ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹ ወደ ልምምድ ተመልሰዋል

ለኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣርያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹ ከጉዳት ተመልሰውለታል።

ኮስታሪካ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ ሁለት ሀገራትን ለመለየት በሦስተኛ ዙር ማጣርያ ወደ ቦትስዋን አቅንቶ 3-1 ያሸነፈው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኃላ የሁለት ቀን እረፍት አድርጎ መስቀል ፍላወር በሚገኘው 35 ሜዳ ለሁለት ቀናት ያህል ልምምዳቸውን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ባረፉበት የካፍ የህልቀት ማዕከል ሜዳ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ተመልክተናል።

ባለፈው ዘገባችን ወቅት ሦስት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መጠነኛ ጉዳት አስተናግደው ልምምድ እንዳልሰሩ ገልፀን ከነበሩት መካከል ረድኤት አስረሳኸኝ እና ናርዶስ ጌትነት ከትናንት ጀምረው ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ልምምድ መጀመራቸውን ተመልክተናል። በአንፃሩ የሴካፋው ኮከብ ተጫዋች ብርቄ አማረ እስካሁን ወደ ልምምድ ያልተመለሰች ሲሆን ምን አልባትም በቀጣዮቹ ቀናት ቡድኑን በመቀላቀል ወደ መደበኛ ልምምድ እንደምትመለስ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ምክትል አሰልጣኟ ቡዛየሁ ጀምበሩ ከትናንት ጀምሮ ቡድኑን ተቀላቅላ እየሰራች እንደሆነች ስንመለከት የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ ረፋድ ላይ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ተነግሯል። ልምምዱን አጠናክሮ የቀጠለው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዕለተ አርብ ታህሳስ 8 ቀን የመልሱን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል።