ኤልኔት ግሩፕ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚሳተፍበት የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመታደም ያሰቡ ደጋፊዎችን ለመውሰድ ያዘጋጀውን ጉዞ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚካፈል ይታወቃል። ከአራት ሳምንት ያነሰ ጊዜ የቀረው ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ሲሳተፍ ደጋፊዎችም ከጎኑ እንዲሆኑ ከዚህ ቀደም በሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን አማካኝነት የጉዞ መርሐ-ግብር መዘጋጀቱ መገለፁ ይታወሳል። አሁን ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ አጋር የሆነው ኤልኔት ግሩፕ ደጋፊዎች ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ ያዘጋጀውን የጉዞ ፓኬጅ በተመለከተ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በኤሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።
መስከረም 24 2014 ለአራት ዓመታት የሚቆይ የ15 ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት የተፈራረመው ኤልኔት በስሩ ከሚገኙት ተቋሞች መካከል በኤልኔት ቱር ኤንድ ትራቭል አማካኝነት የደጋፊዎች ጉዞ አዘጋጅቷል። ከጥር አንድ ጀምሮ በሚደረገው ውድድር ላይ ተቋሙ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ከኢትዮጵያ አይር መንገድ ኢቲ ሆሊደይስ ጋር በመተባበር በርካታ ደጋፊዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በተሻለ ጥራት እና ደህንነቱን በጠበቀ ሁኔታ ብሔራዊ ቡድኑን ደግፈው፣ ባህላችንን እና አንድነታችንን አሳይተው፣ ሐገር ጎብኝተውና ተዝናንተው የሚመለሱበትን ዕድል ማዘጋጀቱን በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
ይህንን አፍሪካ ዋንጫ በአካል ለማየት የሚፈልግ ደጋፊም ፍላጎቱን ለማሟላት ሁለት የተለያዩ ፓኬጆች መዘጋጀታቸው ተገልፇል። በዚህም የመጀመሪያው ፓኬጅ ለአስራ አንድ ቀናት የሚቆይ በኢቲ ሆሊደይስ የተመረጠ የሆቴል ቆይታ፣ የምግብ፣ በኢቲ ሆሊደይስ አጋሮች የሚመራ የጉብኝት ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ወጪን እንዲሁም የትኬት፣ የቪዛ፣ የኢንሹራንስና የኮቪድ ምርመራ ወጪን የሚያካትት ሲሆን ሁለተኛው ፓኬጅ ደግሞ ለአስራ ሰባት ቀናት የሚቆይ በኢቲ ሆሊደይስ የተመረጠ የሆቴል ቆይታ፣ የምግብ፣ በኢቲ ሆሊደይስ አጋሮች የሚመራ የጉብኝት ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ወጪን እና እንደ አንደኛው ፓኬጅ የትኬት፣ የቪዛ፣ የኢንሹራንስና የኮቪድ ምርመራ ወጪን ያካተተ እንደሆነ ተብራርቷል።
አንድ ደጋፊም የምድብ ጨዋታዎችን ለማየት ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝሮች በመጠቀም የሚያወጣው ወጪም አንድ መቶ ሠላሳ አምስት ሺ (135,000) ብር እንደሆነ ተነግሯል። ከዚህ ውጪ የተወሰኑ ጋዜጠኞችንም ወደ ስፍራው ለመውሰድ እንደታሰበ ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋዜጠኞች ምርጫ ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።