በኢትዮጵያ እግርኳስ ረጅም ታሪክ ያለው መከላከያ ከሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ጎፈሬ ጋር ለመስራት ቅድመ ስምምነት አድርጓል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ አስራ ስድስት ክለቦች መካከል ከአስሩ ጋር አብሮ እየሰራ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ጎፈሬ በዛሬ ዕለት ከመከላከያ ጋር አብሮ ለመሥራት ቅድመ ስምምነት ያደረገ ሲሆን የስምምነቱ የመጀመርያ ምዕራፍ የሆነውን ሥራም ጎፈሬ በክለቡ ፅህፈት ቤት በመገኘት አስረክቧል።
በርክክቡ ወቅት መከላከያን በመወከል የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጄ፣ በጎፈሬ በኩል አቶ ሳሙኤል ተገኝተዋል። በቅድመ ስምምነቱ መሠረት በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ የሚያደርገውን ሁለት ዓይነት መለያ ከአሰልጣኞቹ አባላት ትጥቅ ጋር ጨምሮ ማስረከብ ሲሆን ወደፊት በሚፈፀሙ ስምምነቶች መሠረት ለሴቶች፣ ለታዳጊ ወጣት ቡድኑ እና በመከላከያ ስር ለሚገኙ በርከት ላሉ የስፖርት ቡድኖች ጎፈሬ ትጥቅ አምርቶ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከርክክቡ በማስከተል የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጄ በንግግራቸው ” ከዚህ በፊት ስንፈልገው የነበረ ሥራ ነወ። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የምንጠቀማቸው ትጥቆች ከሀገር ውጭ የሚመረቱ ነበሩ። እስከ ዛሬም አጋጣሚውን አጥተን ሀገር በቀል ምርቶች ሳንጠቀም ቀርተናል። ይህም ብቻ ሳይሆን የገበያው አካሄድም በጣም የተወሳሰበ ነበር። አሁን ግን የቀድሞ የመቻልን መለያ የተወሰነ ለውጥ ብናደርግም እንዳለ ይዘት ሳይለቅ ተቋሙን እና ጦሩን የሚገልፅ መለያ እውቅና ካለው ሀገር በቀል ትጥቅ አምራች ጋር መጠቀማችን ትልቅ አስተዋፆኦ አለው። እፎይታም አለው። በቀጣይም እንደ ቡድን ብቻ ሳይሆን እንደ ተቋም የመከላከያ ሠራዊቱ መለያ ከጎፈሬ ጋር ለመሥራት እንጨርሳለን።” ብለዋል።
አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው ” መከላከያን ከሚያክል ትልቅ ክለብ ጋር አብረን በመስራታችን ደስታ ይሰማናል። መከላከያ የኛን ምርት ለመጠቀም በማሰቡም አስደስቶናል። በአንድ ቀን ነው ንግግራችን ያለቀው፤ በአንድ ቀን ነው ምርቱንም አምርተን ያስረከብናቸው። እነርሱ ከውጭ የሚጠብቁትን መለያ ሀገር በቀል በሆነ ተቋም ሰርተን እነርሱን ደስተኛ በማድረጋችን እንደ ጎፈሬ ደስተኞች ነን። በሂደት የረጅም ጊዜ ውል ገብተን እስከ መጨረሻው ደረስ የትጥቅ ጉዳይን በዘላቂነት እንፈታለን። እነርሱም ስራውን አምነው ለኛ በመስጠታቸው በጣም እናመሰግናለን።” በማለት ተናግረዋል።
መከላከያ በሰባተኛው ሳምንት ነገ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የጎፈሬ ምርት የሆነውን አዲሱን መለያ በመልበስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።