ትናንት የተጀመረው የ2014 የኢትዮጵያ ከፍተና ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ በሦስት ምድቦች ስድስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።
ምድብ ሀ
8፡00 ላይ በደቡብ ደርቢ ሀላባ ከተማ ከ ጌዲኦ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ተከናውኖበት በዲላ አሸናፊነት ተጠናቋል። የቀድሞ አሰልጣኙ አላምረው መስቀሌን መልሶ የቀጠረው ሀላባ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ነበር። ሰይድ ግርማ በ19 ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ መምራት የጀመሩት ሀላባዎች ውጤታቸውን ማስጠበቅ ሳይችሉ ቀርተው በ60ኛው ደቂቃ ላይ በድሩ ኑርሁሴን የአቻነቱን፤ 30ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የቀድሞ የቡታጅራ አጥቂ ክንዴ አቡቹ የአሸናፊነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውም በጌዲኦ ዲላ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
12፡00 ላይ ባቱ ከተማን ከ ሻሸመኔን ያገናኘው ጨዋታ በባቱ አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ጎል የዘለቀው ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያው ደቂቃ ላይ የሺጥላ ዳቢ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ባቱ ከተማ ሙሉ ሶስት ነጥብ አስጨብጦ ተጠናቋል።
ምድብ ለ
8:00 ላይ አዲስ አዳጊው ቡራዩ ከተማ ከ ቤንጂ ማጂ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በባለፉት ዓመታት ግብ በማስቆጠር የሚታወቀው ወንድምአገኝ ኬራ ለቤንች ማጂ ቡና ሲያስቆጥር ቡራዩ ከተማ በሁለተኛው ግማሽ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።
የዕለቱ የመጨረሻ የምድቡ ጨዋታ በከፋ ቡና እና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተደረገ ሲሆን ካፋ ቡና ባለ ድል ሆኗል። በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያው ደቂቃ አበበ ታደሰ እና ክንፈ መኮንን ያስቆጠሯቸው ግቦች ካፋ ቡና 2-0 በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያሳኩ አድርጓል።
ምድብ ሐ
ከሰዓት 8፡00 ላይ አዲስ አዳጊው ጉለሌ ክፍለ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ለመሸናነፍ ያደረጉት ጥረት ጨዋታውን እልህ የተሞላበት እና የመስመር ላይ ጥቃቶች የበዛበት ቢሆንም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በመቀጠል የተከናወነው በነቀምቴ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ መካከል የተደረገ ነበር። ጨዋታውን ነቀምቴ ከተማ ምኞት ማርቆስ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።