የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በስድስተኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው በአሰልጣኞች ዙርያ የሚነሱ ሀሳቦችን በሦስተኛው ፅሁፋችን ተመልክተናቸዋል።

👉 የአሰልጣኞቻችን ደካማ የጨዋታ ወቅት አስተዳደር

የአሰልጣኞች አቅም በትክክል ከሚፈተንባቸው መመዘኛዎች አንዱ እና ዋነኛው የአሰልጣኞች የጨዋታ ወቅት አስተዳደር (In game management) እንደሆነ ይታመናል። በዚህ መመዘኛ ግን በሊጉ እያሰለጠኑ የሚገኙ አሰልጣኞች በጥቅሉ ደካማ አፈፃፀም እንዳላቸው እየተመለከትን እንገኛለን።

ቡድኖች ከጨዋታ በፊት በሚኖሩ ቀናት የተጋጣሚያቸውን ሁኔታ በማጥናት መሰረታዊ የጨዋታ ሀሳባቸውን ሳይለቁ እንደ ጨዋታው ይበጀናል ያሉት የጨዋታ ዕቅድ ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ነድፈውት የገቡት ጨዋታ ዕቅድ ከራሳቸው ተጫዋቾች የአተገባበር ችግር ወይንም ተጋጣሚያቸው ከጠበቁት መንገድ ውጪ በመቅረቡ አልያም በሌላ ምክንያት በሚፈለገው መንገድ ውጤታማ ላይሆን ይችላል።

ይህ ሁኔታ ሲፈጠር የአሰልጣኞች የጨዋታ ማንበብ እና የመረዳት አቅም የሚፈተንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ከዚህ አንፃር የሊጉን አሰልጣኞች ከመዘንናቸው አፈፃፀማቸው ደካማ በሚባል ደረጃ ነው።

በሊጉ በስፋት እንደሚስተዋለው ይዘውት የገቡት የጨዋታ መንገድ በሚፈለገው ደረጃ እንኳን እየሰራ ባልሆነበት ሂደት አሰልጣኞች ይህን ሂደት ለመቀልበስ የተጫዋቾች ፣ የጨዋታ መንገድ ፣ የስልት ሆነ የአደራደር ለውጥ ለማድረግ በጣም ሲዘገዩ ብሎም ይህን ሂደት ለመቀልበስ ሳይችሉ ቀርተው መመልከት በጣም የተለመደ ነው።

የሊጉን የፉክክር ደረጃ ለማሳደግ አሰልጣኞች በዚህ ረገድ የሚስተዋልባቸውን ክፍተት መሙላት የግድ ይላል።

👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ የአሰልጣኞች ቅጥር አዙሪት ቀጥሏል

ከሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ፊቱን ወደ ውጭ ሀገራት ካዞረ ሁለት አስርት ዓመታት ለመድፈን የተቃረበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደርዘን የላቁ አሰልጣኞችን በእነዚሁ ዓመታት አፈራርቋል። ይህ ሂደት ግን ከ2009 ወዲህ እየሰራ ያለ አይመስልም።

በ2009 የውድድር ዘመን ከሊጉ ባሻገር ስኬታማ የነበረ አህጉራዊ ጉዞን ማድረግ የቻለው ቡድኑ 2010 የውድድር ዘመን ጅማሮ ወቅት ከሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርት ኑይ ጋር በጤና እክል ምክንያት ከተለያየ ወዲህ ያደረጋቸው የአሰልጣኝ ቅጥሮች እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም።

እሳቸውን ተክተው ቡድኑን የተረከቡት ፖርቹጋላዊው ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ ቡድኑ ለዘመናት ከሚጣወቅበት ቀጥተኛ እግርኳስ አውጥተው በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ቡድን ለመገንባት ብዙ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ማጠናቀቂያ ዕለት የሊጉን ዋንጫ በጅማ መነጠቃቸው አይዘነጋም። በቀጣዩ የውድድር ዘመን ጅማሮም የመጋረጃ መግለጫ የነበረውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ማሳካት አለመቻላቸውን ተከትሎ በቅድመ ውድድር አብረውት ከቆዩት ስብስብ እንዲለዩ ተደርጓል።

