ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የስድስተኛ ሳምንት ምርጥ 11

በጥቅሉ ደካማ በነበረው ስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን ያካተትንበት ምርጫችንን እነሆ !

አሰላለፍ 3-2-3-2

ግብ ጠባቂ

ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ

በአምስተኛው ሳምንት ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ይተካተተው ዳንኤል ተሾመ በዚህ ሳምንትም ቦታውን አስከብሯል። እንደ ግብ ጠባቂው የዕለቱ ብቃት ባይሆን ኖሮ ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታውን በጊዜ በሁለት ግብ ልዩነት መምራት በቻለ ነበር። ዳንኤል የተስፋዬ አለባቸውን የርቀት ሙከራ እና የዑመድ ዑኩሪን ፍፁም ቅጣት ምት ያዳነባቸው ቅፅበቶች ቡድኑ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑ ነበሩ። ዳንኤል ከወልቂጤው ሲልቪየን ግቦሆ እና ፅዮን መርዕድ ጋር ተቀራራቢ አቋም ቢያሳይም የፍፁም ቅጣት ማዳኑ በሳምንቱ ምርጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ተከላካዮች

ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

ሚሊዮን አዳማ ሲዳማ ቡናን በገጠመበት ጨዋታ የቀኝ መስመር ተከላካይ በመሆን መልካም አፈፃፀም አሳይቷል። ከመከላከሉ ባለፈ በማጥቃት ላይ የነበረው ተሳትፎ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ ሙከራ እስከማድረግ የደረሰ ሲሆን በመሀል ተከላካይነትም መጫወት መቻሉን ከግምት በማስገባት በመረጥነው አሰላለፍ ከሦስቱ ተከላካዮች ውስጥ በቀኝ በኩል ያለውን ቦታ ሰጥተነዋል።

ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በውጥ አቋሙ የሚታወቀው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ቡድኑ ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት መመለሱ የተመቸው ይመስላል። በዋና ኃላፊነቱ በተለይ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከሀዋሳ ከተማ የደረሰበትን ጫና እንዲቋቋም ጥሩ የተንቀሳቀሰ ሲሆን ቀጥተኛ ማጥቃትን ለማድረስ የሚረዱ ኳሶችን ወደፊት መስመር ይልክ የነበረበት መንገድም ዓይን የሚገባ ነበር።

መልካሙ ቦጋለ – ወላይታ ድቻ

አምና በወላይታ ድቻ ቡድን ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው ወጣቱ ተከላካይ ዘንድሮም በዛው አቋሙ ገፍቶበታል። በጉዳት እና በሌሎች ምክንያቶች መነሻነት ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ብቅ በማለት ከበረከት ወልደዮሐንስ ጋር በፈጠረው ጥምረትም ከኋላ ቡድኑን በብስለት በመምራት ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ግብ እንዳይቆጠርበት ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

አማካዮች

አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሀዋሳ ከተማን ለቆ ባህር ዳርን የተቀላቀለው ቁመታሙ አማካኝ አለልኝ ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋር ላይ የሁለት ለምንም ድል ሲያገኝ የነበረው ተሳትፎ ድንቅ ነበር። በ4-4-2 ዳይመንድ ፎርሜሽን ወደ ሜዳ በገባው ቡድን ውስጥ የግራውን ጫፍ ይዞ ከሳጥን ሳጥን የመሮጥ ፍቃድ ተሰጥቶት ሲጫወት የነበረው ተጫዋቹ በአይደክሜ ባህሪው ቡድኑ በመሐል ሜዳው ላይ ጠጣር እንዲሆን ሲያደርግ ነበር።

አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከተማ

እንደ አለልኝ ሁሉ ባሳለፍነው የዝውውር መስኮት አዳማን የተቀላቀለው አማኑኤል ጎበናም ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ የማጥቃት እንቅስቃሴውን በማስጀመር እና ራሱ በመሳተፍ ያደረገው እንቅስቃሴ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል። የአቻነቱንም ግብ በግንባር አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም በጨዋታው ግማሽ ሰዓት አካባቢ ሌላ ኳስ ወደ ግብ ልኮ የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሌላኛው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ የተካተተው የመስመር ተጫዋች አቤል ያለው ነው። በጨዋታ መሐል በግራ እና በቀኝ መስመር ቦታዎችን እየቀያየረ ታታሪነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አቤል ሁለቱ የቡድኑ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበር ፤ አንዱን በቀኝ አንዱን ደግሞ በግራ መስመር በኩል በመገኘን አመቻችቶ በማቀበል። ጎሎቹ በጨዋታው ውጤት ቀያሪ ከመሆናቸው መነሻነት በቀኝ መርመር በኩል ቦታ ሰጥተነዋል።

