👉”አንድ የማልዋሸው ነገር መሸነፍ አይደለም አቻ ብንወጣ ሁላችንም የሚሰማን ስሜት ነበር” ሥዩም ከበደ
👉”..ስለዚህ የፈለገውን እርምጃ ቢወስዱብኝ ምንም ችግር የለውም።… በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ መስራትም ከባድ ነው የሚመስለኝ።” ገብረመድህን ኃይሌ
አራት ግቦች ከተስተናገዱበት የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከቡድኖቹ ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።
ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ጨዋታው እንዴት ነበር?
መጀመርያም እንደተናገርኩት ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ላይም የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። አጨራረስ ላይ እና የተጋጣሚ ሦስተኛ አጋማሽ ላይ የነበረን ነገር ነው ሰንካላ የነበረው። ያንን ለማሻሻል በሜዳም ሆነ በክፍል ውስጥ ስንዘጋጅ ሳምንቱን ያሳለፍነው። በመስመርም ሆነ በመሀል እንገባለን፥ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረግነው ነገር ጥሩ ነው። ትልቅ የምናለቸው እንደነ ሱራፌል እና በዛብህ ሜዳ ውስት ሳይኖሩ ገብተው የሚጫወቱ ተጫዋቾች የቡድኑን ደረጃ እየጠበቁ ነው። እነ ናትናኤል እና ዓለምብርሃን የወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው። ሌሎቹም ወጣቶች የመጫወት እድል ሲያገኙ ያንን የማስጠበቅ ነገር ስናይ የፋሲልን ትልቅነት ኣሳያል። በአጠቃላይ ዛሬ በጣም ወሳኝ ጨዋታ ነበር። ውጤት በማግኘታችን ተደስቻለሁ።
ስለዓለምብርሃን እንቅስቃሴ?
ዓለምብርሀን በኃይል የተሞላ ተጫዋች ነው። ከዚህ በፊት በቀኝ መስመር ማጥቃት ላይ ሲጫወት ነበር። ግን የበለጠ ከኋላ ሲመጣ በጣም አሪፍ ነው። አሁን የሚጎድለው ደፍሮ መሄድ ነው። ቦታ አጠባበቁ እና ፍጥነቱ በጣም መልካም ነገር ነው። ግን ቁርጠኝነት ይፈልጋል። በዚህ ረገድ የሚሻሻል ነው። በጨዋታውም መልካም ነገር ነው ያየሁበት።
በጨዋታው ይዘውት ስለገቡት የተጫዋች አደራደር ቅርፅ?
4-1-4-1 ለማጥቃትም ሆነ ለመከላከል በጣም ተመራጭ ነው። እኛ ደግሞ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደጋግመን ያየነው ነገር ነው። ውጤት ለማስጠበቅ ስንፈልግ ደግሞ ኩሊባሊን እንዳስገባነው ወደ 4-2-3-1 እየቀየርን እናገግማለን። ከተከላካዮች ፊት የተሰለፈው ይሁን ደግሞ በደንብ አድርጎ ነው ቦታውን የሸፈነው። ለቡድኑም ሚዛናዊነት ጥሩ ነው። እነ ኦኪኪም እንደ ዛሬው ወደ ጎል ሲቀርቡ በቀጣይ የተሻሉ ነገሮች ይኖሩናል።
የዛሬው ውጤት ትርጉም?
አንድ የማልዋሸው ነገር መሸነፍ አይደለም አቻ ብንወጣ ሁላችንም የሚሰማን ስሜት ነበር። ምክንያቱም እያራቅን እንሄዳለን። ነጥቦች ደግሞ ተቀራራቢ ስለሆኑ የመጠጋጋት ነገር የኖራል። ስለዚህ ለሚቀጥለው ጨዋታ እየከበደብን ይሄድ ነበር። የዛሬውን ውጤት ማግኘታችን በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ነገር እንዲኖረን ያደርጋል።
ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ጨዋታውን መቆጣጠር ስላልቻሉበት ምክንያት?
ዋናው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተፈጠሩት ክስተቶች ናቸው። መቆጣጠር በማንችልበት ሰዓት ላይ ስህተቶች ፈፅመናል። በተለይ የአማካይ መስመራችን ከተጋጣሚ ቡድን አማካዮች ፍጥነት ጋር መመጣጠን ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ተደጋጋሚ (አንድ አይነት) ክፍተቶች ስንፈጥር ነበር። ከዚህ መነሻነት ጨዋታውን መቆጣጠር አልቻልንም።
በሦስተኛው ደቂቃ የተቆጠረችው ጎል ስለነበራት ተፅዕኖ?
ተፅዕኖ ነበረው። አንደኛ የመዓዘን ምት የተገኘበትን መንገድ ስታየው በራሳችን ችግር የመጣ ነው። እና ያ ጎል በጊዜ መግባቱ ትንሽ። ግን እሱ ገባ ከዛ በኋላ የተፈጠሩት ነገሮች ናቸው ትልቅ ችግር የሆነብን። ይህ እግርኳስ ላይ የሚያጋጣም ነገር ነው። እኛ አጋጥሞናል። ምንም ማድረግ አይቻልም።
ሁለት የተከላካይ አማካዮችን በጨዋታው ስለመጠቀሙ?
በጥንቃቄ መጫወት ነበረብን። ነገርግን ባልጠበቅነው ነገር ስህተቶች አጋጥመውናል። እነዛን ደግሞ መቆጣጠር አልቻልንም። እንጂ ሀሳባችን ጨዋታውን ተቆጣጥሮ መጫወት ነበር።
ተፅዕኖ ውስጥ ስለመግባታቸው
እግርኳስ ላይ በየትኛውም ዓለም አንድ ክለብ ሲገና እንዲባረር ነው። ስለዚህ የፈለገውን እርምጃ ቢወስዱብኝ ምንም ችግር የለውም። እኔ የምቀበለው ነገር ነው። እኔ ግን ምንም ተፅዕኖ የለብኝም። የምታየው ደጋፊ ግን ይላል። እነሱ መብታቸው ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ መስራትም ከባድ ነው የሚመስለኝ።