እኩል ሰባት ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚከተለው ተቃኝቷል።
በወጥነት ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጊዜ ካስመዘገባቸው የአቻ ውጤቶች በኋላ በሁለተኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ያገኘውን ድል ዳግም በማግኘት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በነገው ጨዋታ ጠንክሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።
በአሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች የሚመራው ጊዮርጊስ የተዋሀደ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም። በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑ መናበብ የሚስተዋልበት እንቅስቃሴ አለማድረጉ በተጫዋቾች የግል ጥረት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ግብ የማግኛ አማራጭ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲሆን ያደረገው ይመስላል። እርግጥ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች እና በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ስል ተጫዋች (እስማኤል አውሮ-አጎሮ) ቡድኑ ቢይዝም እነሱን አዋህዶ በቡድናዊ መዋቅር ተጋጣሚ ላይ ጫና ለማሳደር እየተቸገረ ነው። ይህ በጊዜ የማይቀረፍ የሚመስለው ችግር ነገ በአንፃሩ ተሻሽሎ ከመጣ ግን በጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ይዞ ሊወጣ ይችላል።
በሲዳማው ጨዋታ ከወትሮው በተለየ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብቶ የነበረው ቡድኑ በመስመር ተመላላሽ ቦታ ተሰልፈው የማያቁትን ከነዓን እና ተገኑን ተጠቅሞ ነበር። እርግጥ በጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች በመስመር በኩል እምብዛም ጥቃት አልፈፀሙም እንጂ በእንቅስቃሴ መሐል የቡድኑ ስስ ጎን ሁለቱ መስመሮች እንደነበሩ ታይቷል። ምናልባት ይህ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ነገም ከተደገመ ግን ቡድኑ ለክፍተቱ መፍትሔን ማምጣት የግድ ይለዋል። ካልሆነ ግን በመስመር ሽግግሮች ወቅት አደገኛ ከሆኑት ሀዋሳዎች ከባድ ፈተና ሊጠብቀው ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን ጥቂት ግቦችን ካስተናገዱት አራት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ክለቡ ነገም በጠጣርነቱ እንደሚቀጥል ሲገመት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ጥረትም ለሀዋሳዎች ሊፈትን እንደሚችል ይታሰባል።
ሌላኛው በወጥ ብቃት ሊጉን እየቀጠለ የማይገኘው ክለብ ሀዋሳ ከተማም በተከታታይ ካስመዘገባቸው የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶቹ በማገገም ወደ አሸናፊነቱ ለመመለስ እና ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋር ነገ ታትሮ እንደሚጫወት ይታመናል።
በሦስቱ የፊት መስመር አጥቂዎች ከሚገባው በላይ ጥገኛ የሆነው ሀዋሳ ከሀዲያ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥርም የአፈፃፀም ችግሩ ዋጋ አስከፍሎታል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን እንደጠቀስነው በብሩክ፣ ኤፍሩም እና መስፍን ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነ የማጥቃት ሀሳቡ ቡድኑን ተገማች እያረገው ይመስላል። በተለይ የአጥቂ አማካዮቹ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግቶ የግብ ዕድሎችን ማመቻቸት እና መፍጠር መሳናቸው እና የመስመር ተከላካዮቹ ለመከላከል ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌ ፊት ላይ ሳሳ እንዲል አድርጎታል። በነገው ጨዋታም ይህንን ጉዳይ አስተካክሎ ወደ ሜዳ የማይገባ ከሆነ እንደ ከዚህ ቀደሙ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት እንደሚቸገር ይታመናል።
በሊጉ ጥቂት ግቦችን (ሦስት) ካስተናገዱ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ዋነኛ የመሐል ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሙን በሀዲያው ጨዋታ በቀይ ካርድ ስላጣ ነገ ለውጦችን ለማረግ ይገደዳል። ይህ ለውጥ ደግሞ ምናልባት አዲስ ጥምረት ሊሆን ስለሚችልም የመከላከል አደረጃጀቱ ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል። የሆነው ሆኖ ግን ቡድኑ በጨዋታው ሊከተለው ከሚችለው ጥንቃቄ አዘል አጨዋወቱ መነሻነት በርከት ብሎ ወደ ራሱ ሜዳ በመጠጋት ለጊዮርጊስ የማጥቂያ ቦታን ለመንፈግ መንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው። ከዚህ ውጪ ግን የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን ፍጥነት በመንተራስ በፈጣን ሽግግሮች ግብ ለማግኘት እንደሚያስብም ይገመታል።
ድረ-ገፃችን ረፋድ ላይ እንዳስነበበችው የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኝ ዝላትኮ ክሪምፖቲች ግልፅ ባልሆኑ ምክንያቶች ከክለቡ ጋር ለመለያየት ከጫፍ በመድረሳቸው በነገው ጨዋታ ቡድኑን አይመሩም። አመሻሽ ላይ በሰማነው መረጃ ደግሞ ክራምፖቲች ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ንብረታቸውን ጠቅልለው የክለቡ ፅህፈት ቤት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች አሠልጣኝ የሆነው ደረጀ አንገቴ ሀዋሳ በመምጣት ከምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ቡድኑ የሚመሩት ይሆናል። በስብስቡ ውስጥ ደግሞ ከነዓን ማርክነህ፣ በረከት ወልዴ እና ተመስገን ዮሐንስ ጉዳት ላይ ናቸው። በሀዋሳ በኩል ደግሞ ፀጋሰው ድማሙ በቅጣት ብሩክ ኤሊያስ ደግሞ በጉዳት ከነገው ፍልሚያ ውጪ ናቸው።
ዘጠኝ ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ኢያሱ ፈንቴ የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ42 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በግንኙነቱ 72 ጎሎችን በማስቆጠር 25 ደል ሲያገኝ ሀዋሳ ከተማም 33 ጎሎችን በማስቆጠር 7 ድል አለው። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን ያገኙ ናቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሄኖክ አዱኛ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሱሌይማን ሀሚድ
ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም
አማኑኤል ገብረሚካኤል – አቤል ያለው – ቡልቻ ሹራ
ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
መሀመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – አዲስአለም ተስፋዬ – ዮሃንስ ሱጌቦ
ወንድማገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