በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የዕለቱን ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡና ላይ ከፍተኛ ብልጫ በመውሰድ አራት ለምንም አሸንፏል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ ጋር ያለ ጎል ተለያይተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ፋሲል ከነማዎች አንድ ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ ፍቃዱ ዓለሙን በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም ከድር ኩሊባሊን በያሬድ ባየህ ተክተዋል። እንደ ፋሲል ሁሉ ባሳለፍነው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ተፋልመው አንድ ነጥብ ያገኙት ሲዳማ ቡናዎችም በተመሳሳይ ዳዊት ተፈራን በሙሉዓለም መስፍን አማኑኤል እንዳለን በምንተስኖት ከበደ ለውጠው ጨዋታውን ለመጀመር ሜዳ ገብተዋል።
ገና ከጅምሩ ቀልብን ሳቢ እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው ጨዋታ በጊዜ መሪ አግኝቷል። በዚህም ጨዋታው በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ያገኘውን የመዓዘን ምት ፍሬያማ አድርጎ መሪ ሆኗል። በዚህም ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ዓለምብርሃን ይግዛው መሬት ላይ ደገፍ በማረግ ግብ አድርጎታል። የግቡ ባለቤት ዓለምብርሃን ከአምስር ደቂቃዎች በኋላም ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ ሊያስቆጥር ከጫፍ ደርሶ ነበር። በተረጋጋ ሁኔታ መጫወት ያልቻሉት ሲዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሁሉም መስፈርቶች ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። ይባሱኑ በደቂቃ ልዩነት ሁለት ተጨማሪ ግቦችን አስተናግደዋል።
በጥሩ ተነሳሽነት እየተጫወቱ የሚገኙት ፋሲሎች 16ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን በግራ መስመር ፈጣን ሩጫ በማድረግ ከበረከት ደስታ ጋር የተናበበ አጨዋወት በመጫወት ሳጥን ውስጥ በመገኘት በግራ እግሩ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ከፍ አድርገዋል። ሁለተኛ ግብ የተቆጠረባቸው ሲዳማዎች ኳሱን ወዲያው ጀምረው ለመቀባበል ሲሞክሩ ሁለተኛውን ጎል አመቻችቶ ያቀበለው በረከት ቅብብላቸውን አቋርጦ ለኦኪኪ አፎላቢ የላከውን ተከላካይ ሰንጣቂ የዐየር ላይ ኳስ ግዙፉ አጥቂ በጥሩ መረጋጋት ከመረብ ጋር አዋህዶታል።
ገና ከጅምሩ ፈተና የጠናባቸው ሲዳማዎች በአስገዳጅ ሁኔታ በ23ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴን በመሐሪ መና ከቀየሩ ከደቂቃ በኋላ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከርቀት በተላከለት እና ለመጠቀም በሞከረው ኳስ ምናልባት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል ሊያገኙ ነበር። ይህ ግብ የማግኘት ፍላጎት በቶሎ ባይሳካላቸውም ቀስ በቀስ የፋሲልን ጥቃት ለመቆጣጠር ተንቀሳቅሰዋል። ሀብታሙ በ24ኛው ደቂቃ ከሞከረው ኳስ ውጪ ግን ሌላ ኳስ ወደ ሜኬል ሳማኪ ሳይልኩ አጋማሹን ሦስት ለምንም እየተመሩ አገባደዋል።
በሁለተኛውም አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ ከባዱን ፈተና በመጋፈጥ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት የሞከሩት ሲዳማዎች ውጥናቸው ሳይሰምር በደካማው የተከላካይ አደረጃጀታቸው በድጋሜ ዋጋ ከፍለው አራተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ሽመክት ከጨዋታ ውጪ እንዳይሆን በጥሩ ቦታ እና ጊዜ አጠባበቅ ላይ ሆኖ ከመሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ የራስ ወዳድነት ስሜት ሳይታይበት ለበረከት አመቻችቶለት ፋሲል መሪነቱን ወደ አራት አሳድጓል።
ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ በሲዳማ በኩል ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ተስተናግዷል። በዚህም ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ከመሐል ከቴዎድሮስ የተላከለትን ኳስ ግቡን ለቆ ከወጣው ሳማኬ ጀርባ አግኝቶት የነበረ ቢሆንም ማስተዛዘኛ እንኳን የምትሆነዋን ጎል ሳያስቆጥራት ቀርቷል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ከቴዎድሮስ እግር የተነሳን የመዓዘን ምት በብሩክ አማካኝነት ለመጠቀም ጥረው መክኖባቸዋል። የሚፈልጉትን እምብዛም ሳይቸገሩ ያገኙት ፋሲሎች በ77ኛው ደቂቃ አምስተኛ ግብ በኦኪኪ አማካኝነት ሊያገኙ ቢሉም ተክለማርያም ሙከራውን አምክኖታል። ጨዋታውም በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በፋሲል አራት ለባዶ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
በውጤቱ መሠረት ጣፋጭ ድል ያገኙት ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን አስራ አራት በማድረስ በጊዜያዊነት የሊጉን መሪነት ከወላይታ ድቻ ተረክበዋል። ሦስት ነጥብ እና አራት የግብ ክፍያ በዛሬው ጨዋታ ለፋሲል የሰጡት ሲዳማዎች ደግሞ ሰባት ነጥብ ቢኖራቸውም የግብ ዕዳቸው ሁለት በመሆኑ ከአስራ አንደኛ ወደ አስራ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።