የሰባተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ-ግብርን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
በሊጉ የመክፈቻ ሁለት ጨዋታዎች ካስተናገዱት ሽንፈት ውጪ ለአንድም ቡድን እጅ ያልሰጡት አዲስ አበባዎች በሚጓዙበት መልካም ጎዳና ለመዝለቅ እና ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይጠብቃሉ።
ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ የሚገኘው የመዲናው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ በተጫዋቾቹ ላይ ከሚስተዋለው ተነሳሽነት ባለፈ በቡድናዊ አጨዋወት በአራቱም የሜዳ ክፍሎች እድገቶችን እያመጣ ይገኛል። በዋናነት በመከላከል ላይ የተንተራሰው የቡድኑ አጨዋወትም በሁሉም የሜዳ ላይ ተጫዋቾች የሚተገበር ሲሆን በማጥቃቱም በኩል ፈጣን የሽግግር እንቅስቃሴ እና ረጃጅም ኳሶችን በመከተል ተጋጣሚን ሲያስጨንቅ ይታያል። በተለይ ደግሞ የመሐል አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ ለቀጥተኛ አጨዋወት ምቹ መሆን እና የመስመር አጥቂዎቹ ፍጥነት (ፍፁም እና እንዳለ) ለቡድኑ የፊት መስመር አንዳች ነገር እንደጨመረ በሚገባ ይታያል። ምናልባት ነገ ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ከከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎቹ የተሻለ ነገር እንደሚያሳይ ቢጠበቅም ዘለግ ያለውን እንቅስቃሴ ግን እንደተለመደው ከኳስ ውጪ በመሆን ፈጣን ጥቃቶች ላይ ጥገኛ በመሆን ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።
በአምስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር እየተጫወቱ መሪ የሆኑበትን ጎል በ45ኛው ደቂቃ አስቆጥረው የነበረው አዲስ አበባዎች ከግቡ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የመረጡት ማፈግፈግ የተሞላበት አጨዋወት የኋላ ኋላ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ይታመናል። ይህ ጨዋታን የመቆጣጠር ስልት ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት በተወሰነ ደረጃ ትምህርት ተወስዶበት ሻል ብሎ ታይቷል። ከዚህ ውጪ የወቅቱ የሊጉ ምርጥ የግብ ዘብ እየሆነ የመጣውን ዳንኤል ተሾመ የያዘው ቡድኑ ካለው ስብስብ አንፃር የኋላ መስመሩ ለክፉ የሚሰጥ ብቃት ባያሳይም የግብ ዘቡን የሚያጋልጡበት ክፍተት ላይ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቅባቸው መናገር የግድ ይላል። ከላይ ከጠቀስነው ቀጥተኛ አጨዋወት በተጨማሪም ወደ ግራ ባደላው (ፍፁም በተሰለፈበት) የማጥቃት ሀይላቸው ነገም ወልቂጤን ሊፈትኑ እንደሚችሉ ይታሰባል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከተጫዋቾች የደሞዝ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ የነበረው ወልቂጤ ከሜዳ ውጪ ካጋጠመው አስተዳደራዊ ችግር ጋር እየተጋፈጠም ቢሆን ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ የዓመቱ ሦስተኛ ድሉን ለማግኘት ነገ አዲስ አበባን መርታት የግድ ይለዋል።
በአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው የሚመራው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በርከት ያሉ ቋሚ ተሰላፊዎቹን ሳያገኝ ወደ ሜዳ ቢገባም ለክፉ የሚዳርገው ውጤት አላስመዘገበም ነበር። ምንም እንኳን ቡድኑ ያልተሟላ ስብስብ ይዞ በ4 ተጠባባቂ ተጫዋቾች ብቻ ወደ ሜዳ ቢገባም በመከላከሉ ረገድ ብዙ ያጎደለው አይመስልም ነበር። በተለይ ደግሞ በጥሩ ተነሳሽነት በመጫወት ክፍተቶችን ለመዝጋር ሲሞክሩ እና የአርባምንጭ ተጫዋቾች ምቾት እንዳይሰማቸው ሲያደርግ ተስተውሏል። ይህ ተነሳሽነት እንዲቀጥል ሲጠበቅ ልምምድ ያቆሙት ወሳኞቹ 9 ተጫዋቾች ጥያቄያቸው በመጠኑ በመመለሱ ልምምድ መጀመራቸው አዎንታዊ ዜና ነው።
ከላይ እንደጠቀስነው ቡድኑ ሙሉ ስብስቡን አለማግኘቱ በመከላከሉ ረገድ አምብዛም ባያጋልጠውም በማጥቃቱ ላይ ግን መሳሳት አስከትሎበት ነበር። በዋናነት ደግሞ በማጥቃቱ ላይ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ተጫዋቾችን ይጠቀም በመሆኑ እና በጨዋታው እነሱ ባለመኖራቸው ነው። ይህ ባለመሆኑ ደግሞ ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ባህሪ ተላብሶ እንዲጫወት አድርጎታል። እንደተባለው ተጫዋቾቹ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለቀናት ከመደበኛ ልምምድ በመራቃቸው ምክንያት ሁሉም የመጀመሪያ ተመራጭ ሆነው ወደ ሜዳ ላይገቡም ይችላሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ በተወሰነ መልኩ እንደ አርባምንጩ ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ላይ የተንተራሰ ግብ የማግኛ ስልት ሊቀይሱ እንደሚችሉ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ሊጉን በፍጥነት የተላመደው ዋሀብ አዳምስ እና ዳግም ንጉሴ ነገ አለመኖራቸው በተከላካይ መስመሩ ላይ አዲስ ጥምረት ልንመለከት እንገደዳለን።
በአዲስ አበባ በኩል ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ፈይሰል ሙዘሚል እና ነብዩ ዱላ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ነገ ቡድናቸውን አያገለግሉም። ወልቂጤ ከተማ ደግሞ እንደጠቀስነው ዘጠኙን ተጫዋቾች ሲያገኝ ዋሀብ አዳምስ ቀለል ያለ ጉዳት በማስተናገዱ ዳግም ንጉሴ ደግሞ በግል ሀዘን ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን የሚገናኙበትን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በአልቢትርነት የምትመራው ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመንህ ታደሰ – ሳሙኤል አስፈሪ – ያሬድ ሀሰን
ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙለቀን አዲሱ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ስልቪያን ግቦሆ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዮናስ በርታ – አበባው ቡጣቆ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታናህ ከበደ – እስራኤል እሸቱ