በ2011 የውድድር ዘመን ጅማሮ የፈረሰኞቹን የአሰልጣኝነት መንበር የተረከቡት እንግሊዛዊው ስቲዋርት ሐል ቡድኑን ወደ ቀደመ ቀጥተኝነቱ ለመመለስ ቢያልሙም በብርቱካናማው እና ቀዩ ቤት የነበራቸው ቆይታ ከስምንት ወር የዘለለ አልነበረም። በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት በሜዳቸው በደቡብ ፖሊስ መሸነፋቸውን ተከትሎ ከቡድኑ ተለያይተዋል።

በ2012 የውድድር ዘመን ደግሞ በድንገት ፈረሰኞቹን የተረከቡት ሰርቢያዊው ሰርጂዮ ከመከላከል ጥንካሬው ባለፈ በቀደሙት ዓመታት አስተማማኝ ያልነበረውን የቡድኑን የማጥቃት ጨዋታ አስደናቂ የአጥቂ ተጫዋቾች ጥምረትን በመፍጠር ተፎካካሪ ቡድን የገነቡ ቢመስልም መልበሻ ቤቱን ለመቆጣጠር በመቸገራቸው እንዲሁም ከጨዋታ መንገድ ጋር በተያያዘ ከደጋፊዎች በቀረቡባቸው ተቃውሞዎች ሊጉ በኮቪድ መከሰት ከተቋረጠበት ጊዜ ጥቂት ቀደም ብለው ክለቡን እንዲለቁ ተደርጓል።

በ2013 የውድድር ዘመን በአፍሪካ በተለይም በደቡብ አፍሪካ የካበተ ልምድ ያላቸውን ኤርነስት ሚድንዶርፕ እና ረዳታቸውን ማሒር ዳቪድስን ወደ ኃላፊነት ያመጣው ቡድኑ ዋና አሰልጣኙ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ ሁኔታ ስጋት ፈጥሮብኛል በሚል ገና ሊጉ ሳይጀመር መልቀቃቸውን ተከትሎ በወጣቱ ማሒር ዳቪድስ ውድድራቸውን ጀምረዋል። ነገርግን አሰልጣኙ በክለቡ የውድድር ዘመኑን ማጠናቀቅ ሳይችሉ በ16ኛው የጨዋታ ሳምንት እህል ውሃቸው አብቅቶ በምትካቸው ፍራንክ ናታል የተሰኙ ሌላ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ በመቅጠር ነበር የውድድር ዘመኑን ያገባደደው።

ዘንድሮው በተመሳሳይ በሰርቢያዊው ዝላትኮ ክራምፖቲች ጋር የውድድር ዘመኑን የጀመረው ቡድኑ ካልተረጋጋ የጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ አሰልጣኙ ቡድናቸው በስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት የመሰናበታቸው ጉዳይ እርግጥ ሆኗል።

በተለይ ከ2010 የውድድር ዘመን ባሉት ዓመታት ቡድኑን በፍጥነት ወደ ቀደመው ውጤታማነቱ ለመመለስ በክለቡ ቦርድ በኩል ለውሳኔዎች የመጣደፍ ነገር እንዳለ በተደጋጋሚ እያስተዋልን እንገኛለን። ከሁሉም በፊት ግን የሚቀድመው ስህተት ከአሰልጣኞቹ የምልመላ ስርዓት የሚመነጭ ነው።

