የ2014 የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ መክፈቻ ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን የምድብ ሀ ጨዋታዎች በሆሳዕና አብዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ዛሬ ሲጀምር አርሲ ነገሌ ጋሞ ጨንቻን ሲያሸንፉ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና ንግድ ባንክ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ ላይ የመጀመርያው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ የከተማው ከንቲባ አቶ አብረሀም መጫ፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ኢብራሂም መሐመድ እና ኢ/ር ኦሌሮ ኦፒዮ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ም/ፀኃፊው አቶ ሰለሞንገብረሥላሴ ተገኝተው ከተጫዋቾች ጋር በመተዋወቅ ጨዋታውን አስጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የአርሲ ነገሌ እና የአንቦ ከተማ ጨዋታ እስከ 20ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የጎል ሙከራ ሳያስመለክተን ዘልቋል። አርሲ ነገሌዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ከማዕዘን ምት በተገኘ አጋጣሚ የጎል ዕድል ፈጥረው የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በከፍተኛ ሊግ የመጀመርያ ተሳትፎ ያደረጉት አንቦዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙም ፍሬ ሳያፈራ በቀላሉ በአርሲ ነገሌ ተከላካዮች ይመለስባቸው ነበር። ያም ቢሆን ከማዕዘን ምት ከተሻገረ ኳስ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ራህመቶ መሐመድ የሚሰለጥኑት አርሲዎች በተለይ አንበሉ ብሩክ ብፁአምላክ መሐል ላይ ኳሶችን በማደራጀት ለአጥቂዎች ለማድረስ የሚያደርገው ጥረት መልካም ቢሆንም የአጥቂዎች ንቁ ያለመሆን እና ቦታ አጠባበቅ ችግር ምክንያት ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተመልክተናል። ያም ቢሆን በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ብሩክ ብፁአምላክ ከሳጥን ውጭ በ72ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው የገላን ከተማ እና የጋሞ ጨንቻ ጨዋታ ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቶበት በጋሞ ጨንጫ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ጎል አይቆጠር እንጂ በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ የሚመራው ገላን ከተማ ኳሱን አደራጅተው በመሄድ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ካለመረጋጋት የተነሳ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ በቀላሉ ኳሱን ይነጠቁ ነበር። በዚህ ሂደት ብሩክ እንዳለ ከሳጥን ውጭ ጥሩ አድርጎ የመታውን ኳስ የጋሞ ጨንቻው ግብ ጠባቂ ነጋ ከበደ አድኖበታል።

ቀድሞ አርባምንጭ ከተማን እና ሲዳማ ቡናን በማሰልጠን በምናቀው አለማየሁ አባይነህ(አሌኮ) የሚሰለጥነው እና በጨዋታው ማድረግ የሚፈልገውን በማድረግ ስኬታማ የነበረው ጋሞ ጨንቻ ከእረፍት እንደተመለሱ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ኪሩቤል ፍቅረማርቆስ በግንባር በመግጨት ጋሞዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። በአንድ ሁለት ቅብብል በፍጥነት ጎል ላይ በመድረስ አደጋ የሚፈጥሩት ጋሞዎች በመልሶ ማጥቃት በደደቢት ተስፋ ቡድን የተገኘው እና በሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ አለማየሁ ጋር አብሮ የሰራው ወጣቱ አጥቂ ከማል አቶም ግብጠባቂው ባጠበበት ቦታ ከሳጥን ውጭ ግሩም ጎል አስቆጥሮ የጋሞዎችን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። እንቅስቃሴያቸው የተሻለ የነበሩት ገላኖች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ጨዋታውን ተሸንፎ ለመውጣት ተገደዋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው እና በኢትዮጵያ እግርኳስ የቀደመ ስም ያላቸውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከንግድ ባንክ ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ አቅም የሚገኙ እና ያለፉት ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ ሲጫወቱ የምናቃቸው ተጫዋቾች በሁለቱም ቡድን መኖራቸው በርከት ብሎ ጨዋታውን ሲከታተል የነበረውን ተመልካች አዝናንቷል።

ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት ኢትዮ ኤሌትሪኮች የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ምንያህል ተሾመ በጥሩ ሁኔታ ከመስመር ያሻገረለትን ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ በመግጨት ጎል አድርጎት ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ፀጋ ደርቤ የኢትዮ ኤሌትሪክ የማጥቃት መነሻ በመሆን የንግድ ባንኮችን ተከላካዮች ሲፈትን ከመቆየቱ ባሻገር ከተመልካቹ አድናቆት ተችሮታል። ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ የዕለቱ ዳኛ ፊሽካ እየተጠበቀ ባለት ሰዓት የተገኘውን የማዕዘን ምት ተጠቅሞ አደም አባስ የቀድሞ ክለቡ ላይ ጎል አስቆጥሮ ንግድ ባንኮችን አቻ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደጋግመው ወደ ጎል በመድረስ ብልጫ የነበራቸው ኤልፖዎች በተሻለ በነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ መሪ ሊሆኑ ነበር። ጥንቃቄ የመረጡት ንግድ ባንኮች በመከላከል ላይ አተኩረው በመልሶ ማጥቃት ጎሎችን ለማስቆጠር ቢሞክሩም በጨዋታው ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት አንድ አቻ ተጠናቋል።