የኢትዮጵያ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት ጀመረ

ከድል የተመለሱት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከአስራ ሁለት ቀን በኃላ ላለው የመልስ ጨዋታ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ከሜዳው ውጪ ቦትስዋናን 3-1 ያሸነፈው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኃላ የሁለት ቀን እረፍት በማድረግ ዛሬ መስቀል ፍላውር በሚገኘው 35 ሜዳ ለአንድ ሰዓት የቆየ የመጀመርያ ልምምድ ሰርቷል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ማረፍያውን አያት በሚገኘው የካፍ የልዕቀት ማዕከል ያደረገ ሲሆን በዛሬው ልምምድ ቀለል ያሉ ኳስን ትንፋሽን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ሠርተዋል። የቡድኑ አባል ከሆኑት 20 ተጫዋቾች መካከል ረድኤት አስረሳኸኝ፣ ብርቄ አማረ እና ናርዶስ ጌትነት መጠነኛ የጤና ዕክል አጋጥሟቸው በዛሬው ልምምድ ያልተገኙ መሆኑ ሲታወቅ በቀጣዮቹ ቀናት ከህመማቸው አገግመው ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ሰምተናል። ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል። በሌላ በኩል ምክትል አሰልጣኟ ቡዛየሁ ጀምበሩ እንዲሁም የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ በአንዳንድ ምክንያቶች አለመገኘታቸውን ተመልክተናል።

የካፍ አካዳሚ ሜዳ ካለበት የሜዳ ችግር አንፃር ተስፋ ለስፖርት ማህበር የ35 ሜዳን ያለ ክፍያ በመፍቀድ ያደረገው ትብብር በመልካምነቱ የሚጠቀስ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት በሸራተን አዲስ መግለጫከቦትስዋና አቻው ጋር ከሜዳው ውጪ ያደረገውን ጨዋታ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከቦትስዋና አቻው ጋር የመልሱ ጨዋታ ዓርብ ታህሳስ 8 ቀን በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወን ሲሆን ይህን ሦስተኛ ዙር ማጣርያን በድል የሚያጠናቅቅ ከሆነ በአራተኛው ዙር የታንዛኒያ እና የቡሩንዲን አሸናፊ የሚገጥም ይሆናል።