የክለቡን እግርኳሳዊ መዋቅር የሚመራ ባለሙያ የሌለው መሆኑን ተከትሎ የአሰልጣኞች ምልመላ የሚደረገው የቦርድ አመራሮች በግላቸው በውጪ ሀገራት ያሏቸውን ሰዎች በመጠቀም መሆኑ የሚመጡት አሰልጣኞችን በጥልቀት በእግርኳሳዊ መመዘኛዎች (Footballing Merit) ለመልመል ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ሲያደርገው ቆይቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአሰልጣኝ ሹም ሽሮች ውስጥ ቡድን በየጊዜው የእግርኳሳዊ አስተሳሰብ ሽግግር ለማድረግ ሲገደድ በዚህም በሜዳ ላይ ውጤታማነትም ሆነ በሚመለምላቸው በሊጉ ደረጃ ጥራታቸው የላቁ ተጫዋቾች ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረገ ይገኛል።

አሁንም ቢሆን ቡድኑ ራሱን ወደ ቀደመው ገናናነቱ ለመመለስ በቅድሚያ የክለቡን ሽግግር ሊያሳልጥ የሚችል የቴክኒክ ዳይሬክተር መቅጠር የግድ ይለዋል። ይህም በአሰልጣኝ ቅጥርም ሆነ በተጫዋቾች ምልመላ ላይ በአሰልጣኞች መለዋወጥ የማይቀያየር የክለቡ መገለጫ የሆነ እግርኳሳዊ እሴትን በመፍጠር መሰል የሽግግር ወቅቶችን የተሳለጠ ማድረግ ይገባቸዋል።

በተመሳሳይ አሁንም ቢሆን ቡድኑ ስለሚያመጣቸው አሰልጣኞች በጥልቀት በማጥናት መቅጠር ፣ ከቅጥሩ በኋላም ለሥራቸው ምቹ የሆነ ከባቢ እና ጊዜ መስጠት የማይችል ከሆነ ወደ ቀደመው ድል አድራጊነቱ ለመመለስ አሁንም ጊዜያትን ለመጠበቅ ሊገደድ ይችላል።

👉 የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከባድ ፈተና

በአማራጮች የተሞላ ስብስብ እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር ጠንካራ አጀማመር የሚያደርግ ቡድን መገንባት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድኖች መለያ ባህሪያት ነበሩ። ዘንድሮ ግን በጅማ አባ ጅፋር የገጠማቸው ከዚህ በተቃራኒ ሆኗል።

ገና ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈልጉትን ተጫዋች ለመመልመል የተቸገሩት አሰልጣኙ ውድድሩ ከተጀመረ ወዲህም እየገጠማቸው የሚገኘው ነገር በአሰልጣኝ አሸናፊ ስር በሚሰለጥኑ ቡድኖች ባልተለመደ መልኩ ከስድስት ጨዋታ በኋላ ምንም ነጥብ ማስመዝገብ የተቸገረ ቡድን ሆኗል።

እርግጥ ቡድኑ በግልፅ በሚታይ መልኩ የስብስብ ጥራት ብቻ ሳይሆን የተጫዋቾች ቁጥር ችግር እንዳለበት ይታወቃል። ጥቂት ባለልምድ ተጫዋቾች ከወጣት ተጫዋቾች ጋር በማዋሀድ ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት የሞከሩት አሰልጣኙ ይህ አስገዳጅ ውሳኔ እስካሁን ውጤት አላስገኘም። አሰልጣኙ በቀደሙት ጊዜያት የስራ ልምዳቸው እንደሚያሳየው በየመጫወቻ ሜዳው በጥራት ጠብሰቅ ያለ ቡድንን መገንባት እንደመፈለጋችው በጅማ አባ ጅፋር ያገኙት ስብስብ ከፍላጎታቸው ውጪ በአስገዳጅ ሁኔታ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

በተመሳሳይ ከጨዋታ መንገድ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄን የሚመርጡት አሰልጣኙ አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ለቀቅ ያለ እና በተጋጣሚው ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ የሚሞክር ቡድን ሆኖ ተመልከተናል። ይህም የአጨዋወት ማስተካከያ በፍላጎት ወይስ የቡድኑ ስብስብ አስገድዷቸው የሚለውም ነጥብ ሌላው መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው።

