ሪፖርት | ሲዳማ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

አዝናኝነቱ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ያለቀው የሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ሲዳማ ቡናዎች ከጊዮርጊሱ የአቻ ውጤት ሙሉዓለም መስፍንን በዳዊት ተፈራ በመተካት ብቻ ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማዎች ከአዲስ አበባ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሦስት ለውጦች አድርገዋል። በዚህም ዮሴፍ ዮሀንስ ፣ አብዲሳ ጀማል እና አሜ መሀመድ በታደለ መንገሻ ፣ ፍራኦል ጫላ እና ዳዋ ሆቴሳ ቦታ ተተክተዋል።


እንደሰሞኑ ጨዋታዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሞራል ድጋፍ በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ በጊዜ ጎል አስተናግዷል። 3ኛው ደቂቃ ላይ የሀብታሙ ገዛኸኝን የማዕዘን ምት ከእይታ ውጪ የነበረው ግርማ በቀለ የጀማል ጣሰውን መውጣት ተከትሎ በቀላሉ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን በፍጥነት መሪ አድርጓል። ከዚህ በኋላ የነበረው የጨዋታ ሂደት ግን በአዳማ ከተማዎች የበላይነት የቀጠለ ሲሆን በቡድኖቹ መካከል የነበረው ፉክክርም ለዓይን ሳቢ ነበር።

ኳስ መስርተው ወደ ሲዳማ ሜዳ በመግባት ሙሉ ትኩረታቸውን ያደረጉት አዳማ ከተማዎች ወደ ቀኝ ያደላ ከፍ ያለ ጫናን ፈጥረው ተጋጣሚያቸው በራሱ ሜዳ ላይ እንዲቆይ አድርገዋል። ሆኖም የቡድኑ ጥድፊያ የበዛበት የቁጥጥር የበላይነት ንፁህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ብዙ ቆይቷል። 24ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች መሀል ሜዳ ላይ ካቋረጡት ኳስ መነሻነት መሀል ለመሀል በሰነዘሩት ጥቃት አማኑኤል ጎበና ከሳጥን አካባቢ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት አቡበከር ወንድሙ ቢያገኘውም ኃይል ያልነበረው በመሆኑ በተክለማርያም ተመልሶበታል።


የአዳማዎች ጫና ሰርጎ የገባባቸው ቅፅበቶች ጥቂት ቢሆኑም ይዟቸው የመጡት የቆመ ኳስ ዕድሎች በቁጥር ጥቂት አልነበሩም። ከእነዚህም መካከል አንዱ ተሳክቶ እነሱም ከማዕዘን ምት አቻ መሆን ችለዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ የሚሊዮን ሰለሞንን የማዕዘን ምት አማኑኤል ጎበና በግንባሩ በመግጨት አዳማን አቻ አድርጓል። ከግቡ በኋላም አዳማዎች ብልጫ ይውሰዱ እንጂ አልፎ አልፎ ይታይ የነበረው የሲዳማ መልሶ ማጥቃት ሁለት ዕድሎችን ፈጥሮ ታይቷል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸለትን ይገዙ ሲያመክነው ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ከቁጥር ብልጫ ጋር በመልሶ ማጥቃት በአዳማ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው ይገዙ ቦጋለ የሰጠውን ሀብታሙ ገዛኸኝ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ከዕረፍት መልስ የጋለው የጨዋታ እንቅስቃሴ ቀዝቅዝ ብሏል። ጨዋታው ግጭቶች በርክተውበት ሲቀጥል አዳማዎች የነበራቸውን የበላይነት ወደ መመጣጠን መጥቷል። ያም ቢሆን ቡድኖቹ ወደ ሳጥን ውስጥ ዘልቀው መግባት ቸግሯቸው ሲታይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ሙከራዎችም ከርቀት የሚደረጉ ነበሩ። 67ኛው ደቂቃ አካባቢ ግን ሲዳማዎች ከተደጋጋሚ የቅጣት ምቶች የተሻለ ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቅ ሲችሉ ለግብ የቀረበ የግብ ዕድል ግን መፍጠር አልቻሉም።


የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎችም በማጥቃት ምልልስ ደረጃ ጥሩ መነቃቃት ታይቶባቸው ነበር። ሆኖም በሁለቱም ለኩል ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች እና የቆሙ ኳስ ዕድሎች ቢፈጠሩም ወደ ጠራ የግብ ዕድልነት ሳይቀየሩ ቀርተዋል። ሰከንዶች ሲቀሩ አቡበከር አዳማን ከቅጣት ምት በመጣ ኳስ ግብ አስቆጥሮ ለድል አበቃ ቢባልም ኳሱን አብዲሳ ጀማል በእጅ ነክቶ በማመቻቸቱ ተሽሮ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።


የአቻ ውጤቱን ተከትሎ እኩል ሰባት ነጥብ ላይ ሲደርሱ ሲዳማ ቡና 9ኛ አዳማ ከተማ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።