ሪፖርት | ከአርባምንጭ ጋር አቻ የተለያየው ጅማ አባ ጅፋር የመጀመርያ ነጥቡን አግኝቷል

በአርባምንጭ እና ጅማ አባጅፋር መካከል የተደረገው የሰባተኛ ሳምንት የአራተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከወልቂጤ ከተማ ጋር ተፋልመው ያለ ግብ አቻ የተለያዩት አርባምንጮች አንድ ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ በአምበላቸወ ወርቅይታደስ አበበ ቦታ ፀጋዬ አበራን በኤሪክ ካፓይቶ ምትክ ደግሞ አሸናፊ ተገኝን በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ሲያካትቱ በባህር ዳር ከተማ ሁለት ለምንም ተረተው የመጡት ጅማዎችም ሦስት ነጥብ ለተጋጣሚ ከሰጡበት የመጨረሻ ጨዋታቸው በተመሳሳይ ሁለት ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሽመልስ ተገኝን እና ምስጋናው መላኩን አሳርፈው በላይ አባይነህ እና ሮጀር ማላን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ከወትሮው በተለየ በተረጋጋ ሁኔታ ኳስን በመቀባበል መጫወት የጀመሩት ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ፍላጎት ኖሯቸው ሲንቀሳቀሱ የታየ ሲሆን አርባምንጮች ደግሞ ኳስን ለተጋጣሚ ሰጥተው በሽግሮች ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ሲያደርጉ ታይቷል። በዘጠነኛው ደቂቃም የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ በእንዳልካቸው መስፍን አማካኝነት አድርገው ተመልሰዋል። ተጫዋቹም ከወደግራ መስመር ያገኘውን ኳስ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ሳጥን ሲልከው ማንም ሳይነካው መረብ ላይ ለማረፍ ተቃርቦ ነበር።

የእንዳልካቸውን ሙከራ ከተመለከትን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጅማዎች በራሳቸው በኩል ሌላ የሰላ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህም ዱላ ሙላቱ ከመሐል መስዑድ መሐመድ የሰነጠቀለትን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር የግብ ዘቡ ይስሐቅ ተገኝ የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት ሲያመክነው የተመለሰውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ያገኘው ዳዊት ፍቃዱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየገቡ የመጡት የአሠልጣኝ መሳይ ተጫዋቾች በተለይ በመስመር ላይ ትኩረት በማድረግ ጥቃቶችን መሰንዘር ይዘዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በ33ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት የተላከውን ኳስ በላይ ገዛኸኝ በግንባሩ ወደ ኋላ ሲልከው ፍጥነቱት ተጠቅሞ ያገኘው ሀቢብ ከማል ወደ ግብነት ሊቀይረው ከጫፍ ደርሶ ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎችም የሰላ አጋጣሚ ሳይፈጠር ያለ ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት አርባምንጮች ናቸው። በዚህም የጅማን ተከላካዮች ሲረብሽ የነበረው ሀቢብ ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ጅማዎች እጅግ አስቆጪ ዕድል አምልጧቸዋል። በዚህም በአጋማሹ መጀመሪያ ተቀይሮ የገባው ምስጋናው መላኩ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ዳዊት ተቀብሎት ለሙሴ ቢያመቻችለትም ወጣቱ አማካኝ በማይታመን ሁኔታ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንኳን ሳያደርገው ዕድሉን አምክኖታል።

በማጥቃቱ ረገድ መሻሻል ያሳዩት ጅማዎች በ53ኛው ደቂቃ የአርባምንጭ ተከላካዮች በፈፀሙት ስህተት መሪ የሚሆኑበትን ሌላ ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህም መስዑድ ከተከላካዮቹ የቅብብል ስህተት የተረከበውን ኳስ ለዳዊት ቢሰጠውም ዳዊት ኳሱን ጥሩ ቦታ ላይ ለነበረው የቡድን አጋሩ ከማቀበል ይልቅ ራሱ መምታትን መርጦ ኳሱ ወደ ውጪ ወጥቷል።

መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ ቢሆንም ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 71ኛው ደቂቃ ድረስ ያለ ሙከራ ከተጓዘ በኋላ የግብ ማግባት አጋጣሚ ተስተናግዶበታል። በዚህም በአብዛኛው በቀኝ መስመር በኩል ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ የነበሩት ጅማዎች አሁንም በዚሁ መስመር በምስጋናው አማካኝነት ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። አከታትለው ባደረጓቸው የተጫዋች ለውጥ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የጣሩት አርባምንጮች ደግሞ በ84ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን እንዳያገናኙ ያገዳቸው የግቡ አግዳሚ ነበር። በዚህ ደቂቃም ሀቢን ያሻገረውን የመዓዘን ምት ፀጋዬ አበራ በግንባሩ ቢገጨውም እንደተጠቀሰው የግቡ አግዳሚ ኳሱን አምክኖታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው 4 ደቂቃ አጋማሽ ላይ ደግሞ ሀቢብ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከመሐል የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ጥሩ ዕድል ቢፈጥርም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የግብ ዘብ አላዛር ማርቆስ አምክኖበታል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በአቻ ውጤቱ መሠረት ስምንተኛ ደረጃ ላይ የነበረው አርባምንጭ ነጥቡን አስር በማድረስ ሁለት ደረጃዎችን ሲያሻሽል ያለ ምንም ነጥብ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ያሳለፈው ጅማ አባጅፋር ደግሞ ከ50 ቀናት በላይ አብሮት የነበረውን ዜሮ ነጥብ ወደ አንድ አሳድጎ ያለበት አስራ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ረግቶ ተቀምጧል።