ሪፖርት | ሠራተኞቹ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ አዲስ አበባን ረተዋል

ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው የሰባተኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በአምበሉ የግንባር ኳስ አዲስ አበባን አሸንፎ በጊዜያዊነት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ሀዲያ ሆሳዕናን በሪችሞንድ አዶንጎ ብቸኛ ግብ አሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት አዲስ አበባዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሙሉቀን አዲሱን ብቻ በብዙዓየሁ ሰይፉ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አቻ ተለያይተው ለዛሬው ፍልሚያ የተዘጋጁት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ከክፍያ ጋር ተያይዞ አተዋቸው የነበሩትን ተስፋዬ ነጋሽ፣ ሐብታሙ ሸዋለም፣ በሃይሉ ተሻገር፣ ያሬድ ታደሰ፣ እስራኤል እሸቱ እና ዮናስ በርታን መጠነኛ ጉዳት ባስተናገደው ዋሃቡ አዳምስ፣ ዮናታን ፍሰሃ፣ ፍፁም ግርማ፣ ፋሲል አበባየሁ፣ ጫላ ተሺታ እና አላዛር ዘውዱ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታው ገና እንደተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ተፈጥሮበታል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተስፋዬ ነጋሽ ከአዲስ አበባ ተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን በረጅም የተላከ ኳስ ከግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመ ቁመት በላይ አሳልፋለው ሲል ሳይሳካለት ቀርቶ አጋጣሚው መክኗል። የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተጫወቱት ወልቂጤዎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ከመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ በአብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት ጥቃት ፈፅመው ነበር።

ረጃጅም ኳሶችን እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለግብ ማስቆጠሪያነት ሲጠቀሙ የነበሩት አዲስ አበባዎች በአንፀሩ እስከ 40ኛው ደቂቃ ድረስ ሲልቫይን ግቦሆን አልፈተኑም። ነገር ግን ከደቂቃ ደቂቃ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የወልቂጤን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጋብ ለማድረግ ጥረዋል። ከላይ በተጠቀሰው አርባኛው ደቂቃ ላይ ከወደ ቀኝ የተሻገረን የቅጣት ምት ግቦሆ በሚገባ ሳያፀዳው ቀርቶ ኤሊያስ አህመድ አግኝቶት ሊጠቀምበት ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ለቅጣት ምቱ መገኘት ምክንያት የነበረው ፍፁም ጥላሁን ከመሐል የተላከውን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ረመዳን እና አበባውን አቅጣጫ ካሳተ በኋላ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም በአስቆጪ ሁኔታ ኳሱን አምክኖታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ አጀማመራቸው ጥሩ የነበረው ወልቂጤዎች አፈፃፀማቸውንም ጥሩ በማድረግ ያገኙትን የቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይረውታል። በዚህም ሀብታሙ ሸዋለም የመታውን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት አዲስ አበባዎች በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቶሎ ወደ ጨዋታው የሚመጡበትን ግብ ፍለጋ የተጫዋች ለውጦችን አድርገው የተሻለ ለመጫወት ሞክረዋል። በ55ኛው ደቂቃም ከአሠልጣኝ ደምሰው ቅያሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ሳሙኤል ተስፋዬ የመዓዘን ምት ተመቶ ግብ ጠባቂው ሲልቫይን ሲተፋው ከሳጥኑ ጫፍ አግኝቶ ቡድኑን አቻ ለማድረጊያነት ሊጠቀመው የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወጥቶበታል።

በወጥነት ጨዋታውን ማድረግ የተሳናቸው ወልቂጤዎች መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል ቢያመሩም ከእረፍት መልስ የማጥቃት ፍላጎታቸው ትንሽ ቀዝቀዝ ብሎ ታይቷል። በተቃራኒው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፈው ላለመስጠት በራሳቸው ሜዳ ሰብሰብ እያሉ አዲስ አበባዎች ብቻ ሊያጠቋቸው ሲመጡ ከጀርባቸው የሚገኘውን ሰፊ ቦታ በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል።

አሁንም አቻ ለመሆን መንቀሳቀስ የቀጠሉት የአሠልጣኝ ደምሰው ተጫዋቾች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በቅድሚያም በ79ኛው ደቂቃ የሺዋስ ላይ የተሰራን ጥፋት ተለትሎ የተገኘን የቅጣት ምት አሰጋኸኝ ወደ ግብ ሲመታው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዋለልኝ ከረጅም የተላከን ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮች ሲመልሱት ከሳጥን ውጪ ዐየር ላይ አግኝቶ ወደ ግብ ልኮት ነበር። ነገርግን አሰጋኸኝ የመታውን ኳስ ሲልቫይን ሲቆጣጠረው ዋለልኝ የላከው ኳስ ደግሞ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግን ሌላ የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ በጨዋታው እጅ ሰጥተው ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያጋጠማቸው አዲስ አበባዎች አስር ነጥቦች ቢኖራቸውም ተጋጣሚያቸው ደረጃ ማሻሻሉን ተከትሎ ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ሸርተት ብለዋል። ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በጊዜያዊነት ከስምንተኛ ወደ ሁለተኛ ደረጃ (በ12 ነጥቦች) የተመነደጉበትን ውጤት ይዘው ወተዋል።