ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው የፅሁፋችን ክፍል ደግሞ ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የተዳሰሱበት ነው።

👉 ለመከላከያ ሠራዊት የሞራል ድጋፍ. . .

ከጨዋታ መጀመር አስቀድሞ በዕለቱ አርቢትር መሪነት የሚደረጉ ተጫዋቾችን ጨምሮ በስታዲየም ውስጥ የተገኙ የስፖርት ቤተሰቦች የሚሳተፉባቸው መርሐ ግብሮች የተለመዱ ናቸው። በእኛም ሀገር ሊግ በብዛት በእግርኳሱ አበርክቶት የነበራቸው ግለሰቦች በስጋ መለየትን ተከትሎ በዚሁ ሥነ ስርዓት በህሊና ፀሎት የሚታሰቡበት ሂደት የተለመደ ነው።

በስድስተኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ይኸው ከጨዋታ በፊት የሚከወነው ሥነ ስርዓት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረግ ተከውኗል። በዚህም ከሁሉም ጨዋታዎች መጀመር አስቀድሞ የተጋጣሚ ቡድን አባላት እና በሀዋሳ ዩንቨርስቲ ስታድየም የተገኙ የስፖርት ቤተሰቦች በጭብጨባ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የህይወት መስዕዋትነት በመክፈል ላይ ላለው የሀገር መከላያ ሠራዊት የሞራል ድጋፍ አድርገዋል።

👉 አሰልቺ የጨዋታ ሳምንት

በአምስተኛ የጨዋታ ሳምንት በክስተቶች የተሞሉ ጨዋታዎችን የተመለከትን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በተቃራኒ አሰልቺ መልክ የነበራቸው ጨዋታዎች በርከት ብለው የተመለከትንበት ነበር።

በቀናት ልዩነት በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍፁም የተለያዩ መልኮች ያላቸው ቡድኖችን መመልከት አንዱ የሊጉ ባህሪ እንደሆነ ቀጥሏል። እርግጥ በጨዋታ ሳምንታት መካከል ያለው የቀናት ልዩነት ጠባብ መሆኑ ቡድኖች በቂ የማገገሚያ ጊዜ ከማግኘት አንፃር በራሱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆነ ወጥ የሆኑ ቡድኖችን ፈልጎ ማግኘት ግን ከባድ እንደሆነ ቀጥሏል።

በተጨማሪም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ተቀራራቢ መሆኑ በየጨዋታዎቹ የሚመዘገቡ ውጤቶች በሰንጠረዡ ላይ የሚያስከትሉት መለዋወጥ ከፍ ያለ ሆኗል። በዚህ ውስጥም ላለመሸነፍ የመጫወት ዝንባሌዎች ገና ከወዲሁ እየተመለከትን እንገኛለን ይህም ምናልባት በቀጣይ ውድድሩ እየገፋ ሲሄድ ይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያተኮሩ ቡድኖች በዝተው የሊጉን የፉክክር ጣዕም እንዳያሳጣው ስጋትን የሚያጭር ነው።

ባልተለመደ መልኩ ከተደረጉት ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱ ያለግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ በተመሳሳይ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁ በአንድ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ ነበሩ። በድምሩ በጨዋታ ሳምንቱ ዘጠኝ ግቦች የተገቆጠሩበት መሆኑም ለመቀዛቀዙ ሌላ ማሳያ ነበር።

👉 በአቅማቸው ልክ ለመኖር የተቸገሩት ክለቦቻችን

ሁሉም ክለቦች አንድ ዓይነት መንገድ ፤ ገንዘብ ማውጣት ፣ ማውጣት ፣ ማውጣት…

በሀገራችን እግርኳስ አዳዲስ ሀሳቦችን መሞከር በጣሙን እንደሚፈራ ያለፉት ዓመታት ተሞክሯችን በቂ ማሳያ ናቸው። በተለይም ከገንዘብ አወጣጥ ጋር በተያያዘ ሁሉም ክለቦች አንዱ ጋር ሰርቷል የተባለን ተሞክሮ እንደ ወረደ የመኮረጅ እንጂ ለራሱ እንዲስማማ አድርጎ የመተግበር አካሄድን ሲከተል አልተመለከትንም።

