በስድስተኛው ሳምንት የሊጉ የነገ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ስለሆነው ጨዋታ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ተከታታይ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ እና አዳማ በአምስተኛው ሳምንት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበው ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። እኩል ስድስት ነጥቦች ያሏቸው ተጋጣሚዎቹ እስካሁን አጥጋቢ የሆነ ውጤት ካለመያዛቸው ጋር ተገናኝቶ ጨዋታውን በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው እንደሚያደረጉ ይታሰባል።
ሁለቱ ታጋጣሚዎች በዓመቱ መጀመሪያ ከፈፀሟቸው ዝውውሮች አንፃር ዓምና ከነበራቸው ደካማ ጉዞ የተለየ ዓመት እንዲያሳልፉ ዕምነት የተጣለባቸው ይመስላል። ይህ እሳቤ ባለፉት ሳምንታት በውጤት ያለመታጀቡ ጫና በሜዳ ላይ ባላቸው እንቅስቃሴ ውስጥ ሲንፀባረቅ ታይቷል። ሲዳማ ቡናዎች በጊዮርጊሱ ጨዋታ ወደ ፊት ገፍቶ ከመጫወት ተቆጥበው መሪነታቸውን ለማዝለቅ ያደረጉት ጥረት በዚህ ይገለፃል። በአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ ከፍ ያለ የጨዋታ ጉጉት ውስጥ ሆነው የፈጠሯቸውን በርካታ የግብ ዕድሎች ከዳር ማድረስ የተሳናቸው አዳማ ከተማዎችም ከውጤት ጋር የመገናኘት ጫና እንደነበረባቸው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት ላይ ጠቁመው ነበር። ከዚህ አንፃር ተጋጣሚዎቹ ካለፉት ግጥሚያዎቻቸው በተሻለ የአዕምሮ ጥንካሬ ወደ ሜዳ መግባት ዋናው የቤት ሥራቸው እንደሆነ መናገር ይቻላል።
የሲዳማ ቡና የማጥቃት ምርጫዎች ጥንካሬ ቀስ በቀስ የደበዘዘ ይመስላል። መጀመሪያ አካባቢ የመስመር ተከላካዮቹን ያሳተፉ ተሻጋሪ ኳሶችን ይጠቀም የነበረበት መንገድ አስፈሪነቱን አጉልቶት ነበር። በመጨረሻው ጨዋታ ግን የመስመር ተከላካዮቹ ብቻ ሳይሆኑ አማካዮችም ጭምር አመዣኙን ደቂቃ በራሳቸው ሜዳ ላይ ሲያሳልፉ ታይተዋል። ያም ቢሆን በነገው ጨዋታ ቡድኑ ከዚህ በተቃረነ የማጥቃት ፍላጎት ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን እንደሚከውን ይጠበቃል። ለዚህም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ጎል ማስቆጠር ያልቻለው የቡድኑ የፊት መስመር ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ከወገብ በላይ ያሉ ተሰላፊዎቹ በቁጥር በርክተው በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚገኙበትን አማራጭ መቀየስ ያስፈልገዋል።
በአዳማ በኩልም በተመሳሳይ ግቦችን የማስቆጠር ችግር ጎልቶ ይታያል። የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ሌላው ደካማ ጎኑ በአዲስ አበባው ጨዋታ ተቀርፎ መታየቱ መልካም ቢሆንም ያንን የማስቀጠል ሥራ ግን ይጠብቀዋል። በተለይም በዚህ ረገድ በጨዋታው የታየበት መነቃቃት ተጋጣሚው ማፈግፈግን በመረጠባቸው ደቂቃዎች ላይ መጉላቱ በወጥነት ስለመታየቱ በእርግጠኝነት ለመናገር እንዲያዳግት ያደርጋል። በነገው ጨዋታ በእኩል መጠን ገፍቶ ለመጫወት ከሚያስብ ተጋጣሚ ጋር የሚኖረው አፈፃፀም የሚጠነቅ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከተከላካይ መስመሩ ጀርባ በሚገቡ ፈጣን አጥቂዎች ሲፈተን የታየበት ሂደትም ለነገ እንዲያስብ የሚያደርግ ነበር።
በመከላከሉ ረገድ ሁለቱም እስካሁን ያሳዩት ጥንካሬ ሳይነሳ አይታለፍም። በአስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ ያልተቀየረ የኋላ ክፍል መያዛቸው እና ጥቂት ግቦችን ብቻ ማስተናገዳቸው ሲታሰብም የነገው ጨዋታ ለአጥቂዎች ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ባለፈ ግን በማጥቃት ሂደታቸው ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ተጫዋቾች መኖር ልዩነት እንዲፈጥሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። የአዳማ ከተማው ዳዋ ሆቴሳ በበድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ዋና ተዋናይ በመሆን በጥሩ አቋም ላይ መገኘት ባለፈው ጨዋታ ወጣቱ ፍራኦል ጫላ ከሰጠው ተስፋ ጋር ሲደመር አዳማን ከፊት ጥሩ ቅርፅ ሊሰጥፕው ይችላል። በሲዳማ በኩል ደግሞ ዳግም ወደ አሰላለፍ የመጣው ብሩክ ሙሉጌታ የቡድኑን የቀኝ መስመር በግል እንቅስቃሴዎቹ መነሻነት ነፍስ ሲዘራበት መታየቱ እና ከአጥቂው ይገዙ ቦጋለ ጋር የነበረው መናበበ አድጎ ከመጣ ለሲዳማ የጎል ምንጭ የመሆን አቅሙ አለዉ።
ሲዳማ ቡና የመሀል ተከላካዩ ጊትጋት ጉትን በጉዳት ሲያጣ አዳማ ከተማ ግን ሙሉ ስብስቡ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ነው።
የነገውን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በ20 አጋጣሚዎች በሊጉ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና ስምንት አዳማ ከተማ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ ሲዳማ 17 አዳማ ደግሞ 16 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)
ተክለማሪያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ያኩቡ መሀመድ – ሰለሞን ሀብቴ
ብርሀኑ አሻሞ – ሙሉዓለም መስፍን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ፍሬው ሰለሞን – ብሩክ ሙሉጌታ
ይገዙ ቦጋለ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ሚሊዮን ሠለሞን – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
ዮናስ ገረመው – አማኑኤል ጎበና – ኤሊያስ ማሞ
አብዲሳ ጀማል – ዳዋ ሆቴሳ – ፍራኦል ጫላ