ወልቂጤ ከተማ በፋይናንስ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋል

👉🏼 ዘጠኝ የቡድኑ ተጫዋቾች ልምምድ ያቆሙ ሲሆን ዛሬ እንደማይጫወቱ አቋማቸውን አስቀምጠዋል።

👉🏼 ችግሩ ቶሎ ካልተፈታ ለክለቡ ህልውና ያሰጋል. . .

ወልቂጤ ከተማ እንደክለብ ለመንቀሳቀስ ፈተና የሆነበት የፋይናንስ ችግር ላይ መውደቁ ተሰምቷል።

እንደሚታወቀው አመዛኙ የፕሪምየት ሊጉ ክለቦች በራሳቸው ለመቆም የሚያስችል የፋይናንስ ሥርዓት እና የገቢ ምንጭ የላቸውም። ይህ መሆኑ ህልውናቸው ከከተማ አስተዳደሮች የሚመደበው በጀት ላይ ብቻ እንዲሆን ሲያስገድድ በጀት በሚስተጓጎልባቸው ጊዜያት እንደ ተቋም የመቀጠል ዕጣ ፈንታቸው ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ይታያል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ይህ ጉዳይ እንደወትሮው በየክለቡ በጭምጭምታ ደረጃ ሲሰማ የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ አደጋ ላይ መውደቁ ታውቋል።

የዘንድሮው ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ የከተማ እና የዞን ምክር ቤቶች ጉባዔያቸውን ባለማድረጋቸው ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ወጪ በቦርዱ በኩል በግለሰቦች ድጋፍ እና በዱቤ ሲሸፍን ቆይቷል። በቀጣይ ጊዜያት በየደረጃው ያሉ ጉባዔዎች ተካሂደው በጀት ቢፀድቅም ባለመለቀቁ ምክንያት ከነችግሩ ወደ ውድድር የገባው ወልቂጤ ከተማ ስራውን ለማስቀጠል ፈተና ውስጥ እንደገባ የክለቡ አመራሮች ይናገራሉ።

ከክለቡ አጠቃላይ ወጪ ሌላ በከተማ ደረጃ በተለቀቀ የሁለት ወር ደመወዝ ብቻ እንቅስቃሴውን የቀጠለው ወልቂጤ አሁን ላይ እንደተቋም የመንቀሳቀስ ህልውናው እየተፈተነ ይገኛል። ከተጫዋቾች ደመወዝ ጋር በተያያዘም ዘጠኝ የሚደርሱ ተጫዋቾቹ ልምምድ ካቆሙ አራተኛ ቀን ያስቆጠሩ ሲሆን ዛሬ ምሽት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ እንደማይሳተፉ አቋማቸውን አስቀምጠዋል።

ከክለቡ አስተዳደር እና የቦርድ አመራሮች ባገኘነው መረጃም ለተጫዋቾቹ ‘ጥያቄያችሁን ሥራችሁን እየሰራችሁ አቅርቡ’ የሙል እንድምታ ያለው ደብዳቤ መስጠታቸውን ገልፀዋል። በለፉት ቀናት ከከተማ እና ዞን አመራሮች ጋር በደረገ ንግግር የበጀቱን ጉዳይ ለመፍታት ቃል ተገብቶላቸው የነበረ ቢሆንም እስካሁን በተግባር መዋል ባለመቻሉ ከተጨዋቾች ደመወዝ እና ጥቅማጥም ባለፈ እስካሁን በዱቤ እና በግለሰቦች ድጋፍ እየተደረገለት የነበረውን አጠቃላይ የክለቡ እንቅስቃሴ ከባድ አደጋ እንደተጋረጠበት አመራሮቹ ነግረውናል።