የስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በቅድመ ዳሰሳችን በሚከተለው መልኩ ተመልክተነዋል።
ጅማ አባጅፋር ላይ ባስመዘገበው የዓመቱ የመጀመሪያ ድል የአሸናፊነትን መንገድ ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ይህ ያገኘውን የአሸናፊነት መንገድ ላለማጣት እና በአስተማማኝ ሁኔታ ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ለመውጣት የነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
ኳስን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች በመቆጣጠር የሚያሳልፈው ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች እምብዛም በዓላማ የተጋጣሚ ሜዳ ላይ በመገኘት የኳስ ቅብብሎችን ባያደርግም በጅማው ጨዋታ በአንፃሩ በዚህ ረገድ ሻል ብሎ ታይቷል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ጎል እንስከሚቆጠርበት ጊዜ ድረስ በቁጥር በርከት ብሎ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥር ነበር። ይህ ከኳስ ጋር የሚኖር ጊዜም በነገው ጨዋታም ሲጠበቅ መከላከያ ምናልባት እንደ ስሙ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ሜዳ ሊገባ ስለሚችል ግን ቡና ዕድሎችን መፍጠር ቀላል ላይሆንለት ይችላል።
ቡድኑ ጅማ ላይ ጣፋጭ ድል ሲያገኝ የመሐል አጥቂ ሆኖ የተጫወተው እና በጨዋታው ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው አቡበከር ናስር በነገውም ጨዋታ የቡድኑ ሁነኛ ተጫዋች እንደሚሆን እሙን ነው። ከዚህ ውጪ ግን በአምስት ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ያስተናገደው የቡድኑ የኋላ መስመር ግን ጥያቄዎች አሉበት። ከኳስ ምስረታ ጋር ተያይዞም የሚነሱት የዝግታ እና የስኬታማነት ችግሮች በነገው ጨዋታ ተሻሽለው መቅረብ የግድ የሚላቸው ይመስላል።
በወረቀት ደረጃ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነውን ባህር ዳር ከተማን ሁለት ለምንም አሸንፈው ለነገው ጨዋታ እየተዘጋጁ የሚገኙት መከላከያዎች ዳግም ሦስት ነጥብ በማሳካት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት አካባቢ ለመዝለቅ ነገም ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይገመታል።
ታትሮ መጫወት መገለጫው የሆነው መከላከያ በቡድናዊ መዋቅር ተቃኝቶ እንዳደረጋቸው የከዚህ ቀደም ጨዋታዎች (ከአዲስ አበባው ጨዋታ ውጪ) ነገም ሊንቀሳቀስ እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ከግለሰቦች ብቃት በላይ ሁሉንም የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ተሳታፊ በማድረግ ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል። ነገም እንደ ከዚህ ቀደሙ ዘለግ ያለውን ጊዜ ከኳስ ውጪ በማሳለፍ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ለተጋጣሚው ቡና ኳስን በመተው ሊጫወት ይችላል።
ምንም እንኳን ቡድኑ ኳሱን ለቡና እንደሚሰጥ ቢታሰብም በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ግብ ለማግኘት መንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው። በተለይ በፈጣኖቹ የመስመር አጥቂዎች እና በአጥቂ አማካዩ ቢኒያም ላይ የተንተራሰ ግብ የማግኛ መንገድ ቀይሶ ሊገባ ይችላል። ከዚህ ውጪ ደግሞ ቁመታሙ አጥቂ ኦኩቱ ኢማኑኤልን ዒላማ ያደረጉ የመስመር እና የመሐል ተሻጋሪ ኳሶችም ይጠበቃሉ። ምንም እንኳን ቡድኑ በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ ያነሱ ግቦችን ቢያስተናግድም ግን የምን ጊዜውም የአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጨዋች ከግብ ጋር መገናኘት ስለጀመረ እሱን ማቆሚያ ጠንካራ ስልት ይዞ ወደ ሜዳ መግባት የግድ ይለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ታፈሰ ሰለሞን ከክለቡ ጋር የገባበት ሰጣ-ገባ ተስተካክሎ ቡድኑን ተቀላቅሎ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ሲነገር ሬድዋን ናስር፣ አቤል እንዳለ እና ሚኪያስ መኮንን ግን ከጉዳታቸው በማገገም ዛሬ ልምምድ ቢጀምሩም በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። በመከላከያ በኩል ግን ምንም የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና እንደሌለ ተመላክቷል።
ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሐል አልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 28 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 14 ሲያሸንፍ 8 ጊዜ አቻ ተለያይተው መከላከያ 6 አሸንፏል። በ28ቱ ግንኙነት ቡና 41 ሲያስቆጥር መከላከያ ደግሞ 25 አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ
ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን
ያብቃል ፈረጃ- አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ዳዊት ማሞ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ገናናው ረጋሳ
ኢማኑኤል ላርዬ – ደሳለኝ ደባሽ
ሰመረ ሀፍታይ – ቢኒያም በላይ – አዲሱ አቱላ
ኡኩቱ ኢማኑኤል