በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ለአፍሪካ ዋንጫ በቂ ዝግጅት ሲባል ሊጉ እንዲቋረጥ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሩን አስተናጋጅነት ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ መደረግ ይጀምራል፡፡ በዚህ አህጉራዊ ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በኋላ ተካፋይ ትሆናለች፡፡ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው የሚመራው ይህ የዋልያዎቹ ስብስብ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የነበረውን ተሳትፎ በተመለከተ እና ከፊቱ ለሚጠብቀው የአፍሪካ ዋንጫ በምን አይነት መልኩ ሊዘጋጅ ይገባዋል በሚል እና የብሔራዊ ቡድን ጠንካራ አቋም እንዲሁም ደካማ ጎኑን የተንተራሰ መፍትሔዎች በሚሉ ጉዳዮች ላይ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና የፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞች በጋራ በመሆን ዛሬ ዕሮብ አመሻሽ ከ11፡30 ጀምሮ በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ መጀመሪያ ላይ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዓለም ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጉዞን የተመለከተ አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ አሰልጣኙ በዋናነት ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑ በምን አይነት መልኩ መዘጋጀት ይኖርብናል፣ የዝግጅት ቀን ማነስ የሚያስከትለውን ተፅእኖ እንዳለ እና ለዝግጅት አስር ቀናት ብቻ መኖራቸው ተጫዋቾቹን ለማቀናጀት በቂ አለመሆኑን እንዲሁም ደግሞ ተጫዋቾች በየክለባቸው እያሉ የክትትል ስራዎች በህክምና እና በአካል ብቃት ባለሙያዎች እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ በመጨረሻም ከምድብ ማለፍ እና ወደ አስራ ስድስቱ ውስጥ መግባት እንደ ግብ ያስቀመጡት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠል የፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞች በተነሱ ሀሳቦች ላይ ግብአት የሚሆኑ እና ቡድኑን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችሉ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በስነ ልቦናው ፣ በወዳጅነት ጨዋታ ፣ የቀድሞው ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑ ላይ መጥተው ማበረታታት እንዴት አለባቸው እንዲሁም ደግሞ በተለይ በፕሪምየር ሊጉ ውድድር ላይ በቂ የልምምድ ሜዳ አለመኖሩ በብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ የታክቲክ ክፍተት ያስከትላል ሲሉ ተደምጠዋል። በተለይ ደግሞ ለብሔራዊ ቡድኑ በቂ ዝግጅት ሲባል ከሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ፕሪምየር ሊጉ ሊቋረጥ ይገባል የሚል የፀና አቅጣጫን አስቀምጠዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ፣ ጳውሎስ ጌታቸው እና ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እንዳሉት “አስር ቀን ብቻ ለብሔራዊ ቡድኑ በቂ አይደለም። ለዚህም ሲባል ከሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ሊጉ ሊቋረጥ ይገባዋል። ይሄ ውድድር ለመመለስ ስምንት ዓመት የፈጀ ነው፡፡ለዚህ ዝግጅት ደግሞ ሊጉ መቋረጥ እና በቂ ጊዜ መሰጠት አለበት። ይህ የሀገር ጉዳይ ማለት የሁላችን ጉዳይ ነው” በማለት አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡ አስራ ስድስቱም አሰልጣኞቹ በነገው ዕለት በደብዳቤ ውሳኔውን ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ካቀረቡ በኋላ ለፌዴሬሽኑ እና ለሊግ ካምፓኒው እንደሚያስገቡ በአንድ ድምፅ ወስነው ተለያይተዋል፡፡
የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ስነ ስርአት ሰብሳቢው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ በውይይቱ ላይ ተገኝተው እንዳሉት “እንደ ሀገር ይህ ጉዳይ ይመለከተኛል። ሊጉ ይቋረጥ ሲባል ግን ህጋዊ ጥያቄ መሆን አለበት። ውድድሩ ሳይጀምር በፊት ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ልከን ነበረ። በዛን ወቅት መቋረጥ ያለበትን ወቅት አልገለፁልንም። እነሱም ጋር ክፍተት ነበር። እኛ ግን እንደ እቅድ ዘጠነኛ ሳምንት ላይ መቋረጥ አለበት ብለን ነው አቅጣጫ ያስቀመጥነው።” ሲሉ የገለፁ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ሊጉ ከሰባተኛ ሳምንት ወይንስ ከዘጠነኛ ሳምንት በኋላ ይቋረጣል የሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መጨረሻም ተጨማሪ ሀሳቦች ከተነሱ በኋላ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