ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን በዳሰሳችን አንስተናል።

በስድስተኛው ሳምንት ሽንፈት ከደረሰባቸው ቡድኖች መካከል ሁለቱ በዚህ ጨዋታ ይገናኛሉ። በእርግጥ የመጨረሻ ውጤታቸው ይመሳሰል እንጂ የተጋጣሚዎች የእስካሁኑ አመጣጥ ለየቅል ነው። ሦስት ድሎች ያሉት መከላከያ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ የመጣ ይመስላል። በነገው ጨዋታ ውጤት ላይ ተመስርቶም ወደ መሪዎቹ የመጠጋት ዕድል ይኖረዋል። ከፍ ባለ ጫና ወደ ሜዳ የሚገቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግን ገና ከድል ጋር ለመገናኘት እያለሙ ይገኛሉ። ነገ ከተሳካላቸው ግን በሦስት አቻዎች ያገኙትን የነጥብ ስብስብ ወደ ስድስት የማሳደግ ዕድሉ አላቸው።

መከላከያ ከሽንፈት ወደ ድል ለመመለስ በሚያደርገው ጨዋታ ቡናን ሲገጥም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የታየበትን እስካሁን ያልነበረ ድክመት መቅረፍ ያስፈልገዋል። ወደ መስመር አድልተው የሚንቀሳቀሱ አማካዮቹ ባላቸው የጎላ የመከላከል ሽግግር ተሳትፎ እምብዛም የማይደፈረው ኮሪደሩ በተለይም በግራ በኩል ክፍት ሆኖ ታይቶ ነበር። ሁኔታውን በቦታው ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትነው የቢኒያም ላንቃሞ አፈፃፀም ደከም ከማለት የመጣ ቢመስልም በዚህም ጨዋታ ቀዳሚው ተመራጭ ሰመረ ሀፍተይ አለመኖሩን ተከትሎ ጦሩ የሳሳውን ቦታ በአግባቡ መሸፈን ይገባዋል። ይህ ካልሆነ ግን በሁለቱ መስመሮች ያላቸውን የማጥቃት ጉልበት ለመጨመር እየጣሩ ላሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ አይቀርም።

ሀዲያ ሆሳዕና በሦስት ተከላካዮች ወደሚጀምር አሰላለፍ በመጣበት በአዲስ አበባው ጨዋታ የማጥቃት ኃይሉ ጨምሮ ታይቷል። የመስመር ተመላላሾቹ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቀርበው እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የቁጥር የበላይነትን ለማግኘት ሲረዳው ተመልክተናል። ሆኖም ቡድኑ አሁንም ይበልጥ ተደጋጋሚ ዕድሎችን በወጥነት መፍጠር ላይ ይበልጥ መሻሻል ይገባዋል። በነገው ጨዋታ ይህንን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ቢገባውም አንገብጋቢው ክፍተቱ ግን ፊት መስመር ላይ ነው። የተፈጠሩት ዕድሎች በርካታ ባይባሉም ጥቂት ግን አልነበሩም። ከግብ የራቁት የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹም ሆኑ በወሳኝ ቅፅበቶች ወደ ሳጥኑ የሚቀርቡት አማካዮች ግብ ማስቆጠር እና በራስ መተማመናቸውን ለማግኘት የነገው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። በነገው ጨዋታ ችግሩን ለመቅረፍ ከተጫዋቾች ሽግሽግ ባለፈ የአደራደር ለውጥም ሊኖር እንደሚችል ይገመታል።

በሌላ መልኩ የመከላከያ የመልሶ ማጥቃት ጥንካሬ ለሀዲያ ሆሳዕና ስጋትን የሚጭር ነው። በአዲስ አበባው ጨዋታ በቀጥተኛ ጥቃት ያስተናገዱት ግብ ለዚህ ማሳያ ነው። ሦስት የመሀል ተከላካዮችንም ይዞ የተጋጣሚን ቁልፍ አጥቂ አለማቆሙ መከላካዮችም በዚህ አኳኋን እንዲቀርቡ የሚያበረታታ ነው። ለዚህ ብቁ የሆነው አጥቂያቸው ኦኩቱ ኢማኑኤል እንዲሁም በቴክኒክ ብቃቱ ከተከላካይ መስመር ፊት ያለው ቦታ ላይ ተፅዕኖውን እያጎላ የመጣው ቢኒያም በላይ ለጦሩ የፈጣን ጥቃት ጥሩ መሳሪያ መሆን ይችላሉ። መከላከያም እንደ ሆሳዕና በመስመር ተከላካዮቹ ባይሆንም በግራ እና ቀኝ በሚሰለፉ አማካዮቹ የሚያጠቃበት መንገድም በቦታው የሚኖረው ፍልሚያ የጨዋታውን ውጤት እንዲወስን የሚያደርግ ይመስላል።

መከላከያ ሠመረ ሀፍተይ እና አዲሱ አቱላን በጉዳት ያጣል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በተቃራኒው ባዬ ገዛኸኝ ወደ ሜዳ የሚመለስ ሲሆን አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ፊት መስመር ላይ አማራጫቸውን ማስፋቱ ለሆሳዕና መልካም ዜና ያደርገዋል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 2008 ላይ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን በዚህም የመጀመርያውን ጨዋታ 0-0 ተለያይተው ሁለተኛውን ጨዋታ መከላከያ 2-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ዳዊት ማሞ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ገናናው ረጋሳ

ኢማኑኤል ላርዬ – ደሳለኝ ደባሽ

ግሩም ሀጎስ – ቢኒያም በላይ – ብሩክ ሰሙ

ኡኩቱ ኢማኑኤል

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ብርሀኑ በቀለ – መላኩ ወልዴ – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ አርፌጮ

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ተስፋዬ አለባቸው – ኤፍሬም ዘካሪያስ

ዑመድ ዑኩሪ – ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