታው እንዳቀድነው እየሄደ ነው። ምክንያቱም እኔ ከተረከብኩ በኃላ የራስችንን እቅድ ሰርተን ነበር። ከማን ላይ ነጥብ ማግኘት አለብን የትኛው ብንሸነፍ ብለን ሰርተን ነበር። በዛ መሰረት ዛሬ ተሳክቶልን ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለናል።
ስለ ሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ
መሀል ሜዳ ላይ ሙሉቀን እና ኤልያስ አካባቢ ከዚህ በፊት ከነበረው እንቅስቃሴ ትንሽ መፍዘዝ ነበር። ስለዚህ ሁለቱን ተጫዋቾች መቀየር ደግሞ በመጠኑ ቡድኑን እንዲያነቃቃው ረድቶታል። አንደኛ በጉልበታቸው አዲስ ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ ጥሩ ይጫወታሉ፤ ልምድም ያላቸው በመሆናቸው በደንብ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ይወጣሉ ብዬ ስላመንኩ ያንን ተጠቅመናል። ጥሩም ነበር።
የግብጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ብቃት
እውነት ነው አንድ ግብጠባቂ ጠንካራ ሲሆን ለቡድኑ ትልቅ አስተዋፆኦ ያደርጋል። ምክንያቱም የግብ ጠባቂ ጥንካሬ ተጫዋቾቹን በደንብ ያነሳሳል። ለተሻለ ውጤት የሚገፋፋ ስለሆነ ዳንኤል ገና ከዚህ በላይ ጥሩ ይሆናል ብዬ አምናለው።
ግብጠባቂው ዳንኤል አንበል ስለመሆኑ
በእሱ እምነት አለኝ። በእርሱ በእርግጥ ሌሎችም አንበሎች አሉ። እርሱ ሦስተኛ አንበል ነው። እነዛ ሜዳ ላይ ስላልተሰለፉ እንጂ ሌሎች አንበሎች አሉ። በእርግጥም አቅም አለው። በዛ ላይ አዕምሮውም ጥሩ ስለሆነ በደንብ ይወጣል ቡድኑንም ይመራል።
ወደ መሪዎቹ እየተጠጉ ስለመሆኑ
እንግዲህ ወደፊት ሜዳው ነው የሚወስነው። በእርግጥ አንድ ቡድን የራሱ እቅድ ይኖረዋል። እቅዳችን መሠረት እየተጓዝን ነው። የወደፊቱን ወደ ፊት እናየዋለን። ውጤታችን ወደዛ ይመራናል። እቅዳችን እንደተጠበቀ ነው። ግን ውጤታችን ወደ ዋንጫ ከመራን የማንፎካከርበት ምክንያት አይኖርም።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና
ይዘውትው የገቡት እቅድ ምን ያህል ተሳክቷል
በእርግጥ ያሰብነውን ለማሳካት አሁንም የተሻሉ የጎል እድሎችን ፈጥረናል። አጨራረስ ላይ ካልሆነ በቀር ሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ ጎል ላይ በመድረስ የነበረን ጥረት እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ፍፁም ቅጣት ምት አልተጠቀምንም። አሁንም አጨራረሱ ነው እንጂ የቀረን የተሻልን ነን።
የፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት ቡድኑን ስለማቀዝቀዙ
አይ ምንም! የመጀመርያው ደቂቃዎች ስለሆነ ምንም ያወርደዋል የሚል ነገር የለኝም። ከዛም በኃላ የተሻሉ የጎል ዕድሎችን ፈጥረናል። አሁንም የመጨረስ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። አሁንም የመጨረሻው ክፍል ላይ ደግመን መስራት ያለብን ለቀጣይ ጨዋታዎች ደግሞ ተዘጋጅተን እንመጣለን። የሚያሰጋን ነገር የለም እንመጣለን።
የተደረጉ የተጫዋቾች ቅያሪዎች በቡድኑ ውስጥ ስለ ፈጠሩት ለውጥ
አጋጣሚ ሆኖ ስትቀይራቸው ለውጥ ሊኖር ላይኖርም ይችላል። ግን ባለቀ ሰዓት ሁለት ሰው ቀይረናል፤ ይሳካልም አይሳካምም። እንቅስቃሴው ግን በዛው የቀጠለ እንጂ ለውጡ ወደ ፊት የተሻለ ነገር ያመጣል።
ስለ መስመር ተጫዋቾች ሚና
ሲጀምር አጨዋወታችን ሦስት አምስት ሁለት ነበር። የግራ እና የቀኝ የመስመር ተጫዋቾች እንደ መስመር አጥቂ ሳይሆን ሁለት አጥቂዎች ነው ያሉን ከጎል ጋር የነበራቸው ቅርበት ጥሩ ነበር። የአጨራረስ ጉዳይ እንጂ አጥቂዎቻችን ወደ ጎል ደርሰዋል። ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች አግኝተዋል። መጨረሻ አካባቢ አራት ሦስት ሦስት መጥተናል በሂደት ወደ ውጤት ይመጣል የሚል ግምት አለኝ።