በቀደሙት ዓመታት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ላይ ከሚቀርቡ ወቀሳዎች አንዱ በመጀመሪያው ዙር ቡድኖቹ ከሚያደርጉት አጀማመር እና ከያዙት ስብስብ አንፃር ይህን አጀማመራቸውን አስቀጥለው ለዋንጫ ያለመብቃታቸው ጉዳይ ሲሆን የዘንድሮው ፈተናቸው ግን ይህን የአማራጮች አጥረት ያለበትን ስብስብ በሊጉ ሊያቆዩት ይችላሉ ወይ የሚለው ሆኗል።

👉 ዳኞች ላይ የሰላ ትችት ያቀረበው ዘርዓይ መሉ

ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱን ተከትሎ አሰልጣኞች ከጨዋታ በኋላ በሚኖራቸው የድህረ ጨዋታ አስተያየት ወቅት ባልተለመደ መልኩ በዳኞች ዙርያ የሚሰጧቸው አስተያየቶች በተወሰነ መልኩ ለዘብ ያሉ እና የተለሳለሱ እየሆነ መጥቷል።

ነገርግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ዳኞች ላይ ጠንከር ያለ ሀሳብን ሰጥተዋል።

“አንደኛ ዳኝነት በጣም መስተካከል አለበት። በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በተለይ መለስ ብዬ ፊልሞችን ስመለከት ብዙ ነጥቦችን እየጣልን የምንገኘው በዳኞች ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ብዙ ፍፁም ቅጣት ምቶችን ስንከለከል ነው የማየው ፤ ግን ቅሬታ አቅርቤ አላውቅም። ዛሬ ግን ከዕረፍት በኋላ በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሚሰሩ ጥፋቶች ኳስ ያስቆማል ግን ቶሎ አያስጀምርም ነበር። ደጋፊው ኳስ ሊያይ ነው የመጣው እንደዚህ ያለ ነገር ሊቆም ይገባል። ሌሎች ዳኞች እርምጃ ይወስዱ ነበር ፤ ካርድ ይሰጡ ነበር። ዛሬ ግን ይህ አልሆነም። ይህን ጨዋታ ይዘው የወጡት በዚህ ነው እንጂ እንዳደረግነው እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል እንደመድረሳችን ጥሩ ነበርን።”የሚል ሀሳብን ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው የጨዋታ ሳምንትም አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም በዳኞች ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሀሳብ መስጠታቸው አይዘነጋም።

👉 ግልፅነት የተሞላበት የዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ አስተያየት

ድሬዳዋ ከተማ ከሰበታ ከተማ ጋር ያለ ግብ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በጨዋታው በርከት ያሉ የተሻሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ተጫዋቾቻቸው መጠቀም ባለመቻላቸው ሁለት ነጥብ ጥለው ለመውጣት የተገደዱት የድሬዳዋ ከተማዎች አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ስለ ቡድናቸው አጨራረስ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ወደፊት እንሄዳለን ኳሶችን ከመስመር ወደ ጎል እናደርሳለን ግን አጨራረስ ላይ ክፍተቶች አሉብን። ይህንንም በግልፅ ተነጋግረን ቀርፈን መምጣት ይኖርብናል። አንዳንድ ቡድኖች ከአንድ አንድ ዕድል አግኝተው ያስቆጥራሉ። እኛ ግን ተደጋጋሚ ዕድሎችን ፈጥረን መጠቀም እየቻልን አይደለም።”

“ዕድሎችን መፍጠር ብንችልም አሁንም አጨራረስ ላይ ክፍተቶች አሉብን። ይህም በኋላ ላይ የሚያስቆጨን ይመስለኛል። አጨራረሳችን የማናስተካክል ከሆነ ረጅም ርቀት ለመጓዝ እንቸገራለን።”

ያጋሩ