የስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሚሹ ክለባዊ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ነው።
👉 ሀዲያ ሆሳዕና 2.0 = ወልቂጤ ከተማ
የ2013 የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ወደ ኋላ ሲታወስ በቀዳሚነት ወደ አዕምሮ ከሚመጡ የውድድር ዘመኑ ትውስታዎች ውስጥ ቀዳሚው ጉዳይ የነበረው ስር የሰደደው የሀዲያ ሆሳዕና የፋይናንስ ምስቅልቅ እንደነበር አይዘነጋም። ዘንድሮም እዚህም እዚያም መሰል ችግሮች ፍንጭ ብንመለከትም የወልቂጤ ከተማ ጉዳይ ግን አፍጥጦ ወደፊት ወጥቷል።
ወልቂጤ ከተማዎች የዘንድሮው ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ የከተማ እና የዞን ምክር ቤቶች ጉባዔያቸውን ባለማድረጋቸው ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ወጪ በቦርዱ በኩል በግለሰቦች ድጋፍ እና በዱቤ ሲሸፍን እንደቆየ ይታወቃል። በሂደት በየደረጃው ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮች ጉባዔያቸውን ማካሄዳቸውን ተከትሎ በጀት ቢፀድቅም በጀቱ ባለመለቀቁ ምክንያት ከነችግሩ ወደ ውድድር የገባው ወልቂጤ ከተማ ስራውን ለማስቀጠል ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦበታል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን በረታበት ጨዋታ በዚህ ደረጃ ባይሆንም አንዳንድ የቡድኑ ተጫዋቾች ክፍያችን ካልተፈፀመ ለመጫወት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቢቀሩም በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አግባቢነት ጨዋታቸውን ማድረጋቸው አይዘነጋም። ነገር ግን ከጨዋታው ማግስት አንስቶ በነበሩት ተከታታይ ቀናት ካልተከፈለ ደመወዝ ጋር በተያያዘ ምክንያት ዘጠኝ የሚደርሱ ተጫዋቾቹ ልምምድ ማቆሟቸው እና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በሚደረገው ጨዋታ እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸው ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በፊት የነበረ ከፍተኛ መነጋገርያ ነበር።
ወልቂጤ ከአርባምንጭ የሚያገናኘው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቅ የነበረው የተጫዋቾች ዝርዝር ይፋ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች በመጀመሪያ ተመራጭነት ከሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ውስጥ ስድስት ተጫዋቾች መጠቀም ያልቻሉ ሲሆን በተጠበባቂነትም አንድ ግብጠባቂ እና ሦስት የሜዳ ላይ ተጫዋቾችን በድምሩ አራት ተጫዋቾችን ይዘው ጨዋታውን ለማድረግ ተገደዋል።
ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ደግሞ በመሀል ተከላካይ ስፍራ በቦታ ሽግሽግ እየተጫወተ ከነበረው አበባው ቡታቆ ጋር የተጣመረው ብቸኛው የቡድኑ የመሀል ተከላካይ ወሀብ አዳምስ መጎዳትን ተከትሎ በአስገዳጅ ሁኔታ ተጫዋች እንዲቀይሩ ሆነዋል።
ያለ ግብ በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች ከግማሽ በላይ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቹን ሳይዝ እንደመጫወቱ ያለመሸነፉ በራሱ እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ ሲሆን የቡድኑ አመራሮችም ተጫዋቾች የጠየቁትን በየትኛውም አግባብ ምክንያት ሊቀርብበት የማይገባውን ተገቢነት ያለው ጥያቄ በመመለስ የቡድኑን ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ሜዳ ላይ ወዳሉ ጉዳዮች እንዲመለስ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
👉 ግብ ማስቆጠር የተሳነው ሀዲያ ሆሳዕና
በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ ምንም ዓይነት ድል ማስመዝገብ የተሳነው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በአዲስአበባ ከተማ ያልተጠበቀ ሽንፈትን አስተናግዷል። ለማሸነፍ ከመቸገራቸው ባለፈ ቡድኑ ግቦች እጅጉን የራቁት እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን።
በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ እንደ ጅማ አባ ጅፋር ሁሉ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ደካማ የማጥቃት አፈፃፀምን ያሉት ሆሳዕናዎች በየጨዋታዎቹ ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ቢያሳዩም የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸውን በግብ ዕድሎች ሆነ በጎሎች ለማጀብ አሁንም ሳይቻላቸው ቀርተዋል።
ከባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ጀምሮ በማጥቃት አደረጃጀት ወቅት ቢያንስ በአምስት ተጫዋቾች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ እየጣረ የሚገኘው ቡድኑ ይህን መዋቅር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በርከት ብለው ከመገኘት ባለፈ መፍትሔ ለሚሻው የማጥቃት ጨዋታቸው መልስ ለመስጠት አልተቻለውም።
አምስት ተጫዋቾችን በማጥቃት አደረጃጀት በተጋጣሚ የማጥቂያ ሲሶ በትይዩ በመነሻነት እንዲገኙ ማድረግ በአሁኑ ወቅት በክለቦች እግርኳስ ሆነ በሀገራት ውድድር በቀዳሚ ተርታ የሚመደቡ ቡድኖች የጋራ መለያ ባህሪ እየሆነ መጥቷል። እርግጥ በቁጥር አምስት መሆናቸው ያመሳስላቸው እንጂ የእነዚህ አምስት ተጫዋቾች ስብጥር የተለያየ መልክ እንዳለው መዘንጋት አይገባም። ለአብነትም በሦስት አጥቂ የሚጠቀም ቡድን ሁለት የመስመር ተከላካዮቹን ከፍ ባለው የሜዳ ክፍል እንዲገኙ በማድረግ ይህን አምስት ተጫዋቾች በአግደመት መፍጠር የሚችሉ ሲሆን በተመሳሳይም ከሦስት አጥቂዎች ጋር ሁለቱን ስምንት ቁጥሮች ወደ ፊት ገፍቶ በማጫወት ይህን አምስት መፍጠር ከተወሰኑት መንገዶች በጣም ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው።
በሰሞነኛ ጨዋታዎች በሦስት የመሀል ተከላካዮች በ(3-4-3/3-5-2) እየተጠቀመ የሚገኘው ቡድኑ አሁንም ቢሆን የማጥቃት ጨዋታው መልክ የያዘለት አይመስልም። ለአብነትም በአዲስአበባ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች አደራደር ለውጥ እስኪያደርጉ ድረስ በተጠቀሙት ቅርፅ በማጥቃት አደረጃጀት ወቅት በአብዛኛው አጋጣሚዎች አምስት የሆሳዕና ተጫዋቾች ከአራት የአዲስአበባ ከተማ ተጫዋቾች የሚገናኙባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል።
በዚህ ሂደት በተለይ በመስመር ተመላላሾች(Wing backs) መጫወት በመሰረታዊነት የሚሰጠው ጥቅም በእነዚህ ተጫዋቾች ሚዛናዊ በሆነ ቦታ አያያዝ በመከላካል ፣ በአማካይ እና በአጥቂ መስመር የቁጥር ብልጫ መፍጠር እንደመሆኑ በሆሳዕና በኩል በመስመር ተመላላሽነት ጨዋታውን የጀመሩት እያሱ ታምሩ እና ብርሃኑ በቀለ ወደፊት ገፍተው በተደጋጋሚ ለአዲስአበባ ከተማ ሳጥን በጣሙን ቀርበው የተጫወቱ ሲሆን ከአማካይ ክፍል ደግሞ በተለይ ከሁለቱ ስምንቶች አንዱ የነበረው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ወደ ሳጥን ተጠግቶ እንዲጫወት በማድረግ ይህን ለፊት አምስት የቀረበ ቦታ አያያዝን በማጥቃት አደረጃጀት ወቅት ለመጠቀም በሆሳዕናዎች በኩል ሙከራዎች ነበሩ።
በዚህ የማጥቃት ቅርፅ ቡድኖች የሚያገኙት አንደኛው ጥቅም የማጥቃት እንቅስቃሴው ከሚገጀምርበት የሜዳ ወገን በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ሚገኝ የሜዳ ወገን ኳሶች በረጅም ኳስ አቅጣጫ እንዲቀይሩ (Switch) ሲደረጉ እንደአዲስ አበባ ያሉ በአራት ተከላካዮች የሚከላከል ቡድን በዚህ ሂደት ውስጥ የመስመር ተከላካዮቻቸው ከአምስቱ የተጋጣሚ ተጫዋቾች ውስጥ ወደ ጎን አስፍቶ ያለውን ወይስ ከእሱ አጠገብ ከውጪ ወደ ውስጥ የሚሮጠውን ተጫዋችን ለመያዝ ውዥንብር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ውጤታማ ለማድረግ ጥረቶችን ማድረግ የተለመደ ሆኗል።
የማጥቃት አቅጣጫን (Point of Attack) በመቀየር ረገድ እጅግ ደካማ አፈፃፀም የነበራቸው ሆሳዕናዎች ሁለት አጋጣሚዎችን ከቀኝ መስመር ወደ ግራ ኳሶችን በመገልበጥ ይህን ለማድረግ ሞክረው በተወሰነ መልኩ አዲስአበባን አደጋ ውስጥ መክተት ችለው ነበር። ነገርግን ይህ ሂደት ሲደጋገም መመልከት ሳንችል ቀርተናል። በተጨማሪም ፊት ላይ በቁጥር እንደመብዛታቸው የተጋጣሚ ተከላካዮችን ወደ ጥልቀት በመሮጥ ወደ ኃላ ተስቦ በመጫወት እና በተለያዩ መንገዶች ውዥንብር ውስጥ ከመክተት አንፃር እንዲሁ ውጤታማ አፈፃፀም አልነበራቸውም።
በዚህ ሂደት በመከላከል ሽግግር ወቅት የነበራቸው እጅግ ዘገም ያለ ሽግግር እና መጠነ ሰፊ የቦታ አያያዝ (Positional) ስህተቶች የአዲስአበባ ከተማ ተጫዋቾች መጠቀም አልቻሉም እንጂ ይህ የማጥቃት ቅርፅ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ ነበር። አተገባበሩ የተለየ ይሁን እንጂ ይህን የማጥቃት ሀሳብ በባህርዳር ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና በተለያየ መንገድ ለመተግበር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ብንመለከትም በልምምድ ሜዳ ላይ ሀሳቦቹ በበቂ መጠን እንዳልተሰሩ (Coach) እንዳልተደረጉ በደንብ እየተመለከትን እንገኛለን።