እርግጥ ተፎካካሪ ቡድኖችን ለመገንባት ገንዘብ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ባለፉት 20 ዓመታት በቀደመው ጊዜ ይህ ነው የሚባል ታሪክ የሌላቸው ክለቦች በፈርጣማ የፋይናንስ አቅም ባላቸው ባለሀብቶች እጅ ገብተው የዓለም አቀፍ እግርኳስን አጠቃላይ የኃይል ሚዛን መቀየራቸው የማያጠያይቅ ሀቅ ነው። በእኛ ሀገርም መጠኑ ይለያይ እንጂ የተሻለ የፋይናንስ ነፃነት ያላቸው ክለቦች የሊጉን ክብር ሲያሳኩ መቆየታቸው ይታወቃል።

በእኛ ሀገር አውድ በመንግሥት የልማት ድርጅት ስር የነበሩ ክለቦች ቁጥር መቀነስን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በማዘጋጀ ቤት ስር የሚታደደሩ የከተማ ክለቦች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። በዚህም አብዛኛዎቹ የሊጉ ክለቦች በቀጥታ ከመንግሥት በሚለቀቅ በጀት ህልውናቸውን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።

እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ጉዳይ የተደላደለ ፋይናንስ አቅርቦት መኖሩ ብቻ ውጤታማ አለማድረጉ ነው። ከሌሎች ተፎካካሪዎች አንፃር በንፅፅር የተሻለ እግርኳሳዊ መዋቅር ይዞ መገኛትም ለውጤታማነት ከፍተኛ ሚናን ይወጣል።

አሁን ላይ እርግጥ ከሊግ አክሲዮን ማህበሩ መምጣት ጋር ተያይዞ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም እግርኳሱ በራሱ ገቢ ማመንጨት ቢጀምርም አሁንም ክለቦች ከዓመታዊ ጠቅላላ በጀታቸው ውስጥ በሚያመነጩት ገቢ የሚሸፈነው መጠን አነስተኛ እንደመሆኑ ድጎማውን መጠበቃቸው አልቀረም።

ይህ መንግሥታዊ ድጎማ በአንዳንድ ሁኔታዎች በወቅቱ ሳይለቀቅ ሲቀር እንዲሁም በመጠንም ቅናሽ በሚያስይበት ወቅት ክለቦች በሰፊው ከመልመዳቸው ጋር በተያያዘ ከበጀት ቅነሳው ጋር ራሳቸውን ለማስተካል ሲቸገሩ ይስተዋላል።

ለዚህ ሁሉ ችግር መሰረታዊው ምክንያት ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት የግድ እና የግድ በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ እና ወርሃዊ ደመወዝ እንዲሁም በሌሎች ማማለያዎች በየዓመቱ ተጫዋቾች በብዛት መፈረም ይገባቸዋል የሚለው የእግርኳሳችን ያልተፃፈው ሕግ ነው።

ቡድኖች ከዓመት ዓመት ተሻሽለው ለመቅረብ ወደ ገበያ መግባታቸው ባልከፋ ነበር። ነገር ግን ቡድኖችን በየዓመቱ እያፈረሱ መገንባት በተለመደበት ሁናቴ በቀጣይነት ይህን ማድረግ በፋይናንስ ረገድ ከሚፈጥረው ጫና ባለፈ የቡድኑን ውጤታማነት በጣሙኑ እንደሚጎዳ እየተመለከትን ነው።

የሚያሳዝነው ነገር ከሞላ ጎደል ሁሉም ክለቦች ይህን መንገድ የመከተላቸው ጉዳይ ሁኔታውን በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የዋጋ መድሎ(Price Discrimination) ማለትም በቂ ገንዘብ ባለመያዛቸው ሳቢያ የሚፈልጉትን እንዳይገዙ የገበያ ሁኔታ ካላስገደዳቸው ክለቦች በስተቀር ሁሉም ክለቦች በዝውውር መስኮቱ ባለ በሌለ አቅም ተጫዋቾች በማዘዋወር ሲጠመዱ እናስተውላለን።

