ሪፖርት | ቡናማዎቹ በአቡበከር ሁለት ጎሎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አግኝተዋል

በሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጨረሻ መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማን ከኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በስድስተኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር ከሰበታ ከተማ ጋር ተጫውተው ነጥብ የተጋሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ አብዱረህማን ሙባረክን ብቻ በአቤል ከበደ ለውጠው ጨዋታውን ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ መከላከያ ላይ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ባገኙበት ጨዋታ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ባለቀ ሰዓት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ያጡትን የግብ ዘብ አቤል ማሞን ብቻ በበረከት አማረ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሦስተኛው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበት መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም መሐመድ አብዱለጢፍ ከመሐል የተሻገረለትን ኳስ ፈጥኖ በማግኘት ወደ ሳጥን በማሻማት ግብ እንዲሆን ጥሮ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ናስር አማካኝነት ጥሩ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። በድጋሜ በጨዋታው ሩብ ሰዓት ኃይሌ ገብረትንሳኤ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ የለቀቀውን ኳስ አቡበከር ናስር ደርሶበት ሊጠቀመው ቢጥርም ተከላካዩ መሳይ ጻውሎስ ከግብነት አግዶታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዳዋዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና የመሐል አጥቂያቸው ማማዱ ሲዲቤን ዒላማ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶቻቸው ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም የቡና የግብ ክልል ተገኝተው በረከት አማረን ፈትነዋል። በዚህም ሙኸዲን ሙሳ ከመሐመድ የተሰነጠቀለትን ኳስ በወረደ አጨራረስ ወደ ግብ መታው እንጂ ቡድኑ በአጋማሹ የፈጠረው ለግብ የቀረበበት አጋጣሚ ነበር። አርባ አምስት ደቂቃው ተጠናቆ የተጨመረው ሁለት ደቂቃም ሊገባደድ ሲል ደግሞ የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሳሁን ከዳንኤል ደምሴ በተከላካዮች መሐል የተረከበውን ኳስ ለመጠቀም ከጫፍ ደርሶ ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ነበር። ነገርግን እንየው ኳሱ እና እግሩ ጥሩ ግንኙነት ሳያደርጉ ቀርተው ግብ ሳይቆጠር ቀርቷል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደግሞ እስከ 58ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ አልነበረውም። ቡናም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ሲንቀሳቀስ ድሬዳዋ ደግሞ ከኳስ ጀርባ መሆንን መርጦ ታይቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ ግን አቡበከር ናስር በመስመሮች መሐል የተቀበለውን ኳስ እየገፋ በመሄድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ፍሬው በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።

ጨዋታው 59ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ከደቂቃ በፊት ያደረገው አቡበከር ናስር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ አደጋ ሊፈጥር ሲል የዕለቱ ዳኛ በላይ ታደሰ ጥፋት ተሰርቶበታል ብለው ኢትዮጵያ ቡና የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም ራሱ አቡበከር በ62ኛው ደቂቃ ግብ አድርጎታል። በፍፁም ቅጣት ምቱ እና በሜዳ ላይ እየተሰጡት በነበሩት ውሳኔዎች ደስተኛ ያልነበሩት ድሬዳዋዎች 60ኛው ደቂቃ መገባደጃ ላይ በአምበላቸው ዳንኤል ደምሴ አማካኝነት ክስ አሲዘዋል።

መሪ ከሆኑ በኋላም ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ ያላቆሙት የአሠልጣኝ ካሳዬ ተጫዋቾች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ያስገቡት ድሬዎች በበኩላቸው ምላሽ ለመስጠት እስከ 86ኛው ደቂቃ ጠብቀዋል። ምንም እንኳን በተጠቀሰው ደቂቃ ቡድኑ በሱራፌል አማካኝነት ሙከራ ቢያደርግም ግን ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል። ይባስ ብሎ አማኑኤል ዮሐንስ ከታፈሰ ሰለሞን በደረሰው እና በቀጥታ ወደ ግብ በመታው የ88ኛ ደቂቃ ኳስ ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ በድጋሜ አቡበከር በሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበት (በሚኪያስ) ቡና ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አቡበከር የመጀመሪያውን ግብ ባስቆጠረበት አቅጣጫ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎታል። መረጋጋት የተሳናቸው ድሬዎች በተጨመረው ደቂቃ ሦስተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ቢቃረቡም ሳይሳካ ጨዋታው ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን አስራ አንድ አድርሰው ከአስረኛ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ለቆት ወደሄደው አስረኛ ደረጃ ሸርተት ብለዋል።