በስድስተኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን ውሎ የመጀመርያ በነበረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሀዋሳ ከተማን በእስማኤል ኦሮ-አጎሮ ሁለት ግቦች ታግዘው 2-1 በመርታት ደረጃቸውን ወደ ማሻሻል ችለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡናው ጨዋታ አራት ለውጦችን ሲያደርግ በደስታ ደሙ ፣ በረከት ወልዴ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና ተገኑ ተሾመ ቦታ ሱለይማን ሀሚድ ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል ያለው ተተክተዋል። ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ከሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ሦስት የአሰላለፍ ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ፀጋአብ ዮሃንስ እና አብዱልባስጥ ከማል የፀጋሰው ድማሙ ፣ ዳዊት ታደሰ እና ወንድምአገኝ ኃይሉን ቦታ በመያዝ ጨዋታውን ጀምረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይ ከቀኝ መስመር በሚነሱ ተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶች ሀዋሳ ከተማን ጫና ውስጥ ለመክተት የሞከሩ ሲሆን በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩበት አጋማሽ ነበር።
በፍላጎት ደረጃ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ግባቸውን በ15ኛው ደቂቃ አግኝተዋል ፤ ጊዮርጊሶች በግራ መስመር የላኩትን ረዘም ያለ ኳስ የተቀበለው አቤል ያለው ወደ ሳጥኑ ሲያሸጋር ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በሦስቱ ተከላካዮች መሀል በመቆጣጠር ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
በዚህ ግብ የተነቃቁ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ32ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለማጥኘት ተቃርበው ነበር ፤ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ያሳለፈለትን ኳስ ኢስማኤል በግራ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ መትቶ ሙንታሪ አድኖበታል።
አጋማሹን በሶስት የመሀል ተከላካዮች የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ፀጋአብ ዮሀንስ በአጋማሹ ጉዳት በማስተናገዱ መነሻነት ሄኖክ ድልቢን ቀይረው በማስገባት ወደ አራት የኃላ ተከላካይ ተመልሰው ጨዋታውን ለማድረግ ሞክረዋል።
እንደ ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ደካማ ጊዜያትን ያሳለፉት ሀዋሳዎች በ41ኛው ደቂቃ በቃሉ ገነነ ከቆመ ኳስ ያሻማውን እና ላውረንስ ላርቴ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣችባቸው ሙከራ ውጭ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ተመልክተናል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በተጨማሪ ደቂቃ በድጋሚ አቤል ያለው እና የአብስራ ተስፋዬ በግሩም ቅበብል ያለፉትን ኳስ አቤል ያለው ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ተንሸራቶ በማስቆጠር አጋማሹ በፈረሰኞቹ ሁለት ለባዶ መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አብዱልባሲጥ ከማልን አስወጥተው ዳዊት ታደሰን ያስገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በ50ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የመለሳቻቸውን ግብ ከፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ፤ ሱሌይማን ሀሚድ ኤፍሬም አሻሞ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አዲስአለም ተስፋዬ ማስቆጠር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በጥቂት ደቂቃዎች ልዮነት ኤፍሬም አሻሞ ዳንኤል ደርቤ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስን ተጠቅሞ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆን የኤፍሬም የግንባር ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች።
በ68ኛው ደቂቃ እስማኤል ሐት-ትሪክ ሊሰራበት የሚችልበትን አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ከጋቶች ፖኖም የደረሰውን ኳስ ላውረስ ላርቴን አልፎ ወደ ግብ ቢልክም ሙንታሪ በድንቅ ቦታ አሸፋፈን ሊያድንበት ችሏል።
ከወሀ ዕረፍቱ በኋላ ጊዮርጊሶች ጫን ብለው ወደ ሀዋሳ ሜዳ አድልተው ለማጥቃት ሞክረዋል። ሀዋሳዎች ከሜዳቸው እንዳይወጡ ከማረግ ባለፈ የቡድኑ ጫና በሙከራ የታጀበው 86ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በቀኝ መስመር በከፈቱት ጥቃት የአጎሮ ሙከራ በተከላካዬች ሲደረብ ናትናኤል ዘለቀ ከሳጥን ውጪ በድጋሚ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሀዋሳዎችም ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን የገቡበት አጋጣሚ ቢኖርም ውጤት ቀያሪ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በዘሪሁን ሸንገታ የተመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የ2ለ1 የበላይነት የተጠናቀቀ ሲሆን ጊዮርጊሶችም ነጥባቸውን ወደ 10 በማሳደግ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።