በወቅታዊ የክለቡ ሁኔታዎች ላይ ትናንት ረፋድ ላይ ስብሰባ የተቀመጠው የሲዳማ ቡና ቦርድ ውሳኔዎችን አሳልፎ እንደወጣ ታውቋል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት አጋማሽ ቡድኑን ተረክበው ከነበረበት የመውረድ ስጋት በማላቀቅ በሊጉ ያቆዩት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ዘንድሮ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ለውድድር ቢቀርቡም የታሰበውን ያህል ውጤት እያገኙ አይደለም። ከትናንት በስትያ ምሽት በፋሲል ከነማ የደረሰባቸው የአራት ለዜሮ ሽንፈት ደጋፊውን ክፉኛ ማስቆጣቱንም መታዘብ ችለናል። ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት አስተያየት ” የፈለገው እርምጃ ቢወስዱብኝ ምንም ችግር የለውም። በዚህ ሁኔታ ሆኖ መሥራትም ከባድ ነው።” በማለት ለመለያየት የቀረበ ፍንጭ መስጠታቸውም ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ የክለቡ ቦርድ ትናንት ከሰዓት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጋር በክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ እና በቡድኑ አቋም ዙርያ ግምገማ አድርጓል። በዚህም መሠረት የቡድኑ ውጤት ለጊዜው ጥሩ ባይሆንም በጊዜ ሂደት መስተካከል የሚችል መሆኑን በማመን አሰልጣኝ ገብረመድኅን በክለቡ እንዲቆዩ ውሳኔ አሳልፏል። ትናንት ማምሻውን ክለቡ ባረፈበት ሆቴል ከተጫዋቾቹ ጋር ስብሰባ የተቀመጡት የክለቡ አመራሮችም አሰልጣኙ በቡድኑ እንደሚቆይ ገልፀው አሁን ካለው ወቅታዊ የውጤት ችግር በመውጣት ቡድኑን ወደ ውጤት እንዲመልሱት መነጋገራቸውን ለማወቅ ችለናል።