በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኞች ዙርያ የተመለከትናቸውን ጉዳዮች የሦስተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙት ገብረመድህን ኃይሌ…
በአሁኑ ሰዓት በሊጉ እያሰለጠኑ ከሚገኙ አስራ ስድስት አሰልጣኞች ውስጥ የሊጉን ዋንጫ በሦስት አጋጣሚ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ማንሳት ከቻሉት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቀጥሎ ደማቅ የስኬት ታሪክ ባለቤት የሆኑት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ዘንድሮ በሲዳማ ቡና ደጋፊዎች የሚፈለገውን ውጤት እያስመዘገቡ አይገኝም በሚል ከፍተኛ ተቃውሞን እያስተናገዱ ይገኛሉ።
በ2013 የውድድር ዘመን በ11ኛው የጨዋታ ሳምንት ከክለቡ ጋር የተለያዩትን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን የተኩት አሰልጣኝ ገብረመድህን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው በማከል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ከወራጅ ቀጠናው በዘጠኝ ነጥቦች ርቀው በ31 ነጥብ በሊጉ ዘጠነኛ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ችለዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ሲዳማን ከተረከቡ ወዲህ በነበሩት አስራ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ቡድኑን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በሚገባ ማሻሻል ችለው ነበር። በተለይም በመጀመሪያዎቹ 11 ጨዋታዎች 17 ግቦችን አስተናግዶ በተቃራኒው 7 ብቻ ግቦችን ቢያስቆጥርም በተቀሩት አስራ ሦስት ጨዋታዎች ግን ያስቆጠረው የግብ መጠን ወደ 20 ከፍ ሲል በተቃራኒው የተቆጠረበትም የግብ መጠን ወደ 14 ዝቅ ብሎ እንደነበር መመልከት እንችላለን።
በዚህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ደስተኛ የነበሩት የክለቡ የቦርድ አመራሮች ከአሰልጣኙ ጋር ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የሚያቆያቸውን ስምምነት በክረምቱ መፈፀም የቻሉ ሲሆን እርግጥ በሰንጠረዡ በክለቦች መካከል ያለው የነጥብ መቀራረብ እና አንድ ጨዋታ ማሸነፍ እና መሸነፍ የሚፈጥረው ልዩነት እንዳለ ሆኖ በሲዳማ ቡና የመጀመሪያው ሙሉ የውድድር ዘመን አጀማመራቸው በተጠበቀው ልክ እየሆነ አይገኝም።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቡ አምና በሊጉ በማቆየት ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው አጥቂዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ኦኪኪ አፎላቢን ጨምሮ ተከላካዮቹን ፈቱዲን ጀማል እና ሰንደይ ሞቱኩን የመሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾቹ ጋር ሲለያይ በሌሎች ተጫዋቾች ለመተካት ያደረገው ጥረት ሜዳ ላይ እስካሁን ውጤት እያስገኘለት አይገኝም።
ዐምና በሊጉ 31 ግቦችን በማስተናገድ ከድሬዳዋ ጋር በጣምራ የሊጉ ደካማው የመከላከል ክብረወሰን የነበረው ሲዳማ በሁለተኛ ዙር መሻሻሎችን ቢያሳይም ዘንድሮ ላይ ዳግም ይህ ችግር የማገርሸት ምልክት እያሳየ ይገኛል። በፋሲል ከነማ አራት ግቦችን ማስተናገዱን ተከትሎ ከጅማ አባ ጅፋር ቀጥሎ የደካማ የተከላካይ መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ በርከት ያሉ ግለሰባዊ ስህተቶች የሚፈፅም እንዲሁም እንደቡድን በመከላከል ረገድ ክፍተት ያለበት መሆኑን እየተመለከትን እንገኛለን።
በማጥቃቱም ረገድ አዲስ ግደይን በ2012 ክረምት ያጣዉ ሲዳማ አምና በተወሰነ መልኩ በኦኪኪ እና ሲዲቤ በኩል በሁለተኛው ዙር ያንን የቀደመ የመልሶ ማጥቃት አስፈሪነቱን ያገኘ መስሎ ቢቆይም ሁለቱ አጥቂዎች በክረምቱ መልቀቃቸውን ተከትሎ ዘንድሮም አዲስ የማጥቃት ስልት ለመቀየስ ተገዷል።