👉ስለ ተፎካካሪነት ማሰብ የጀመረው አዲስ አበባ ከተማ
ሊጉ ሲጀመር ብዙዎች የዚህ ቡድን መጨረሻ እንደ 2009 የውድድር ዘመኑ ባደገበት ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ እንደተመለሰው ቡድን ሊሆን ይችላል የሚሉ ሀሳቦች ቢሰነዘሩም አዲስአበባ ከተማ አስደናቂ መሻሻሎች በማሳየት ወደ ሰንጠረዡ አናት መጠጋት ችለዋል።
በመጀመሪያ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በባህርዳር ከተማ እና በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ከሽንፈቶቹ ባለፈ በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን የማስተናገዱ ጉዳይ ከነበራቸው ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ቡድኑ በስጋት እንዲሸበብ ያስገደደ ነበር።
ነገርግን በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ሦስቱን በማሸነፍ በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይተው ከአስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን ማሳካት ችለዋል ። በወቅታዊ አቋም የመጨረሻ አራት ጨዋታዎችን ነጥለን ብንመለከት ከወላይታ ድቻ ቀጥሎ ሁለተኛው ጠንካራ ቡድን እየሆነ እንደመጣ እየተመለከትን እንገኛለን።
አሁን ላይ በአስር ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻሉት አዲስአበባ ከተማዎች ይህን አስገራሚ ግስጋሴ በማስቀጠል በሊጉ ምን ያህል ወደፊት ይጓዛሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 አሰልጣኙን የማይመስለው ሰበታ ከተማ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በማሰልጠን ላይ ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያላቸው ቡድኖች በመገንባት ከሚታወቁ አሰልጣኞች ውስጥ አንዱ ዘላለም ሽፈራው እንደሆኑ በተደጋጋሚ የገነቧቸው ቡድኖች ምስክር ናቸው። በአዲሱ ቡድናቸው ሰበታ ከተማ ግን ይህ እየሆነ አይገኝም።
በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባልተጠበቀ መልኩ ለተጋጣሚያቸው በቀላሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን የሚፈቅዱ ፣ በርከት ያሉ አደገኛ ግለሰባዊ ስህተቶች የሚፈፅሙ እንዲሁም በመከላከሉ ረገድ የተበታተነ ቅርፅ ያለው ቡድን ሆነው ተመልክተናል።
በእርግጥ በስድስት የጨዋታ ሳምንት በአማካይ በጨዋታ አንድ ግብ እያስተናገደ የሚገኘው ቡድኑ በሊጉ ከሦስት ቡድኖች ጋር በጣምራ አራተኛው ደካማ የተከላካይ መስመር ባለቤት ነው። ከዚህ ባለፈ ቡድኖች በሊጉ ካለው ደካማ የግብ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ንፃሬ አንፃር ሆነ እንጂ በየጨዋታው ለተጋጣሚዎች በቀላሉ የማግባት አጋጣሚዎችን እንደመፍቀዳቸው በተጋጣሚዎቻቸው የሚገባቸውን ቅጣት እያገኙ አይደለም።
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ይህ ጉዳይ በጉልህ እየታየ ይገኛል። ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ 4-2 የተሸነፈው ቡድኑ ያስተናገዳቸው ግቦች እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በዋነኝነት ከመስመሮች መነሻቸውን ባደረጉት የድሬዳዋ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማቋረጥ ተቸግሮ ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን ሲያስተናግድ አስተውለናል።
በጥቅሉ ከሰሞኑ እየተመለከትነው የምንገኘው ሰበታ ከተማ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የጨዋታ መፅሀፍ ላይ መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳቦችን የሳተ መሆኑን እየተመለከትን እንገኛለን። በተጨማሪም ከብኩኑ የቡድኑ የአጥቂ መስመር ጋር ተዳምሮ ሰበታ ከተማ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኝ አስገድደዋል።
👉 ቡናማዎቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግበዋል
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ያሳኩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ መከላከያን በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ማሰመዝገብ ችለዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በንፅፅር በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነት ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች መከላከያን ሲረቱ ግን ተቀያያሪ መልክ ነበራቸው። ጨዋታውን እንደተለመደው ተጋጣሚያቸው ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ በአውንታዊነት የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በቀኝ መስመር በኩል የሚሰነዝሩት ጥቃት ይበልጥ አደገኛ የነበረበትን አጋማሽን አሳልፈዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከተጋጣሚያቸው የሚሰነዘረው ጫና ያየለባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ተገፍተው በጥንቃቄ ሲጫወቱ ብሎም ከሜዳቸው ለመውጣት ተቸግረው በርከት ያሉ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሲልኩ እና በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ የመልሶ ማጥቃት መልክን ተላብሰው ወሳኝዋን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ታትረዋል።
ከውጤቱ ባለፈ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የቡድኑ ተጫዋቾች በሁለተኛው አጋማሽ ሜዳ ላይ ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ የሚሆኑ አይመስልም። ይህንንም ከኮአሰልጣኙ በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው በሚገባ ያነሱት ሲሆን በተከታታይ የተመዘገቡት ድሎች የቡድኑን የራስ መተማመን ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ከፍ ከማድረግ አንፃር ዓይነተኛ ሚና እንደሚወጡ ቢታመንም ቡድኑ ቀስ በቀስ ከነጥቦቹ ባለፈ ስለሚታወቅበት የጨዋታ መንገድ (Style of Play) በጨዋታዎች ላይ በቀጣይነት ማስቀጠል ስለሚችልበት መንገድ ማሰብ ይኖርበታል።
👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀደመ ቀጥተኝነቱ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን በረታበት የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስመለከቱን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቀደመውን ቅዱስ ጊዮርጊስን በተወሰነ መልኩ የሚያስታውስ ነበር።
በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኛቸው ዘሪሁን ሸንገታ የተመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ በአስራ ሁለት አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ጥቃቶችን የሰነዘሩ ሲሆን አስራ አንዱ(92%) የሚሆነው የቡድኒ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻውን ያደረገው ከሁለቱ መስመሮች እንደነበር ቁጥሮች ያሳያሉ። ምናልባት ይህ ቁጥር (Sample Size) ከድምዳሜ ለመድረስ በቂ ባይሆንም ግን የሚሰጠን ጠቋሚ ነገሮች እንዳሉ መመልከት ችለናል።
እግርኳሳዊ ማንነት (Footballing Identity) በሌለበት እግርኳሳችን ምናልባት ይህን ማውራት ተገቢ ባይሆንም የአስራት ጊዜያት የሊጉ አሸናፊ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን ከዚህ የስኬታማነት ጉዟቸው በስተጀርባ ቡድኑ ይበልጥ ከቀጥተኛ አጨዋወት ጋር የተሳሰረ መገለጫ ያለው ቡድን እንደሆነ መናገር ይቻላል። ነገርግን ባለፉት ዓመታት ቡድኑ በተወሰነ መልኩ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብቶ እንደነበር መናገር ይቻላል።
በዚህ ሳምንት በዘሪሁን ሸንገታ የተመራው ቡድን የቀደመውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያስታውስ መልኩ በተደጋጋሚ በመስመሮች በኩል ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሙከራዎች ሲያደርግ አስተውለናል። በተለይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል ከአጠቃላዩ የመስመር ጥቃቶች ውስጥ ሰባት (63%) የሚሆኑት መነሻቸውን ያደረጉ ነበሩ።
በቀጣይ ጨዋታዎች ቡደኑ በምን መልኩ ይቀርባል የሚለው ጉዳይ በጉጉት የሚጠበቅ ቢሆንም ምን አልባት ውስጠ ሚስጥሩን ጠንቅቀው የሚያውቁት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድኑን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ የአጨዋወት ምርጫውንም ወደ ቀደመውን መንገድ ይልሱት ይሆን ? ብለን እንድጠይቅ የሚያደርግ የጨዋታ ሳምንትን ተመልክተናል።