ሪፖርት | የመሪዎቹ ፍልሚያ ያለግብ ተጠናቋል

ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማን ያገናኘው የዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተፈፅሟል።

ወላይታ ድቻ በሰበታ ከተማ ላይ ባሳካው ድል የተጠቀመበትን የተጨዋቾች ምርጫ ሳይቀይር ወደ ሜዳ ገብቷል። ፋሲል ከነማም ቅጣት ላይ የሚገኙት ያሬድ ባየህ እና ሀንታሙ ተከስተን በአስቻለው ታመነ እና ኦኪኪ አፎላቢ ከመተካቱ በቀር ሌላ የተጫዋች ለውጥ አላደረግም።

እንደትናንቱ ሁሉ ለመከላከያ ሰራዊት በተደረገ የማራል ድጋፍ የጀመረው ጨዋታ በጥሩ ግለት የተከፈተ ነበር። ፋሲል ከነማዎች ኳስ ይዘው ክፍተቶችን በመፈለግ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ሲቆዩ አልፎ አልፎም ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ለመላክ ይጥሩ ነበር። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ከኳስ ጀርባ መሆንን ምርጫቸው አድርገው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መጠባበቅን መርጠዋል። ሆኖም ድቻዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በአናጋው ባደግ እና ቃልኪዳን ዘላለም ጥምረት ሳጥን ውስጥ የደረሱበት እና ወደ ማዕዘን ምትነት በተቀየረው አጋጣሚ ነበር የመጀመሪያ መልሶ የማጥቃት ቅፅበት ያገኙት።

ወደ መሀል ጠበብ ያለው የፋሲል ከነማ ጥቃት ተጋጣሚውን ማስከፈት ከብዶት ታይቷል። ድቻዎችም ለተጋጣሚያቸው ነፃነት አይስጡ እንጂ ጥቃታቸው እምብዛም ነበር። በአጋማሹ የተደረጉት ሙከራዎች በአመዛኙ የርቀት ሲሆኑ በብዙ ልዩነት ኢላማቸውን የማይጠብቁም ነበሩ። 45ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች በግራ ከሽመክት ጉግሳ መነሻነት ሳጥን ውስጥ ገብተው ኦኪኪ አፎላቢ አመሽቻችቶለት በዛብህ መለዮ የሞከረው ኳስ የታሻለ ቅርበት ኖሮት ቢታይም እሱም ወደ ላይ የተነሳ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ በድቻዎች ፈጣን ጥቃት ቢጀምርም የፋሲሎች የማጥቃት ጫና ይበልጥ ከፍ ብሎ ታይቶበታል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች አስፈሪ በሆነ ጥቃት ሳጥን ውስጥ ደርሰው አምሳሉ ጥላሁን በግራ ከእይታ ውጪ ደርሶ ከኦኪኪ የተላከለትን ኳስ አክርሮ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታው ወደ ስልሳኛው ደቂቃ ከቀረበ በኋላም ሁለቱም ቡድኖች ከወገብ በላይ ባለው የቡድናቸው ክፍል ላይ ለውጦችን አድርገዋል። ሆኖም በወላይታ ድቻ ሜዳ ላይ አመዝኖ የቀጠለው ፍልሚያ ጠንካራ ሙከራዎችን ሊያስተናግድ አልቻለም።

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ፋሲሎች በቻሉት አቅም ማጥቃት በቀጠሉበት ጨዋታ የተሻሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። ከተቀያሪዎቹ መካከል የሆነው የፋሲሉ ሳሙኤል ዮሀንስ 78ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን በተነሳ እና ዓለምብርሀን ይግዛው ባመቻቸለት ኳስ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ግብ ባይሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ፂዮን መርዕድን የፈተነ መሆን ችሏል። ፂዮን 84ኛውው ደቂቃ ላይም ከበዛብህ ሌላ ኢላማውን የጠበቀ የርቀት ሙከራ አስተናግዶ መልሷል። አልፎ አልፎ የወላይታ ድቻ የመልሶ ማጥቃት የታየባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ሳይታይባቸው እንደተጠበቀው ያልነበረው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

በውጤቱ አንድ አንድ ነጥብ የጨመሩት ተጋጣሚዎቹ በነበሩበት የአንደኛ (ወላይታ ድቻ) እና ሁለተኛ (ፋሲል ከነማ) ደረጃ ረግተዋል።