ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የሰባተኛ ጨዋታ ሳምንት ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በዚህኛው ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉 አስደንጋጩ የሲዳማ ቡና መከላከል

በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ፋሲል ከነማን የገጠሙት ሲዳማ ቡናዎች እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የ4-0 ሽንፈትን አስተናግደዋል። በብዙ መመዘኛዎች ደካማ የጨዋታ ቀን ያሳለፉት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ በጨዋታው ይከላከሉ የነበረበት መንገድ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በሰንጠረዡ አናት ለመፎካከር ከሚያስብ ቡድን ፍፁም የሚጠበቅ አልነበረም።

ከጨዋታው አስቀድሞ የቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እንደተናገሩት የመከላከል ሂደቱ ላይ ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ስለመኖራቸው ጠቁመው ነበር። መሰል ይዘት ያለው አስተያየት በቡድናቸው መከላከል ላይ ሲሰጡ አሰልጣኙ ይህ የመጀመሪያቸው አልነበረም። በቀደሙት ጨዋታዎችም በመከላከሉ ረገድ በቡድናቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን እና ለማሻሻል ጥረቶች ስለመኖራቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድ አቻ የተለያዩት ሲዳማ ቡናዎች በሦስቱም ጨዋታዎች በቅድሚያ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም መሪነታቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሲገደዱ ተመልክተናል። እርግጥ ይህኛው ጉዳይ በቀጥታ ከመከላከል ጋር የሚገናኝ ባይሆንም የሚነግረን ነገር ግን ይኖራል። በተጨማሪም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ አዳማዎች እንደፈጠሯቸው ጥራት ያላቸው ዕድሎች ሲዳማ ቡና አንድ ነጥብ ይዞ መውጣቱ በራሱ ዕድለኛ የሚያስብለው ነበር።

በፋሲሉም ጨዋታ ግን ሲዳማዎች እንደቀደሙት ጨዋታዎች በመከላከሉ ረገድ ስህተቶች መስራታቸውን መቀጠላቸውን ተከትሎ በጥራት ረገድ ከቀደሙ ተጋጣሚዎቻቸው የተሻለ የሆነው የፋሲል የማጥቃት ኃይል ሲዳማ ቡናዎችን ለሰሯቸው የመከላከል ስህተቶች በሙሉ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል።

በተቆጠሩት አራት ግቦች ውስጥ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች የሰሯቸው መሰረታዊ የመከላከል ስህተቶች የጎሉ ነበሩ። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማውን የማዕዘን ምት ለመከላከል ግብ ጠባቂያቸው ተክለማርም ሻንቆ እና ተከላካዩ ግርማ በቀለ ሳይነጋገሩ ለአንድ ኳስ በመሻማታቸው በተፈጠረ ግጭት የተገኘው ኳስ ለፋሲሎች ግብ መነሻ ነበር።

ሁለተኛው የአምሳሉ ግብ ስትቆጠር በቅድሚያ ኳሱ ከፋሲል ተከላካይ መስመር ሲነሳ የተወሰኑ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ጫና ለማሳደር ወደ ፊት በተጠጋ አቋቋም በተቃራኒው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሲዳማ ተጫዋቾች ደግሞ ወደ ራሳቸው ግብ በተጠጋጋ አቋቋም ላይ ይገኙ ነበር። ይህም ይበልጥ ቡድኑ እንዲለጠጥ (Stretched) ያስገደደ ሲሆን በዚህም የፋሲል ተጫዋቾች በመሀል በሚገኘው ሰፊ የሜዳ ክፍተት ኳሶችን ተቀብለው (Positional Superiority) ወደ መስመር ለማውጣት ሲጥሩ በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾች ኳሱን ወደ ያዘው ተጫዋች መምጣታቸውን ተከትሎ ኦኪኪ ወደ መስመር ያወጣው ኳስ በቀላሉ ሁለተኛ ግብ እንዲቆጠር አድርጓል።

ሦስተኛ እና አራተኛ ግብ የተቆጠሩበት መንገድም በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይነት ነበረው። ሦስተኛው ግብ ሲቆጠር ፋሲሎች የሲዳማዎች ቅብብል ካቋረጡ በኋላ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የጣሉትን ኳስ ሲዳማዎች ለመከላከል በማይመች የተበታተነ አቋቋም ላይ በመገኘታቸው ግቡ የተቆጠረ ሲሆን አራተኛው ግብ ላይም እንዲሁ የተጫዋቾች የቦታ አያያዝ ስህተቶች እና እንደ ሦስተኛው ግብ ሁሉ ደካማ የሆነ የጨዋታ ውጪ ወጥመድ አሰራር ከግቦቹ በስተጀርባ የነበሩ ስህተቶች ናቸው።

