“በጥናቱ መሰረት ከራሳችን ጀምሮ ሊነካን የሚችል ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፤ ስለዚህ ያንን አንፈራም…” አቶ አብነት ገብረመስቀል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የአስተዳደር መዋቅሩን ለማዘመን የሚረዳውን ውል አስሯል።

በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የመዝናኛ ማዕከል ከስምንት ሰዓት አንስተናል በተጀመረው መግለጫ ላይ በቅድሚያ ማብራሪያ የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ነበሩ። እንደ አቶ አብነት ገለፃም ከዚህ ቀደም ክለቡ ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ውስጥ ክለቡን በሙከራ ላይ ከተመሰረተ አካሄድ ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማምጣት ዕቅድ እንደነበረው አንስተው የዛሬው ስምምነትም ይህንኑ የተመለከተ እንደሆነ ጠቁመዋል። በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ የውስጥ አደረጃጀቱን ለማዘመን ድንቅ ኢትዮጵያ ብራንዲንግ ጋር ለመስራት መወስኑን አስተዋውቀዋል።

የድንቅ ኢትዮጵያ ብራንዲንግ ኮንሰልታንት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አየለም ድርጅታቸው በክለቡ ዙሪያ ሊሰራው ስላሰበው ጥናት ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ኤርሚያስ ለ15 ዓመታት በታላቁ ሩጫ ስለነበራቸው ሚና አንስተው ሩጫ ላይ ሲሰሩ ቢቆዩም ለእግርኳስም ቅርብ መሆናቸውን በማንሳት ወደ ዋናው ገለፃ ገብተዋል።

አቶ ኤርሚያስ ድርጅታቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ ጋር የክለቡን አጠቃላይ አደረጃጀት የተመለከተ ሰፊ ጥናት ለመስራት ላለፉት አራት ወራት ሲነጋገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። እንደ ፕሬዘዳንቱ ገለፃም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የሚሰሩት ጥናቱ ሁለት ክፍሎች ይኖሩታል። ከዚያ ቀደም ብሎ ግን የውጪ ድርጅት የሆነው ቢ ዲ ኦ አካውንቲንግ እና ኮንሰልቲንግ ክለቡ ያለበትን አሁናዊ አጠቃላይ የአወቃቀር ጤና ይመረምራሉ። በመቀጠል ከሁለቱ የጥናት ክፍሎች ቀዳሚው የሆነው የክለቡ የሰው ኃይል አስተዳደር አወቃቀር ምን ይምሰል በሚለው ላይ በዘርፉ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ባላቸው አቶ ዘነበ ገብረስላሴ አማካይነት ይከወናል። ሁለትኛው ክፍል ደግሞ ማርኬቲንጉን በድንቅ ኢትዮጵያ አማካይነት ከደጋፊዎች ጋር ፣ ከስፖንሰርሺፕ እና የማርኬቲንግ ስራውን የተመለከቱ ጥናቶች ይደረጋሉ።

“ክለቡ ለሀገርም የሚተርፍ መሰረተ ልማት አለው” ያሉት አቶ ኤርሚያስ ከቦርዱ እና ከደጋፊው ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ እና ጥናቱም በውስጡ የተከፋፈሉ የቀን ገደቦች ያሉት ሲሆን በጥቅሉ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ያህል እንደሚፈጅ ጠቁመዋል።

ወደ መድረኩ ተመልሰው ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት አቶ አብነት ቦርዱ ጥናቱን ሲጠናቀቅ በተግባር ለማዋል ያለውን ቁርጠኝነት “ከራሳችን ጀምሮ ሊነካን የሚችል ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ በጥናቱ መሰረት። ስለዚህ ያንን አንፈራም ፤ መደረግ ያለበትን አድርገን መቀየር ያለበትን ቀይረን ስፖርቱን ማሳደግ እና ሀገራችንን መቀየር አለብን።” በማለት ገልፀውታል።