ሮቤል ተክለሚካኤል – ኢትዮጵያ ቡና

ሌላ ከሳጥን ሳጥን በመሮጥ የተዋጣለት የነበረው አማካኝ የኢትዮጵያ ቡናው ኤርትራዊው ተጫዋች ሮቤል ተክለሚካኤል ነው። እንደ አማኑኤል ሁሉ የዘገዩ የሳጥን ሩጫዎችን በተደጋጋሚ በጥሩ የሰዓት አጠባበቅ ሲያደርግ የነበረው ሮቤል ብቸኛዋ ቡናን አሸናፊ ያደረገ ጎል ለዊልያም ሰለሞን አመቻችቶ ከማቀበሉ በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽም ቡድኑ ጥቃቶች በበረከቱበት ጊዜ ወደ ኋላ እየተመለሰ የተከላካይ ክፍሉ እንዳይጋለጥ ሲጥር ነበር።

ዊሊያም ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን እንዲያገኝ የዊልያም ሰለሞን ጎል አስፈላጊ ነበረች። ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በመሐል ሜዳው ላይ የተሰጠውን ነፃ ኃላፊነት በሚገባ ሲወጣ የነበረው ተጫዋቹ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጠጣሩን ቡድን ለማስከፈት ሲጥር ነበር። በዋናነት ደግሞ በመስመሮች መካከል እየተገኘ የመጨረሻ ኳሶችን ለማመቻቸት ሲጥር ነበር። ምንም እንኳን ዊልያም የአማካይ መስመር ተጫዋች ቢሆንም በምርጥ ቡድናችን ወደ ግራ ያዘነበለ ቦታ ሰጥተነዋል።

አጥቂዎች

ዓሊ ሱሌይማን – ባህር ዳር ከተማ

ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ወደ ሜዳ የገባው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ በጅማው ድል ቁልፍ ድርሻ ነበረው። ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ ሲጫወት የነበረውን የጅማን የኋላ መስመር ጀርባም በፈጣን ሩጫዎቹ አጥቅቶ ሁለት ጎሎችን ለቡድኑ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎችም ራሱን ነፃ አድርጎ በተጋጣሚ ሳጥን እየተገኘ ለመጠቀም ሲሞክር ታይቷል። ከፍጥነቱ፣ ከቦታ አያያዝ ብቃቱ እና አጨራረሱ መነሻነትም የምርጥ ቡድናችንን የፊት መስመር እንዲመራ አድርገነዋል።

እስማኤል አውሮ-አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወደ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የተሸጋገረበትን ምርጥ ሳምንት ያሳለፈው እስማኤል አውሮ-አጎሮ ጊዮርጊስ ሀዋሳን ሲያሸንፍ ሁለቱንም ጎሎች አስቆጥሯል። በተለይ ደግሞ የመጀመሪያውን ጎል በግራ እግሩ ከመረብ ያዋሀደበት መንገድ ምርጥ የሳጥን ውስጥ አጥቂ እንደሆነ ያስመሰከረ ነበር። ከዚህ ወጪ በተሻለ ራስን ነፃ የማድረግ ቦታ አያያዝ ላይ ሆኖ የግብ ዕድሎችንም ለመፍጠር የጣረበት ሂደት የሚደነቅ ነበር።

አሰልጣኝ  – ዘሪሁን ሸንገታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲሱን የውድድር ዓመት ከሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ጋር ቢጀምርም አሰልጣኙ ሁሉንም ጨዋታዎች አልመሩም። በእነዚህ ሳምንታት ቡድኑን ይዘው ወደ ሜዳ ሲገቡ የነበሩት ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ከሰርቢያዊው አሰልጣኝ ስንብት በኋላም በስድስተኛው ሳምንት ፈረሰኞቹን ለድል ያበቁበትን ጨዋታ መርተዋል። የቀደመውን ጊዜ በሚያስታውስ መልኩ ቀጥተኛ አጨዋወትን የሚተገብር ቡድን አሳይተውም ተፈላጊውን ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ተጠባባቂዎች

ሲልቪያን ግቦሆ – ወልቂጤ ከተማ
ልመንህ ታደሰ – አዲስ አበባ ከተማ
ደስታ ዮሀንስ – አዳማ ከተማ
ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ
አብዱልከሪም ኒኪማ – ባህር ዳር ከተማ
የአብቃል ፈረጃ – ኢትዮጵያ ቡና
ቢኒያም በላይ – መከላከያ
ሪችሞንድ ኦዶንጎ – አዲስ አበባ ከተማ