የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ የመሰናበታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል

ትናንት በነበረው ዘገባችን የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ የመሰናበታቸውን ነገር በገለፅነው መሠረት በቀጣይ ክለቡን ማን የሚረከበው ይሆናል?

ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፓቲች በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነታቸው የጥቂት ወራት እድሜ ቢያስቆጥሩም በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከክለቡ ጋር ተስማምተው ስራቸውን እየሰሩ አለመሆናቸውን ተከትሎ የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ከትናንት በስትያ ማምሻውን ባደረገው ረጅም ስብሰባ አሰልጣኙ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚቀጠሉ ከሆነ በቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድር በመሆኑ እንዲሰናበቱ ወስኗል። ስለሆነም አስፈላጊውን ጉዳዮች ከፈፀሙ በኃላ አሰልጣኙ ወደ ሀገራቸው የሚሸኙ ይሆናል። የዛሬው ጨዋታ ጨምሮ የተወሰኑ ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ እና ትናንት ማምሻውን ወደ ሀዋሳ የደረሰው የተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ በጋራ በመሆን ቡድኑን ወደ ውጤታማነቱ እንዲመልሱ ኃላፊነት ሰጥተዋቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በቀጣይ ክለቡን በዘላቂነት ተረክቦ የሚያሰለጥነው ማነው የሚለው ጉዳይ አስመልክቶ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የሚመዘገበውን ውጤት ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዲስ አሰልጣኝ ከውጭ ይምጣ አልያም በምክትሎቹ ይቀጥል የሚለው ጉዳይ በሂደት የሚወሰን መሆኑን ሰምተናል። የቡድኑን መንፈስ ለመጠበቅ እና አስፈላጊውን ነገር ለማድረግ ሁለት የክለቡ የቦርድ አባላት ዛሬ ከጨዋታው አስቀድሞ ወደ ሀዋሳ የሚጓዙ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስካሁን ባለው የስድስተኛ ሳምንት ጉዞ ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኙን ያሰናበተ ሁለተኛ ክለብ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ እስማኤል አበቡበከርን በማሰናበት ቀዳሚ ክለብ መሆኑ ይታወሳል።