በተወሰነ መልኩ የተለየ ነገር ለመሞከር እየጠሩ ከሚገኙ ጥቂት ክለቦች ውጪ በሁሉም ክለቦች ያለው አስቀያሚ ልምምድ ይህ ከላይ የጠቀስነው ነው። ነገርግን ይብዛም ይነስም ሁሉም ክለቦች በፋይናንስ ለመፎካከር የሚያስችል ቁመና ላይ አይገኙም። በመሆኑም የተሻለ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ክለቦች በፈለጉት መንገድ የመጓዝ አቅም ሲኖራቸው በተቃራኒው ውስን የፋይናንስ አቅም ያላቸው ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ፈጠራ የታከለባቸው አዳዲስ መንገዶች መጠቀም የማይችሉ ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አሁን ላይ እንደ አሸን የፈሉት በመንግሥት የሚደገፉ ክለቦች ቀጣይነት አደጋ ውስጥ እንደሚገባ አያጠያይቅም።

👉 ችላ የተባለው የተጫዋቾች ድርጊት

በሊግ ውድድሮቻችን ላይ ከየትኛው የዳኝነት ውሳኔ በኋላ “ተበድያለሁ” የሚለው ክለብ ተጫዋቾች ዳኞችን ማዋከብ እና መክበብ የተለመደ ድርጊት ሆኗል።

ከከበባው ባለፈ ተጫዋቾቻችን ዳኞችን የሚጎነትሉበት መንገድ ግን እጅግ በጣም አስነዋሪ ምግባር ነው። በአንዳንድ አጋጣሚ ተጫዋቾቻችን “የመንደር ጎረምሳ” ይመስል ብዙዎች በቴሌቪዥን በሚከታተሉት ውድድር ላይ ከዳኞች ጋር የሚፈጥሩት ያልተገባ ግርግር አሁንም የሊጉ አሉታዊ መገለጫ እንደሆነ ቀጥሏል።

በዚህ ሂደት ዳኞች ራሳቸውን ለማስከበር የሚያደርጉትም ጥረት እጅግ አነስተኛ መሆኑ እና ሁኔታዎቹን አቻችለው የሚያልፉበት መንገድ ተጫዋቾቹ ዘንድ ‘እንደዚህ ብናደርግ ምንም የሚመጣብን ነገር የለም’ በሚል እሳቤ ከድርጊቱ ከመቆጠብ ይልቅ በዚህ አሳፋሪ ተግባር ውስጥ በግልፅ ሲሳተፉ እንመለከታለን።

ከውሳኔዎች በኋላ በሚኖሩ ቅፅበቶች አንዳንድ ተጫዋቾች ዳኛውን ለመተናነቅ ሲቃጣቸው ሌሎቹ ደግሞ ለመገፍተር ሲሞክሩም አሁንም እየተመለከተን እንገኛለን። በመሆኑም ጨዋታን የሚመሩ ዳኞች ተጫዋቾች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማስቻል ድርጊቱን የሚፈፅሙ ተጫዋቾቹን በካርድ መቅጣት የግድ ይላቸዋል።

በተጨማሪም በክለብ ደጋፊዎች ዘንድ በመሰል ድርጊት የሚሳተፉ ተጫዋቾችን ለክለብ ተቆርቆሪ እና ጠበቃ አድርጎ በመቁጠር ረገድ የሚታየው የተሳሳተ እስቤ ተጫዋቾችን ላልተፈለገ “ጀግንነት” የሚገፋፋ በመሆኑ ደጋፊዎች ተጫዋቾች በመጨረሻም ክለቡን ሊጎዳ በሚችል ድርጊት ውስጥ እንዳይካፈሉ መገሰፅ እንኳ ባይቻል ይህን ድርጊት ባለማበረታት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

👉 የአዳዲስ የጨዋታ ተንታኞች

በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ወቅት አዳዲስ የጨዋታ ተንታኞችን በብዛት እየተመለከትን እንገኛለን።

እስከ አምስተኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አማካይ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ የሆነው ዕድሉ ደረጀ እንዲሁም የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አማካይ የነበረው ሚካኤል ወልደሩፋኤልን በጨዋታ ተንታኝነት የተመለከትን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ተንታኞችን ተመልክተናል።

የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ተጫዋች ግሩም ባሻዬ፣ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቪዲዮ ትንተና ባለሙያ የሆነው ኤልሻዳያ ቤከማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በጨዋታ ተንታኝነት ሀሳቦችን ሲሰጡ ተከታትለናል።

አዳዲስ ሀሳብ ያላቸው እና የቀድሞው የእግርኳስ ተጫዋቾችን በተንታኝነት ከስክሪን ፊት እንዲቀርቡ በኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር እና በመልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው።