የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ዛሬ ተጀምሯል። በምድብ ለ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎችም ሺንሺቾ፣ ወራቤ እና ቡታጅራ አሸንፈዋል።
የምድቡ የመከፈቻ ጨዋታ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ከምባታ ሺንሺቾ መካከል የተደረገ ነበር። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ያስጀመሩት ይህ ጨዋታ ለህልውና ዘመቻ መስዋዕትነት ለከፈሉ የፀጥታ ኃይሎች የአንድ ደቂቃ መታሰብያ ከተደረገ በኋላ ተካሂዶ በሺንሺቾ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
እጅግ የተቀዛቀዘ የነበረው የመጀመርያ አጋማሽ አንድም የጠራ የጎል ዕድል ያልተፈጠረበት ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቅብብሎች ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጡበት እና ከመሐል ሜዳ ያልተሻገረ ሆኖ ያለ ጎል ተጠናቋል።
የተለየ መልክ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ለሺንሺቾ ድንቅ የነበረ ሆኖ አልፏል። በ63ኛው ደቂቃ የሺንሺቾ አምበል ኤፍሬም ታምራት ከሳጥኑ አቅራቢያ ወደ ግራ ካደላ ቦታ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በሽር ባወጣበት ሙከራ የጨዋታው የመጀመርያ ጥሩ ሙከራ የተመለከትን ሲሆን ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጃፋር ከበደ ሺንሺቾን ቀዳሚ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ የማጥቃት መንገዱ ወለል ብሎ የተከፈተላቸው ሺንሺቾዎች ተደጋጋሚ ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን በ74ኛው ደቂቃ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ኤፍሬም ታምራት ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል። ልደቱ ለማ 85ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ መልካም አጋጣሚ አግኝቶ ግብ ጠባቂ በመለሰበት ኳስ በጨዋታው ተዳክመው የቀረቡት ለገጣፎዎች ልዩነቱን ለማጥበብ ተቃርበው የነበረ ሲሆን ሺንሺቾዎችም 90ኛው ደቂቃ ላይ ጃፋር ከበደ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ባመከነው ኳስ አስቆጪ ሙከራ አድርገዋል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ አሸናፊ ዋሎ በጥሩ ሁኔታ የደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስት ተረጋግቶ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ግብነት ለውጦት ጨዋታው በሺሺቾ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
8፡00 ላይ ስልጤ ወራቤን ከ ኮልፌ ቀራንዮ ያገናኘው ጨዋታ እንግዶቹ ኮልፌ ቀራንዮዎች ትጥቅ ባለማሟላታቸው እንዲሁም ዘግይተው ሜዳ በመድረሳቸው ከታሰበለት ሰዓት 45 ደቂቃዎችን ዘግይቶ 8፡45 ላይ ተጀምሯል።
እጅጉን ተቀዛቅዞ የጀመረው ጨዋታ ለ30 ደቂቃዎች ያክል የጠራ የግብ ሙከራ ያላስመለከተ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር ረገድ ግን የኮልፌ ቀራንዮ ቡድን እጅጉን ብልጫ ወስዶ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማሳየት ሳይችል ቀርቷል። በተቃራኒው የአሰልጣኝ ግርማ ተጫዋቾች በራሳቸው የግብ ክልል ቆይታ ቢያደርጉም በረጅሙ የሚልኳቸው ኳሶች በአጥቂዎቻቸው ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ሲቆራረጥ ቆይቶ በ35ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ደስታ ጊቻሞ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ ጋር አገናኝቶት መሪ ሆነዋል። የመጀመሪያውም አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።
በሁለተኛ አጋማሽ በሁለቱም በኩል በእንቅስቃሴ መሻሻል የተመለከትን ሲሆን በተለይም ኮልፌ ቀራንዮ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ሲደርስ ነበር። በመልሶ ማጥቃት እጅግ ጥሩ የነበሩት ስልጤ ወራቤዎች ደግሞ በ57 እና በ62ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወግኔ እና አምረላ ደልታታ ባደረጉት ሙከራዎች ተጨማሪ ግብ ሊያገኙ ነበር። በዚሁ መንገድ በ77ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ሌላ ኳስ በረከት ወንድሙ እና ሳዲቅ ሴቾ አንድ ሁለት በመቀባበል በረከት ወንድሙ ግብ አስቆጥሮል የወራቤ የግብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ብሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ወራቤዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲዘነዝርባቸው ተስተውሏል። በ87ኛው ደቂቃም ኮልፌዎች ከሽንፈት ያላደናቸውን ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ፈቱ አብደላ አስቆጥሯል። ከፍፁም ቅጣት ምቱ መቆጠር በኋላ ኮልፌዎች ወርቃማ ዕድል አግኝተው ሳይጥቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውም በስልጤ ወራቤ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቆል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ምክንያት ከተያዘለት ሰዓት ዘግይቶ የጀመረው የቡታጅራ እና የሰንዳፋ በኬ ጨዋታ ኃይል እና ጉልበት የበዛበት እና በረጃጅም ኳሶች የታጀበ ሆኖ ተደርጓል።
በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ከኋላ መስመር የተሻገረን ኳስ መሳይ ሰለሞን በፍጥነት በመድረስ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ፈረሰኞቹ በ13ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለማው ታደሰ ባደረገው የግብ ሙከራዎች የሰንዳፋን ግብ ፈትሸዋል። ጨዋታው 22ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የሰንዳፋው ተጫዋች ሚኪያስ ጌታቸው አደገኛ ጉዳት አስተናግዶ በአምፖላንስ ወደ ህክምና ማዕከል አምርቷል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቀኝ መስመር ሰብሮ የገባውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው መሳይ ሰለሞን በግምት ከ18 ሜትር ላይ ሆኖ አክርሮ የመታው ሲሆን ኳሱም የግቡን አግዳሚ ለትሞ መረብ ላይ አርፏል።
የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ተጭነው የተጫወቱት ሰንዳፋዎች ከሁለቱም መስመር የሚሻገሩ ኳሶችን ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በፈረሰኞቹ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክቱ የጨዋታው መጠናቀቂያ ደርሷል። በማብቂያው ላይም ወሰኑ ዓሊ ለፈረሰኞቹ ተጨማሪ ግብ አክሎ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ ጨዋታው ተጠናቋል ።
የምድቡ ቀሪ የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ 8፡00 ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከ ቡራዩ ከተማ፣ 10፡00 ላይ ካፋ ቡና ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ ይጫወታሉ።