ሀብታሙ ገዛኸኝ አምና እና ዘንድሮ የቀደመ ማንነቱን ለማግኘት እንደተቸገረ መቀጠሉን ተከትሎ በቡድኑ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይጠበቅ የአጥቂ መስመሩን በዋነኝነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት ይገዙ ቦጋለ ተስፋ እያሳየ ይገኛል። በተጨማሪም ብሩክ ሙሉጌታ እና ፍሬው ሰለሞን በተወሰኑ ጨዋታዎች ልዩነት ሲፈጥሩ ቢታይም በወጥነት ይህን ለማስቀጠል ተቸግረዋል።
ከእነዚህ ፈተናዎች ጋር እየታገለ የሚገኘው ሲዳማ በደጋፊዎቹ ዘንድ ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ የነበረው ከፍተኛ ተስፋን በሜዳ ላይ መመልከት አለመቻላቸው ተከትሎ በተለይም በሮድዋ ደርቢ በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፉበት ጨዋታ ጀምሮ ተቃውሞዎች እየተደመጡ ይገኛሉ። ይህ ተቃውሞ በተለይ ደግሞ ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል 4-0 በተሸነፉበት ጨዋታ በጣም ተጋግሎ ተመልክተናል።
አሰልጣኙም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ስለሁኔታው ሲገልፁ
“ክለቡ የፈለገውን እርምጃ ቢወስዱብኝ ምንም ችግር የለውም። እኔ የምቀበለው ነገር ነው። እኔ ግን ምንም ተፅዕኖ የለብኝም። የምታየው ደጋፊ ግን ይላል። እነሱ መብታቸው ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ መስራትም ከባድ ነው የሚመስለኝ።” ሲሉ ተደምጠዋል።
አሰልጣኙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ተሻግረው ቡድኑን ወደ ከፍታው ይመለሱታል ወይ የሚለው ጉዳይ በቀጣዮቹ ሳምንታት የምንመለከተው ይሆናል።
👉 ጨዋታዎችን የመገምገም ጉዳይ
በሊጋችን በመስራት ላይ የሚገኙ አሰልጣኞች ጨዋታዎችን ሊያሸንፉ የቻሉባቸውን ሆነ የተሸነፉባቸውን ሁነቶችን በምልሰት በመገምገም ለማሻሻል ሆነ ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶችን እምብዛም እየተመለከትን አንገኝም።
እርግጥ በሀገራችን አውድ የአሰልጣኞች ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ በቡድኖች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዙርያ በሚነሱ ሀሳቦች በቅድሚያ የሚወቀሱትም ሆነ የሚወደሱት ዋና አሰልጣኞች እንደመሆናቸው ይህን የጨዋታዎች በምልሰት ተመልክቶ የመገምገም ጉዳይም በዋና አልያም በምክትል አሰልጣኞች ላይ የሚጣል ኃላፊነት ነው።
ታድያ በዚህ ረገድ ያለው አረዳድ እና ጥረት ደካማ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከጨዋታ ጨዋታ ፍፁም የተለያዩ ድግግሞሽ የማይታይባቸውን የጨዋታ መንገዶች እየተመለከትን ከመገኘታችን በስተጀርባ ይህ ሂደት አንደኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
ለአብነት ያህል ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን የረቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ይበልጥ በቀጥተኛ አጨዋወት እንዲሁም በተደጋጋሚ ከመስመሮች በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የኢስማኤል ኦሮ-አጎሮን ከሌሎች ጨዋታዎች በተሻለ ያማከለ አጨዋወትን ተግባራዊ በማድረግ ልዩነት መፍጠር ችለው እንደነበር አይዘነጋም። ይህም አጨዋወት በተወሰነ መልኩ ደካማ የነበረውን የቡድኑን የማጥቃት አጨዋወትን የተለየ ገፅታ አላብሶት እንደነበረ መታዘብ ችለናል።
ታድያ በዚህ ሳምንት ደግሞ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት የተጠቀሙበትን እና ውጤት ያስገኘላቸውን መንገድ ይበልጥ አሻሽለው እና አጎልብተው ይመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአዳማው ጨዋታ ሜዳ ላይ የተመለከትነው እንቅስቃሴ ግን ፍፁም ተፃራሪ የነበረ ነበር።
የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ሳይቀየሩ ባሳለፍነው ሳምንት ምርጥ የነበረው ቡድን ቢያንስ የተወሰኑ የጨዋታ ሂደቶች (Element) ማስቀጠል ሳይችል ሲቀር በባለፈው ጨዋታ ያሸነፈበት መንገድ ተጠንቶ የተተገበረ ሳይሆን በተጫዋቾች ደመነፍሳዊ ትግበራ የተገኘ ይሆን እንዴ ብለን እንድንጠይቅ የሚያሰገድድ ይሆናል።
እርግጥ ቡድኖች መሰረታዊ ነገራቸውን ሳይለቁ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁናቴ ራሳቸው ማስተካከላቸው የሚጠበቅ ቢሆንም የባለፈውን ውጤታማ ለመተግበር የሚያስችሉ ምቹ ሁናቴዎች በሜዳ ላይ ስለመኖራቸው በግልፅ እየታየ ቡድኑ ይህን የጨዋታ መንገድ ለማስቀጠል መቸገሩ በአሰልጣኞቹ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳል።
ለማሳያነት የቅዱስ ጊዮርጊስን አነሳን እንጂ ይህ ጉዳይ የአብዛኞቹ ቡድኖች የወል መገለጫ ነው። በመሆኑም አሰልጣኞች የጨዋታ ምስሎችን የማግኘቱ ዕድል ሰፊ በሆነበት በዚህ ጊዜ የድል ሚስጥራቸውን ሆነ የሽንፈት ምክንያታቸውን ጠንቅቀው ለመረዳት መጣር እና ለማሻሻልም ሆነ ለማዳበር ጠንካራ ሥራዎችን መስራት ይኖርባቸዋል።
👉 የዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ እና የአቡበከር ናስር ምክክር
ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና 2-0 ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ እና አቡበከር ናስር ቆመው ሲነጋገሩ ተመልክተናል።
በጨዋታው ሁለት ግቦችን ከፍፁም ቅጣት ምት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመጀመሪያ ፍፁም ቅጣት ምት “150% አስመስሎ መውደቅ ነው” ሲሉ ፍፁም ቅጣት ምቱን የተሰጠበትን መንገድ ተቃውመው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው አቡበከር ናስር ከአሰልጣኙ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ሲናገር ዘማርያም ፍፁም ቅጣት ምቱ በተሰጠበት አጋጣሚ በቂ ንኪኪ ስላልነበረ ዳኛው እንኳን ተሳስቶ ፍፁም ቅጣት ምቱን ቢሰጥም አቡበከር ተገቢ አይደለም ብሎ የዳኛውን ውሳኔ ማስቀየር እንደነበረበት እንደነገሩት ገልፆ እሱም ስለሁኔታው ሲያብራራ በነጥብ ጨዋታዎች ላይ ይህን ማድረግ ከባድ እንሆነ አስረድቷል።
👉 ሥራ ስለማጣት አለመስጋት…
በሊጉ ውስጥ በጫና ውስጥ የሚገኙ አሰልጣኞች ይፋዊ በሆኑም ሆነ ባልሆኑ መንገዶች አሁን እየሰሩ ከሚገኙበት ኃላፊነት ቢነሱም ሥራ ስለማጣት እንደማይሰጉ ሲናገሩ ይደመጣል። ይህን ጉዳይ ግን በትኩረት ማየት ይፈልጋል።
እርግጥ አሰልጣኞቹ በቀደመ ኃላፊነቶቻቸው ማስመዘገብ የቻሉት ውጤት ምንም ሆነ ምን በፕሪሚየር ሊጉ ያሰለጠኑ አሰልጣኞች በሊጉ እየተዘዋወሩ የማሰልጠናቸው ነገር የተለመደ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከክለቦች ቢሰናበቱም የጊዜ ጉዳይ እንጂ መልሰው ስራ ማግኘት እንደማይቸገሩ በደንብ የሚያሳብቅ ነው።
ክለቦችም አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ደፋር ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ አሰልጣኞች የመሸጋሸግ ነገር የተለመደ ነው። ይህ አካሄድ አዳዲስ ሀሳብ ያለቸው ወጣት አሰልጣኞችን በሊጉ በትልልቅ ኃላፊነቶች እንዳናይ እያደረገን መጥቷል።
ይህ ሂደት በሊጉ እያሰለጠኑ የሚገኙ አሰልጣኞች ያለ ሀሳብ ውጤት መጣም አልመጣም በሊጉ የመስራታቸው ነገር ሳይታለም የተፈታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እምብዛም ራሳቸውን ለማሻሻልም ሆነ በተለየ መንገድ ተፎካካሪ ቡድን ስለመገንባት እንዳይጨነቁ እያደረጋቸው ይሆን ?