ከአራቱም ግቦች በስተጀርባ ከመሰረታዊ የመከላከል መርሆዎች ውጪ የሆኑ ግለሰባዊ ስህተቶች ያለ ቢመስልም ከግለሰባዊ ስህተቶች በስተጀርባ በጉልህ የሚታይ የቡድኑ መዋቅራዊ ስህተቶችም መዘንጋት አይገባቸውም። በመሆኑም በከፍተኛ የደጋፊዎች ተቃውሞ ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ በቀጣይ ውጤቱንም ሆነ የመከላከል ድክመቶችን በምን መልኩ ቀርፎ ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ ይጥራል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ዐፄዎቹ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

ሰሞነኛ የውጤት መቀዛቀዝ አጋጥሟቸው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን በመረምረም ከሰሞኑ ሲሰነዘሩባቸው ለነበሩ ትችቶች በቂ ምላሽን መስጠት ችለዋል።

በሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ላይ አራት ግቦችን አስቆጥረው ካሸነፉ በኋላ በነበሩት ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በአዲስ አዳጊው አዲስ አበባ ከተማ ሲሸነፉ ከአርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጋር አቻ ለመለያየት ተገደው ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ከተወሰደባቸው የበላይነት ውጪ ቡድኑ በሦስቱም ጨዋታዎች የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ቢኖረውም በክፍት ጨዋታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መቸገሩ ብሎም የተገኙትን ዕድሎች መጠቀም አለመቻሉ ከውጤታማነት እንዳገደው የተስተዋለ ሀቅ ነበር።

በሊጉ ባለፉት ሦስት ዓመታት በወጥነት ጥንካሬውን በማስመስከር አምናም የሊጉ አሸናፊ ለመሆን የበቃው ፋሲል ከነማ ከዚህ እውነታ በመነሳት በየጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያስመዘግብ ከፍተኛ ጥበቃ (expectation) የመኖሩ ነገር ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም። በዚህ ሂደት ውስጥ አይደለም መሸነፍ ነጥብ መጋራት እንኳን እንደ ሽንፈት በሚታይበት ሁኔታ ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ አለመያዙን ተከትሎ በርካታ ሀሳቦች ቢንሸራሸሩም የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ውጤት ግን ነገሮችን በቀጣይ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች በተለያዩ ምክንያቶች ከሜዳ በራቁበት በዚህ ወቅት የተቸገረ ቢመስልም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ልዩ ሆኖ አሳልፏል። በተለይም በማጥቃቱ ረገድ የነበራቸው የመፈፀም አቅም ከሰሞኑ የተሻለ ነበር። በየትኛውም የጨዋታ ቅፅበት ለተጋጣሚ ተከላካዮች ተጠግተው የሚጫወቱ ሁለት ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን (Dedicated Strikers) በመጠቀም ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች ፈተና ከመሆን ባለፈ ያገኟቸውን ዕድሎች በአግባቡ ወደ ግብነት በመቀየር ጥሩ ቀንን ማሳለፍ ችለዋል።

👉 ወልቂጤ ከተማ አሸንፏል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ሲታመሱ የሰነበቱት ወልቂጤ ከተማዎች ከተሟላ የጨዋታ ዕለት ስብስብ ጋር ወደ ድል ተመልሰዋል።

አዲስ አበባ ከተማን በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ በረቱበት ጨዋታ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ያልተጠቀሙባቸውን ስድስት የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾችን ዳግም በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያገኙ ሲሆን ከእነሱም በተጨማሪ በአራት ተጠባባቂ ተጫዋቾች ብቻ ጨዋታውን ያደረገው ቡድኑ በዚህኛው ጨዋታ አስራ ሁለት ተጠባባቂ ተጫዋቾችን ይዞ ጨዋታውን ከውኗል።

የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ እንደገና የቡድኑ ወሳኝ ሰው መሆኑን ባስመሰከረበት በዚሁ ጨዋታ ወልቂጤዎች ድል በማድረግ ደረጃቸውን ወደ አራተኛነት ከፍ ማድረግ ችለዋል። አምና በተለይ ከውድድሩ አጋማሽ አንስቶ በተፈጠረ የውጤት መቀዛቀዝ በመጨረሻም በሁለተኛ ዕድል በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠው ክለቡ የአምናው ዓይነት ስጋት ዳግም እንዳይከሰት ትኩረት ሊያስቀይሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በሙሉ በፍጥነት ምላሽ በመስጠት በሜዳ ላይ ባሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩሮ የተሻለ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ለማስቻል መሰል አስተዳደራዊ ክፍተቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የክለቡ ሰዎች ትኩረት አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል።

👉 ሀዲያ ሆሳዕና ከሦስት ነጥብ ታርቋል

ከጨዋታ ጨዋታ ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ቢያሳዩም እንቅስቃሴውን በውጤት ማጀብ ተስኗቸው የቆዩው ነብሮቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት መከላከያን በመርታት የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥባቸውን ማግኘት ችለዋል።

ቡድኑ አሁንም ቢሆን በስድስት ነጥብ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኝም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን ለተመለከተ ግን የሚገኝበት የሊጉ ደረጃ እንደማይመጥነው መመስከር ይቻላል።

ምናልባት ከውጤታማ ለመሆን ከመቸገራቸው በስተጀርባ ይነሳ የነበረው ጉዳይ ቡድኑ ግቦችን ለማስቆጠር መቸገሩ እንደነበር ይነሳል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዑመድ ዑኩሪ በጉዳት አለመኖሩን ተከትሎ የቡድኑን የፊት መስመር እየመሩ የገቡት ባዬ ገዛኸኝ እና ሀብታሙ ታደሰ እንደ ወትሮው ሁሉ ጥሩ ጥረት አድርገው ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ውጤት መምራት ችለዋል።

ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸውን ተከትሎ ጫና ውስጥ የሰነበቱት አሰልጣኝ መሉጌታ ምህረት እና ስብስባቸው በዚህ ድል መነሻነት ሀዲያ ሆሳዕናን በሰንጠረዡ ወደ ላይ የማስጠጋት ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

👉 ጥራት ያላቸው ዕድሎችን ወደ ግብነት መቀየር የተሳነው አዳማ ከተማ

ሰባተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር እስካሁን አራት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻሉት አዳማ ከተማዎች እጅግ ደካማ የማጥቃት አፈፃፀማቸው አሁንም ቡድኑን ከሦስት ነጥብ እንተደራራቀ እንዲቀጥል አድርጎታል።

በውድድር ዘመኑ በአምስት ጨዋታዎች አቻ የተለያየው አዳማ ሁለቱን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አንድ አቻ ተለያይቷል። አዳማዎች በወላይታ ድቻ 1-0 ሲሸነፉ ጅማ አባ ጅፋርን ደግሞ በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

የአዳማ ከተማን ሰባት ጨዋታዎችን ከውጤት ባለፈ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር ቡድኑ በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት መሆኑ በመልካምነቱ የሚታይ ቢሆንም በተቃራኒው በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ ግብ በታች የማስቆጠሩ ነገር ስጋት ውስጥ የሚከትው ነው።

ከጊዮርጊስ ጋር አቻ በተለያዩበት የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማዎች በጣም በትንሹ አራት ወደ ግብነት መቀየር የሚገባቸውን እጅግ ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ያለቀላቸው ባይሆኑም በጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተመልክተናል። ነገር ግን አሁንም ቢሆንም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ በተመሳሳይ በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም ከማዕዘን ምት ከተገኘችው የአማኑኤል ጎበና ግብ ውጪ ተጨማሪ ግቦችን ማግኘት አልቻለም።

በማጥቅት ረገድ እንደ ቡድን ተፈላጊው ጉዳይ ዕድሎችን መፍጠር ቢሆንም በአዳማ ከተማ ደረጃ ግን የሚፈጠሩ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት መቀየር አለመቻል በጣም አሳሳቢ ነው። ዕድሎችን የመፍጠር ሂደት እንደ ቡድን የሚከወን ተግባር ቢሆንም በተቃራኒው የግብ ዕድሎቹ መጨረሻ ላይ ተገኝቶ ግቦችን የማስቆጠሩ ሂደት በግለሰቦች ብቃት ላይ የተመሠረተ ነው።

