የአሠልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ወልቂጤ ከተማ

በወልቂጤ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነተረ ከተጠናቀቀው የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ብድን አሠልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ማዕዘን ምት አጠቃቀማቸው

ማዕዘን ምት ላይ እንዳልሰራን ዛሬ ተገንዝቤኣለሁ። አሻምተህ ብቻ ጎል መጠበቅ ስህተት ነው። የኛ ተጫዋቾች ደሞ አብዛኛዎቹ አጫጭሮች ናቸው። በነ ጌታነህ እና እስራኤል ነው ልንጠቀም የምንችለው። ለሚቀጥለው አንድ መላ እንዘይዳለን።

ግልፅ የማጥቃት እቅድ ስለመያዙ

ከዚህ በፊትም ከቡድናችን አንድ ነገር ጠብቁ ብዬ ተናግሬያለሁ። ቡድናችን ቅርፅ እየያዘ ነው። በአማካዮችም ሆነ ፊት ላይ ባሉት ጌታነህ እና እስራኤል ጥምረት ደስተኛ ነኝ ። ከኳስ ጋርም ሆነ ያለ ኳስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ሆኖ እየተመለከትኩ ነው።

ስለ ጌታነህ ከበደ

ከተጫዋቾቹ ጋር የመግባባት ነገር መጥቷል። እዛው ሳጥን ውስት እንዲቆም ብናደርገው ብዙ ጎል እንደሚያገባ እናውቃለን። ነገር ግን ወደ ኋላ ሲመለስ የአማካይ ቁጥር ስለሚያበዛ እና ተደርቦ መጥቶ አደጋ መፍጠር እንደሚችል ስለምናውቅ ነው። ጌታነህ በአሁኑ ወቅት ቡድናችንን እየመራ መንፈሱ እና ስነልቦናው ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ እያደረገ ነው።

ከተሻጋሪ ኳሶች ጎሎች እያስቆጠሩ ስለመሆኑ

ከዚህ በፊት አብዱልከሪም ያገባውም በእንቅስቃሴ የገባ ነው። ቅጣት ምት ሲገኝም እነ ጌታነህ ጥሩ ነው የሚጠቀሙት። እነ ያሬድ ተጫውተው መግባት ይችላሉ። አሁንም መናገር የምፈልገው ቡድኑ ይበልጥ እየተብላላ ሲሄድ ከዚህ በላይ ጥሩ ቡድን እንደሚሆን ጠብቁ ነው።

ስለ አበባው አጠቃቀም

ጉዳቶች እና ሌሎች ነገሮች አሉ። እነ ዳግም በሀዘን እነ ዋሃቡ በጉዳት የሉም ነበር። ሲጀምር እዚህ ነው ብሎ የሚመረጥ ተጫዋጭ የለም። ልምምዱን በደንብ የሰራ እና ጥሩ እረፍት ያረፈ ማንኛውም ተጫዋች የትም መጫወት ይችላል። ስለዚህ እኔ ስለ ቦታ ብዙ አልጨነቅም።

ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ስለ ውጤቱ?

ይህ እግርኳስ ነው። የመጣውን ነገር በፀጋ እንቀበላለን። ወደ ሜዳ ስትገባ የምታቅደው በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ላይሳካ ይችላል። ይህንንም እንቀበላለን።

ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ስለነበረው ክፍተት?

የመከላከል አደረጃጀቱ ላይ ክፍተቶች አሉ። የመግባባት ችግርም አለ። ይህንን በስራ አስተካክለን ለመምጣት እንጥራለን።

የግብ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ስለጣሩበት መንገድ?

ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ሳንጠቀም ቀርተናል። እንጂ በተደጋጋሚ ወደ ጎል ስንደርስ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከተጫዋቾች ብስለት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ነገሮች ናቸው። የተሻለ ቦታ ላይ ያለን ተጫዋች አይቶ ማቀበል እየተቻለ በግል የሚሞከሩ ነበሩ። ይህ ትንሽ ቡድናችን ግብ እንዳያገኝ አድርጎታል። ይህንን በስልጠና እንቀርፋለን።

በጨዋታው ስላደረጋቸው የተጫዋቾች ቅያሪዎች ውጤታማነት?

ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበሩ። ዛሬ ትንሽ ቡድናችን የመፍዘዝ ባህሪ ነበረው። ይህ እግርኳስ ነው። ያለፉትን ጨዋታዎች ጥሩ ነበርን። ዛሬ ትንሽ ፈዘዝ ብለናል። ይህ ግን የሚያጋጥም ነው።

ውጤቱ በቀጣይ ጨዋታዎች ስለሚኖረው ተፅዕኖ?

አይ ተፅዕኖ አያመጣም። እግርኳስ ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣት አለው። ይህንን ተቀብለን ሁሉንም ነገር እንደየአመጣጡ ማስተናገድ ነው የሚሻለው።

ፍፁም ጥላሁን አግኝቶት ስላልተጠቀመበት የግብ ማግባት አጋጣሚ?

አለመረጋጋት እና የትኩረት ማነስ ትንሽ ከባድ ነው። ይህ ከማግባት ይልቅ ለመሳት የሚከብድ ኳስ ነበር። ግን ይህ ኳስ ነው። ያጋጥማል። ይህንንም አሻሽሎ ግቦችን ያገባል ብዬ አስባለሁ።