የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ቦትስዋናን አሸንፏል

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ሦስተኛ የማጣርያ ዙር ቦትስዋናን የገጠመው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 3-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን አመቻችቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው የአሰልጣኝ ፍሬው ተጫዋቾች በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል አመዛኙን ጊዜ በማሳለፍ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። ጨዋታው በተጀመረ በሰባተኛው ደቂቃ ላይም ረድኤት አስረሳሠኝ አንድ ተጨዋች ቀንሳ ከሳጥኑ አቅራቢያ በቀጥታ መትታ ግብ ጠባቂዋ ባዳነችባት ኳስ ወደ ጎል መቅረብ የጀመሩ ሲሆን በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ረድኤት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሳትጠቅምበት ቀርታለች። በተለይ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ከገነት ኃይሌ አግኝታ ያልተቀመችበት እና ከግራ መስመር ቱሪስት ለማ ወደ ውስጥ ገብታ አመቻችታላት መቆጣጠር ሳትችል ያባከነቻቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

የሜዳውን የግራ መስመር ለማጥቃት ምርጫቸው ያደረጉት ታዳጊዎቹ ሉሲዎች በ36ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አርያት ኦዶንግ የቦትስዋና የኋላ ክፍል አለመናብብ ተጠቅማ ኳስ በመቀማት በቀጥታ የመታቹ ኳስ ለኢትዮጽያ የመጀመሪያ ግብ ሆናለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ እጅጉን የተጫኑት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በ43ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አክለዋል። ረድኤት ከሳጥን ውጪ በተጫዋቾች መሐል ያገኘችውን ኳስ ይዛ በመግባት ወደ ግብ ስትመታ በቦትስዋና ተከላካይ ተጨርፎ ወደ ግብነት በመለወጥ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ባለ ሜዳዎቹ ቦትስዋናዎች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃ የቦትስዋና ብልጫ የታየበት እንዲሁም የኢትዮጽያን ተጨዋቾች ደግሞ መከላከሉ ላይ የተሻሉበት ሲሆን ዜብራዎቹ በ57ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረው ልዩነቱን በማጥበብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል።

ከጎሉ በኋላ ቀስ በቀስ የበላይነታቸውን ያስመለሱት የኢትየጵያ ተጫዋቾች በመልሶ ማጥቃት መልካም አጋጣሚ ፈጥረው አርያት ኦዶንጓ ከግራ መስመር ላይ የመታችው ኳስ የግቡን አግዳሚ መልሶባታል። ባለሜዳዎቹ በአንፃሩ ከቆመ እና ከርቀት የሚሞክሩት የግብ ላይ ጥቃት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ይበልጥ ብልጫ ያሳዩት ሉሲዎቹ ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች ጥቃት በመሰዘር ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ81ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አስተማማኝ ማድረግ ችለዋል። የፈጠሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ በቦትስዋና ተከላካዮች ሲመለስ በግራ በኩል ከሳጥኑ አቅራቢያ የነበረችው መሳይ ተመስገን በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይራዋለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በኢትዮጵያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የመልሱ ጨዋታ ከ15 ቀናት በኋላ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወን ሲሆን በወቅታዊ አስደናቂ አቋም ላይ የሚገኘው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድኑ በድምር ውጤት አሸናፊ ከሆነ ወደ አራተኛው ዙር የሚሸጋገር ይሆናል።