የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለማግኘት የሚደረገውን የነገውን ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ አንድ ለምንም ከተረታ በኋላ ቀጣዮቹ አራት ጨዋታዎች ላይ ጠንክሮ በመቅረብ 12 ነጥቦችን የሰበሰበው ወላይታ ድቻ ያገኘውን የአሸናፊነት ጉዞ ለማስቀጠል እና የሊጉ መሪ ሆኖ ለመዝለቅ ነገ የሚጠብቀውን ከባድ ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል።
በቅድመ ውድድር ፍልሚያዎች ላይ ራሱን በሚገባ ሳይፈትሽ ሊጉን የጀመረው ወላይታ ድቻ ብዙዎች ትንሽ ቦታ ቢሰጡትም ከጨዋታ ጨዋታ ጠንካራ ብቃት እያሳየ ይገኛል። በአራቱ ጨዋታዎች ድል ከማግኘቱ በተጨማሪ ደግሞ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ በድምሩ ሰባት ግቦችን ተጋጣሚ ቡድን ላይ ማስቆጠሩ ወቅታዊ ብቃቱ ከፍተኛ እንደሆነ ይነግረናል። ከምንም በላይ ግን በቡድኑ ተጫዋቾች ላይ የሚታየው አልሸነፍ ባይነት እና ታጋይነት በጨዋታዎች የጎላ የሀይል ሚዛን ብልጫ እንዲኖረው ያደረገ ይመስላል።
በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ ካለው ታታሪነት በተጨማሪ ደግሞ በአጥቂ መስመር ላይ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ፍጥነት በነገው ጨዋታም ለፋሲሎች አደጋ አምጪ እንደሚሆን ይታመናል። በቀጥተኛም ሆነ በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት (በትንሹ) የግብ ዕድሎችም የሚፈጥሩ ተጫዋቾች ስብስቡ ውስጥ መኖሩ ደግሞ እንዳይገመት አድርጎታል። ከዚህ ውጪ ግን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ በርከት ያሉ ግቦችን ቢያስቆጥርም በተቃራኒው የኋላ መስመሩ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አፍሳሽ ሆኗል። ይህ ነገ ካልተስተካከለ ደግሞ በስሎቹ የፋሲል ተጫዋቾች ሊቀጣ ይችላል።
ሊጉን በጥሩ ሁኔታ ከጀመረ በኋላ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች መጠነኛ መደነቃቀፍ ያጋጠመው የሚመስለው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ካጋጠመው ወቅታዊ አሉታዊ ውጤት በመውጣት ዳግም የሊጉን መሪነት ለማግኘት የነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ክለብ ፋሲል ከነማ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት ዓምና ካቆመበት የቀጠለ አስመስሎት ነበር። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን በሊጉ አዲሶቹ ክለቦች (አዲስ አበባ እና አርባምንጭ) ተፈትኖ አምስት ነጥቦችን ጥሏል። ይህ ቢሆንም ግን አሁንም ክለቡን የዋንጫ ተፎካካሪ ከመሆን ያገደው አይደለም። ለዋንጫ የሚፎካከሩ ክለቦች ደግሞ ከሽንፈት እና ከአቻ ውጤቶች በኋላ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ይታሰባል። ለዚህ ደግሞ ፋሲል ከበላዩ የተቀመጠውም ክለብ ማግኘቱ ምላሹን አዎንታዊ በማድረግ ጣፋጭ ውጤት እንዲያገኝ የሚያረገው ይመስላል። በዚህም ፋሲል በነገው ጨዋታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኮስተር ብሎ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይገመታል።
ፋሲል ወሳኝ ተጫዋቾችን በቅጣት የማጣቱ ጉዳይ በክለቡ በኩል ያለ መጥፎው ዜና ነው። በተለይ ቀዳሚ ተመራጮቹ ያሬድ ባየህ እና ሀብታሙ ተከስተ በአርባምንጩ ጨዋታ በጥፋት ምክንያት ከሜዳ በመወገዳቸው ነገ መጠነኛ ክፍተት በቡድኑ ላይ እንደሚያስከትል ይገመታል። ይህ ቢሆንም ግን በስብስብ ጥራት እና ጥልቀት የማይታማው ቡድኑ ሁለተኛ አማራጮቹን በመጠቀም ጨዋታውን ለማድረግ ይገደዳል። የሆነው ሆኖ በጨዋታው ሊኖረው እንደሚችል ከሚገመተው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መነሻነት የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሱ እንደሚያደርግ ቢታሰብም የዲቻን የመልሶ ማጥቃት እና የረጃጅም ኳሶች ጥቃት መመከቻ መፍትሔ ወደ ሜዳ ይዞ ካልገባ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
ወላይታ ድቻ በነገውም ጨዋታ ሁለቱን የግብ ዘቦች ወንድወሰን አሸናፊ እና ቢኒያም ገነቱ በጉዳት ምክንያት የማያገኝ ሲሆን አምበሉ ደጉ ደበበ ግን ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ መስራት መጀመሩ ተሰምቷል። ፋሲል ከነማ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አምበሉ ያሬድ ባየህ እና ሀብታሙ ተከስተን የሚያጣ ይሆናል። የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው መጠነኛ ልምምድ መጀመሩም ተመላክቷል።
የሳምንቱ ትልቁ ጨዋታ የሆነውን ፍልሚያ ፌዴራል ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ለ8 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማም 5 ጊዜ ድል በማግኘት ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ ደግሞ 3 ጊዜ አሸንፏል። አቻ በማያቀው ግንኙነታቸው ላይ በአጠቃላይ 20 ጎሎች ሲቆጠሩ ዐፄዎቹ 11 የጦና ንቦቹ ደግሞ 9 አስመዝግበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ፅዮን መርዕድ
ያሬድ ዳዊት – በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ
እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ
ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቃልኪዳን ዘላለም
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኬ
አብዱልከሪም መሐመድ – ከድር ኩሊባሊ – አስቻለው ታመነ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