ዳዋ ሆቴሳ አለመኖሩን ተከትሎ ባለፉት ጨዋታዎች የቡድኑን የፊት መስመር እየመሩ የሚገኙት ተጫዋቾች በተወሰነ መልኩ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈለጉበት የብቃት ደረጃ ላይ ናቸው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ከከፍተኛ ሊግ የመጣው አቡበከር ወንድሙ ከሊጉ ጋር ራሱን የሚያስተካክልበት የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ላይ ሲገኝ በተመሳሳይ ከከፍተኛ ሊግ ከመጣ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ላይ የሚገኘው አብዲሳ ጀማልም በተመሳሳይ በጉዳት የውድድር ዘመኑ ጅማሮው እንደተጠበቀ አልሆነለትም ፤ አሜ መሀመድም የቀደመ ብቃቱ ላይ አይገኝም።

ከዳዋ ጉዳት ባለፈ አዳማ እጁ ላይ ያሉት አጥቂዎችን የአጨራረስ ብቃት ለማሻሻል ወሳኝ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል። አጥቂዎቹ በራስ መተማመናቸውን መልሰው እንዲያገኙም በቶሎ ኳስ እና መረብን ወደማገናኘቱ መንፈስ እንዲመለሱ ይጠበቃል። ይህን ለማድረግ ግን የቡድኑ ዕድሎችን የመፍጠር አቅምም እየጎለበተ መቀጠል ይኖርበታል።

👉 ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ነጥቡን አሳክቷል

በመጀመሪያዎቹ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ነጥብ ማስመዝገብ ተስኗቸው የዘለቁት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የነበራቸውን መርሐግብር ያለ ግብ በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ማሳካት ችለዋል።

በንፅፅር በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት የመከላከል እንቅስቃሴ እና ከፍተኛ ጥረት ነጥቡን ምን ያህል ይፈልጉት እንደነበረ ማሳያ ነበር።

እርግጥ በሊጉ በክለቦች መካከል ያለው የነጥብ መቀራረብ እስካሁን ምንም ድል ማስመዝገብ ላልቻሉት ጅማዎች ተስፋ የሚሰጥ ነው። በአንድ ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት አባ ጅፋሮች አሁን ላይ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ ስድስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። ይህም አሁን ካለው ሁናቴ አንፃር ሊደረስበት የሚችል ልዩነት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው።

ጅማዎች በቀጣዩቹ የጨዋታ ሳምንታት ሊጉ ለአፍሪካ ዋንጫ ከመቋረጡ አስቀድሞ በሚኖሩት ሁለት ጨዋታዎች (ከአዲስ አበባ ከተማ እና ሰበታ ከተማ) ውጤቶችን በማስመዝገብ ከአናታቸው ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያገኙትን የመጀመሪያ ነጥብ እንደ መስፈንጠርያ በመጠቀም የውድድር ዘመኑን ጉዞ ማቃናት ይገባቸዋል።

👉 በወጥነት ወጥ ያልሆነው ድሬዳዋ ከተማ

ሰባተኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር በወጥነት ወጥ ያልሆነው ቡድን ድሬዳዋ ከተማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ የተቸገረው ቡድኑ በአንድ የጨዋታ ሳምንት ነጥብ እያስመዘገበ በቀጣዩ ነጥብ እየጣለ ጉዞውን ቀጥሏል።

ሊጉን ወላይታ ድቻን በመርታት በድል የጀመረው ድሬዳዋ በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና ፍፁም የሆነ የበላይነት ተወስዶበት ተሸንፏል። በሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በአራተኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን በአሳማኝ ሁኔታ ረትቷል። በወልቂጤ ከተማ በአምስተኛው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ሲደርስበት ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ወጥቶ በዚህኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2-0 ተሸንፏል።

ወጥ ያለመሆን ነገር የሊጉ መገለጫ ባህሪ መሆኑ ቢታመንም የድሬዳዋ ከተማ ግን በአስገራሚው አዎንታዊ እና አሉታዊ ውጤቶችን እያፈራረቀ የማስመዝገብ አካሄዱ የተለየ ያደርገዋል። በዚህም አካሄድ መሠረት ቡድኑ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አዎንታዊ ውጤት ያስመዘገብ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

ከባለፉት ዓመታት አንፃር የተሻለ ስብስብን ይዘው ወደ ውድድር የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከጨዋታ ጨዋታ አሳማኝ እንቅስቃሴ ለማሳየት እየተቸገሩ ይገኛሉ። እንደቀደሙት ዓመታት ላለመውረድ የሚፍጨረጨር ሳይሆን ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት ውጥን ያላቸው ድሬዎች ይህን ለማሳካት ከአሁኑ በተሻለ በወጥነት መንቀሳቀስ የግድ ይላቸዋል።