ዴቪድ በሻህ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንዲያጠናክሩ የመለመላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ዝርዝር ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታለች።
የቀድሞው ተጫዋች ዴቪድ በሻህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በመመልመል ስራ ተጠምዶ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በቅርቡ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለብሄራዊ ቡድኑ ጥንካሬን ሊለግሱ ይችላሉ ተብሎ ከመታሰቡም በተጨማሪ በአጠቃላይ በቡድኑ ውስጥ ለቦታ በሚኖረው ፉክክር ተጫዋቾች የራሳቸውን እምቅ ብቃት አውጥተው መጫወት እንዲችሉ ያበረታታቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለረጅም ጊዜ ብሄራዊ ቡድኑን ሲፈትን የቆየው የግብ ጠባቂ ችግር ላይም ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ይታሰባል፡፡ የሆነው ሆኖ ዴቪድ የመለመላቸውን ተጫዋቾች ከሚጫወቱበት ቦታ እና ከክለባቸው ጋር ዝርዝራቸው ሶከር ኢትዮጵያ ደርሷታል። ለኢትዮጵያ ለመጫወት ፈቃደኝነታቸውን የገለጹት ዘጠኝ ተጫዋቾችም የሚከተሉት ናቸው።
– አንዋር ሚዴይሮ (19 ዓመት) – በአታላንታ ከ19 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በቀኝ መስመር እና አጥቂ አማካይ ቦታ የሚጫወት
– መለሰ ፍሮይንዶርፍ (19 አመት) – በጀርመን 4ኛ ዲቪዝዮን ለሆፈንሃይም ሁለተኛው ቡድን የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ የሚጫወት
– ዴቪድ ደጎ (20 ዓመት) – በእስራኤል አንደኛ ዲቪዝዮን ቤይታር ጀሩሳሌም ቡድን ውስጥ የማጥቃት ባህሪ ያለው የመሃል አማካይ ሆኖ የሚጫወት
– ኬኒ ፕሪንስ ሬዴንዶ (27 ዓመት) – በጀርመን 3ኛ ዲቪዝዮን ካይዘርስላውተርን ቡድን ውስጥ በሁለቱም በኩል መጫወት የሚችል የክንፍ ተጫዋች
– ኦር ኢንብሩም (25 ዓመት) – በእስራኤል 1ኛ ዲቪዝዮን ኤፍሲ አሽዶድ ቡድን በግራ ክንፍ ተጫዋች ቦታ የሚጫወት
– አውካ አሽታ (22 ዓመት) – በእስራኤል 1ኛ ዲቪዝዮን በአፖዌል ጀሩሳሌም የሚገኝ
– ስንታየሁ ሳላሊች (30 ዓመት) – በቱርክ 2ኛ ዴቪዝዮን ጌንክለርቢርሊጊ ቡድን በሁለቱም ክንፍ የሚጫወት አጥቂ
– ዳንኤል ንጉሤ ስክሬትበርግ (19 አመት) – በኖርዌይ 1ኛ ዲቪዝዮን ስትሮምስጎስት ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነ
– ያኮቭ ብሪሆን (28 ዓመት) – በእስራኤል 1ኛ ዲቪዝዮን ኤፍ ሲ አሽዶድ ቡድን በሁለቱም ክንፍ የሚጫወት አጥቂ
ዴቪድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የምልመላ ጊዜው አጭር በመሆኑ ምክንያት አብዛኛው ትኩረቱ የነበረው በአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን ሊረዱ የሚችሉ ተጫዋቾች ላይ ነው፡፡ በቀጣይ ግን ለሊቨርፑል ወጣት ቡድን እንደሚጫወተው ታዳጊ መልካሙ ፍሮይንዶርፍ አይነት ተጫዋቾችን ለመመልመል ሀሳብ እንዳለው አክሏል፡፡
እንደ ዳቪ ሰልከ እና ማረን ሃይለስላሴ አይነት ተጫዋቾች ገና ያልወሰኑ ሲሆን አሁን ያሉት ተጫዋቾች ግን በማጥቃቱ በኩል ብሄራዊ ቡድኑን የሚያግዙ ከመሆናቸው በተጨማሪ የግብ ጠባቂ ችግሩን ለቀጣይ ረጅም ዓመታት ሊፈታ የሚችል ወጣት ግብ ጠባቂ መኖሩ ተገልጸል፡፡ የተጫዋቾቹ ዝርዝር እና ምስላዊ ማስረጃዎችም ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተላከ ሲሆን ውሳኔያቸው የሚጠበቅ ይሆናል፡፡