የሊጉ ሰባተኛ ሳምንት የሚቋጭበት ጨዋታ የዳሰሳችንም ማሳረጊያ ይሆናል።
በዕኩል ስምንት ነጥቦች ከሰንጠረዡ አጋማሽ በታች የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ማሸነፍ ከወገብ በላይ ለመቀመጥ ዕድሉን ይሰጣቸዋል። የቅርብ ጨዋታዎች ውጤቶቻቸውን ስንመለከት ግን የውጤት ተቃርኖን እናገኛለን። ድሬዳዋ ከተማ በጅማ ላይ ካሳካው ድል በኋላ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ሲያሳካ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ያልድል ከተጓዘባቸው አራት ቀዳሚ ሳምንታት በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ለነገው ጨዋታ ደርሷል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች ለኳስ ቁጥጥር ከሚሰጡት ቦታ አንፃር አማካይ ክፍል ላይ ያላቸው ሰሞንኛ አቋም ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ የሚቀር አይመስልም። በዚህ በኩል በመጨረሻው ጨዋታ ከብቸኛ አጥቂያቸው ጀርባ ከሚሰለፉ ሦስት አማካዮች ሁለቱን ለውጠው ያስወጡት ድሬዎች ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው ከተከላካይ መስመሩ ፊት ያለው የዳንኤል እና ብሩክ ጥምረት መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማቋረጡ በኩል ጥሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የቡናን አማካዮች ለመግታት የተሻለ ግምት ሊሰጠው ይችላል። በማጥቃቱ በኩል ግን በግራ ወደሚነሳው አብዱለጡፍ መሀመድ የሚያጋድለው የቡድኑ መዋቅር ቅብብሎችን የሚያሳልጥ ሁነኛ ሰው ማግኘት ሳያስፈልገው አይቀርም።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ቡናን ስንመለከተው ታፈሰ ሰለሞን ከቡድኑ ጋር አለመኖሩን ተከትሎ የተፈጠረው የዊሊያም እና ሮቤል ጥምረት መልካም ነገርን ይዞ የመጣለት ይመስላል። በተለይም በተጋጣሚ ደካማ የመከላከል መስመር ላይ የቁጥር ብልጫን በመውሰድ ቅብብሎችን ከውኖ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ እንዱሁም ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍ ብሎ እየታየ ነው። እዚህ ላይ በመከላከያው ድል የታገኘው ብቸኛ ግብም የሁለቱ ጥምረት ውጤት መሆኑ ሲታሰብ አቡበከር ላይ ያለውን ግብ የማስቆጠር ጫናም በመቀነሱ ረገድ ጥሩ ጅምር ሆኖ ይታያል። በነገው ጨዋታም ጥምረቱ በማጥቃት ሰዓት በሚከፈተው ወደ ድሬ የቀኝ መስመር አድልቶ ክፍተቶችን እንደሚያነፈንፍ ይጠበቃል።
ድሬዳዋ ከተማ ነገ አሻሽሎ እንዲመጣ የሚጠበቀው ሌላው ክፍተቱ የአጨራረስ ብቃቱ ነው። ማማዱ ሲዲቤን በፊት አጥቂነት የሚጠቀመው ቡድኑ ሌሎችንም ወደ አስቆጣሪነት ለመምጣት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በርክቶ መገኘት እና ሲዲቤም ምቹ ሆኖ በሚጨርስበት የአደጋ ዞን ትክክለኛው ቦታ ላይ እንዲገኝ የማድረግ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ቡድኑ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የወትሮው ኳስ ይዞ ጨዋታውን የማርገብ ከዛም አለፍ ሲል ተጋጣሚው ከግብ ክልሉ በራቀበት ቅፅበት ድንገተኛ ጥቃት የሚሰነዝርበትን ጠንካራ ጎኑን መልሶ ማግኘት እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። ሌላው ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ግን የሁለቱም የቀኝ መስመር ተከላካዮች ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ ሲሆን በሽግግሮች ወቅት እነዚህ ቦታ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት የመጠቀም ስልነታቸው የጨዋታውን ውጤት ሊወስን እንደሚችል ይታመናል።
ድሬዳዋ ከተማ በጨዋታው ዳንኤል ኃይሉን እና ጋዲሳ መብራቴን በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ሲያጣ የቁርጭምጭሚት ጉዳት ያገኘው እንየው ካሳሁን መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቤል ማሞ ቅጣት ላይ ሲሆን አላዛር ሽመልስም በጉዳት ለነገው ጨዋታ አይደርስም። በመከላከያው ጨዋታ ተጎድቶ የነበረው አበበ ጥላሁን ግን አገግሞ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ተሰምቷል።
ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት ይከናወናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ18 ጊዜያት ያህል ተገናኝው ኢትዮጵያ ቡና 10 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ድሬዳዋ 3 ጊዜ ድል ቀንቶታል ፤ 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ 30 ጎሎች በኢትዮጵያ ቡና 15 ጎሎች ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ አማካይነት ተቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ
ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ
ሳሙኤል ዘሪሁን – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ
ማማዱ ሲዲቤ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
ኃይሌ ገብረተንሳይ – ወንድሜነህ ደረጀ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ
ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን
ያብቃል ፈረጃ- አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