ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የባህር ዳር እና ወላይታን ፍልሚያ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
ከሦስት ተከታታይ ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ጅማ አባጅፋር ላይ የሁለት ለምንም ድል ያገኘው ባህር ዳር ይህንን የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ለማስቀጠል እና በወረቀት ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ ነው የሚለውን ተቀፅላ በተግባር ለማሳየት ነገ ጠንካራ ጨዋታ ከሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ (በጊዜያዊነት ዛሬ በፋሲል ተነጥቋል) ይጠብቀዋል።
በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር የሊጉ አጀማመር ድንቅ የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ መንገራገጭ አጋጥሞት ነበር። ከዚህ የውጤት ማጣት ችግሩ የወጣበት የሚመስለውን ድል ደግሞ በስድስተኛ ሳምንት ጅማ ላይ አግኝቷል። የጅማው ጨዋታ ላይ የነበረው ጥሩ ብቃት ደግሞ ከደካማ ተጋጥሚ መነሻነት የመጣ አለመሆኑን ለማሳየት ነገ የሚፈተንበትን ጨዋታ እንደሚጠብቀው እሙን ነው። ባህር ዳር በዘንድሮ የውድድር ዘመን ባልተለመደ መልኩ በጅማው ጨዋታ የመልሶ ማጥቃት ባህሪ ተላብሶ ታይቷል። ወላይታ ድቻ ግን በጅማ ልክ የራሱን ሜዳ ነቅሎ የሚያጠቃ ቡድን አለመሆኑ ወደ ኳስ ቁጥጥሩ ሊመልሰው ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ቦታ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ፍጥነት ለጠጣሮቹ የድቻ ተከላካዮች ምቾት ላይሰጥ እንደሚችል ይታሰባል።
ባህር ዳር ነጥቡን 10 ያደረሰበትን ድል ሲያገኝ መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይ የቁመታሙ አጥቂ ኦሴ ማውሊ በ63ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘሁን ቀይሮ ሲወጣ ያሳየው ከልክ ያለፈ የመበሳጨት ስሜት ነው። ይህ የተጫዋቹ መበሳጨት ከዓሊ ምርጥ አቋም ማሳየት ጋር አሠልጣኙ ጠንካራ ጎናቸው በሆነው የሰው ቁጥጥር (Man Management) አስተካክለውት ዳግም ያጣምሯቸዋል ወይስ ወደ ዓሊ ፊታቸውን ያዞራሉ የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ውጪ ግን በመከላከሉም ረገድ ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ እንዲጫወት ድፍረት የሚሰጠው የኋላ ክፍሉ በመልሶ ማጥቃት ስል የሆነ ታጋጣሚ ማግኘቱ ሊፈትነው እንደሚችል መናገር ይቻላል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በሆነው መርሐ-ግብር በድሬዳዋ ከተማ አንድ ለምንም ከተሸነፈ በኋላ ከጨዋታ ጨዋታ ጠንካራ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የተመቸው የሚመስለውን የሊጉን መሪነት ዛሬ በጊዜያዊነት በፋሲል ቢነጠቅም ሌላኛውን ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ነገ በመፋለም ዳግም መሪ መሆንን በማለም ይጫወታል።
የብዙዎችን ግምት ፉርሽ ባደረገ መልኩ ሳይጠበቅ የሊጉን መሪነት ተቆናጦ የነበረው ድቻ በሁሉም ጨዋታን በሚወስኑ ሁነቶች ላይ እንደ ቡድን መንቀሳቀሱ እየጠቀመው ይመስላል። በተለይ ደግሞ ከወልቂጤ በመቀጠል ከሌሎች አራት ክለቦች ጋር በጣምራ የሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ ሁለተኛ ክለብ የሆነበት የመከላከል አደረጃጀት ለተጋጣሚ ቡድኖች ትንሽ ከበድ ያለ ፈተናን የሚሰጥ ነው። ከሦስት ጊዜ በላይ የተለያዩ የመሐል የተከላካይ መስመር ጥምረቶችን ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ያሳየው ቡድኑም ግቡን እምብዛም ሲያጋልጥ አልነበረም። የዋናዎቹ የደጉ እና አንተነህ ጥምረትንም የበረከት እና መልካሙ ጥምረት በአስተማማኝ ሁኔታ እየተረከበው ይመስላል። ከዚህ ውጪ የመስመር አጥቂዎቹ ምንይሉ እና ቃልኪዳንም በቡድኑ አጨዋወት ውስጥ የመከላከል ተሳትፏቸው ጎልቶ ሲታይ ነበር።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ተጫውቶ ያለ ግብ የተለያየው ድቻ በዋናነት በጨዋታው የሊግ መሪ መንፈስ ኖሮት ጨዋታው አላደረገም ነበር። ጨዋታዎችን በተከታታይ እያሸነፈም ወደ አሸናፊነት ሥነ-ልቦና ያልመጣ እስኪመስል ድረስ በጨዋታው ድፍረት ኖሮት ሲያጠቃ አልነበረም። በቀደሙት ጨዋታዎች በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ እንደሆነ በጉልህ ቢያሳይም በፋሲሉ ጨዋታ ግን ከተጋጣሚ ግብ ርቆ መንቀሳቀሱ ይህን ጠንካራ ጎኑ እንዳደበዘዘውም ይታመናል። ምናልባት ነገ ግን የቀደመ የመልሶ ማጥቃት ስልነቱን አግኝቶ ወደ ሜዳ ከገባ ለባህር ዳር ተከላካዮች የፈተና ጊዜን ሊሰጥ ይችላል።
ባህር ዳር ከተማ ተመስገን ደረሰን እና ሰለሞን ወዴሳን ከጉዳት መልስ በሙሉ አቅም ሲያገኝ አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙን ግን ነገ አያገኝም። ወላይታ ድቻ በበኩሉ ሁለቱን የግብ ዘቦች ወንድወሰን አሸናፊ እና ቢኒያም ገነቱ ግልጋሎት ነገም አያገኝም።
ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት ይካሄዳል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ እስካሁን በሊጉ በአራት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል። በሦስቱ ግንኙነታቸውን አቻ ሲለያዩ የአምናው የሁለተኛ ዙር ጨዋታ በድቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታዎቹ ወላይታ ድቻ አራት ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ሁለት ግቦች አሏቸው።
ግምታዊ አሠላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ፋሲል ገብረሚካኤል
ግርማ ዲሳሳ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ
ፍፁም ዓለሙ – አለልኝ አዘነ – አብዱልከሪም ንኪማ
ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ – ተመስገን ደረሰ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ፅዮን መርዕድ
ያሬድ ዳዊት – በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ
እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ
ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቃልኪዳን ዘላለም